Wednesday, June 27, 2012

'ነጻ ፈቃድ - Free will' ያለው ማነው???

by Tibebe Belay  ·

“ለሰው ልጅ የተሰጠውን ነጻ ፈቃድ እግዚአብሔርም ሆነ ሰይጣን አይጋፉትም። ይህ ማለት እግዚአብሔር በግድ ሰዎችን አያጸድቅም። ሰይጣንም በግድ ሰዎችን ኃጢአት አያሰራም። «ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።» ያዕ ፩፡ ፲፬። እግዚአብሔር የመዳን (የሕይወት) ጥሪ፡ ሲያቀርብ ሰይጣን የኃጢአት (የሞት) ጥሪ ያቀርባል። ሰው ከሁለቱ አንዱን መምረጥ ይችላል። የመረጠውን ነገር ውጤት ግን ይቀበላል እንጂ አይመርጥም።”

የዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ከላይ የምታነቡት በእሕት ታምረ ጽዮን የቀረበው ሀሳብ ነው። በመሰረቱ ይህ ሀሳብ ሁሉም ሐይማኖቶች የሚቀበሉት ሲሆን በዘመናት መካከል እየዳበረ የመጣና በሁሉም ዘንድ እውነትነቱ ጥርጥር የሌለው እስኪመስል ድረስ ተቀባይነትን ያገኘ ሃሳብ ነው። ነገር ግን እውነቱ ከብዙዎች ተሰውሮአል። ይህን ለመረዳት እንዲህ ብለን እንጠይቅ፣ የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ አለው?? በእርግጥ ነጻ ፈቃድ ያለው ማነው??

“… እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥኩ የሥጋ ነኝ። የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም።” (ሮሜ.7፡14-15)
እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ በዔደን ገነት ሲያኖረው በሞትና በሕይወት መካከል መምረጥ የሚችል ነጻ ፈቃድ ያለው ፍጡር አድርጎት ነበር። ለዚህም ነው “… ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ።” የሚል ትዕዛዝ የሰጠው። ነገር ግን አዳም በእባቡ ተንኮል፣ በሴቲቱም መታለል ምክንያት ሞትን መረጠ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ዘር በሙሉ፣የቀደመው አባቱ አዳም በመረጠለት በዚህ ክፉ ምርጫ ሰበብ የኃጢአትና የሞት ባሪያ ሆኖ በምድር ላይ መብዛቱን ጀመረ። ታድያ፤ ማነው ይህን የወደቀ ሰው በሞትና በሕይወት፣ በመልካምና በክፉ፣ በጽድቅና በኃጢአት… መካከል መምረጥ የሚችልበት “ነጻ ፈቃድ”፣ መርጦም የወደደውን ማድረግ የሚችልበት ኃይልና ጉልበት ያለው ፍጡር ነው ብሎ የሚከራከር?? ሰው ሁሉ ኃጢአትን እያደረገ የሚሞተው በራሱ ፈቃድና ምርጫ ነው ብሎ የሚያስብ፣ ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም መግባቱን፣ በኃጢአትም ምክንያት ሞት ለሰው ሁሉ መድረሱን፣ ደግሞም “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ...” ተብሎ መጻፉን መጽሐፉን ገልጦ ያንብብ!!!

እስራኤላውያን ለአራት መቶ አመታት በግብጽ ምድር በነበሩበት ጊዜ ሁሉ የፈርዖን ባሪያዎች ነበሩ። ነጻ አውጪው ሙሴ እስኪመጣ ድረስ በዚያ የባርነት ምድር በእግር ብረት ታስረው የፈርዖንን ጡብ ከመጠፍጠፍ ውጪ ሌላ ምን ምርጫ ነበራቸው?? ሰለዚህም “አባቶቻችሁ በግብጽ ምድር በባርነት በነበሩ ጊዜ…” ተብሎ ተጻፈባቸው። የወደደውን ማድረግ ለማይችልና በባርነት ላለ ሕዝብ የሚያስፈልገው ቀንበሩን ሰብሮ ነጻነቱን የሚያውጅለት ነጻ አውጪ እንጂ “ምርጫ” አይደለም። (በረሀብ ይሰቃይ ለነበረ ሕዝብ ‘ለምን ኬክ አይበሉም’ የሚል ‘የምግብ ምርጫ’ ያቀረበችውን ልዕልት ስም ረሳሁት) ለዚህም ነው እግዚአብሔር “በግብጽ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፣ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሳ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ፣ ከግብጻውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ…..” ብሎና ሙሴን ለዚህ ዓላማ አስነስቶ “በበረታችና በፀናች ክንድ” ሕዝቡን ከግብጽ ምድር አውጥቶ በምድረ በዳው መንገድ ወደተስፋይቱ ምድር የመራቸው።

እዚህ ላይ አንድ የከበረ እውነት ላካፍላችሁ!! ከላይ እንዳልኩት በባርነት ላለ ሕዝብ የሚያስፈልገው ነጻ አውጪ እንጂ “ምርጫ” አይደለም። ይህን የሚያውቀው የእስራኤል አምላክ ለሕዝቡ የሕጉን ትዕዛዝ የሰጣቸው ደግሞም የሕይወትና የሞት፣ የበረከትና የመርገም…. ምርጫዎችን በፊታቸው ያቀረበው በግብጽ ምድር በባርነት ባነበሩበት ጊዜ ሳይሆን፣ በጸናችና በበረታች ክንድ ከዚያ የባርነት ምድር አውጥቶአቸው በምድረ በዳው በኩል ወደተስፋይቱ ምድር ይመራቸው በነበረበት ጊዜ ነው።
“በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ። እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እነዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።” (ዘዳ.30፡19-20)

“የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው። ለድሆች የምስራች እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፣ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፣ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል።” (ኢሳ.61፡1)
ይህ ከሁሉ አስቀድሞ በራሱ በወንጌሉ ባለቤት በክርስቶስ ከዚያም በዘመናት ሁሉ መካከል የወንጌል ሰባኪነትን አደራ በተቀበሉና በእግዚአብሔር መንፈስ ተቀብተው በተላኩ እውነተኛ የቃሉ አገልጋዮች የተሰበከና የሚሰበክ “የመንግሥት ወንጌል” ነው። በእግዚአብሔር መንፈስና ኃይል ብቻ ሊነገር የሚችለውና ሌላ ማንንም ሳይሆን ክርስቶስን ብቻ የሚሰብከው ይህ ወንጌል ለሰዎች ሲነገር አስቀድሞ የሚያደርገው የሚሰሙትን ሁሉ ከዚህ ዓለም ባርነትና ከሰይጣን እስራት መፍታት ነው። ሰው አስቀድሞ የእግዚአብሔር የማዳኑ ኃይል በሆነው የክርስቶስ ወንጌል ከሰይጣን ባርነት ካልተፈታ፣ በዓለም እስር ቤት ውሰጥ ያለና ከኃጢአት በታች እንዲሆን ለገዛ ስጋው የተሸጠ ባሪያ ነው። ያኔ በጸናችውና በበረታችው የእግዚአብሔር ክንድ አማካኝነት ቀይ ባህር ተከፍሎላቸው ከፈርዖን ሰራዊት ያመለጡትና፣ “ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባህር ጣለ!” የሚል የነጻነት መዝሙር እየዘመሩ ወደተሰጣቸው የበረከት ምድር መትመም እንደጀመሩት እስራኤላውያን፤ ይህን ወንጌል ሰምተው በእውነት ከሰይጣን እስራት የተፈቱ ወገኖች ብቻ፣ “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አውጣን!!...” የሚለውን የአዲሰ ኪዳን የነጻነት መዝሙር ሊዘምሩ ይችላሉ። ይህ ነጻነታቸውም የሚመራቸው አግዚአብሔርን በመስማትና በመታዘዝ ወደሚወረሰው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ነው። አሁን ከላይ ለጠየቅነው ጥያቄ መልስ እንስጥ!!! በእርግጥ በሞትና በሕይወት፣ በጽድቅና በኃጢአት፣ በበረከትና በመርገም፣ በመልካምና ክፉ…. መካከል የመምረጥ ነጻነትን ያገኙት እነዚህ የክርስቶስን ወንጌል በመቀበል ከአግዚአብሔር መንፈስ ዳግመኛ የተወለዱ የእግዚአብሔር ልጆች ብቻ ናቸው።

“እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ዕዳ አለብን፣ እንደሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም። እንደሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና።” (ሮሜ.8፡12-14)

No comments:

Post a Comment