Wednesday, June 27, 2012

እግዚአብሔር ሥራውን ይመዝናል - ጥቂት ስለ እግዚአብሔር ፍርድ!!

በዘመናት ውስጥ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች መካከል በትህትናቸው የተመሰከረላቸው ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ደግሞም በትዕቢታቸው ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች የወደቁ ሰዎችን ታሪክ አንብበናል። ከእነዚህ ትዕቢተኞች መካከል እንደባቢሎኑ ንጉስ- ናቡከደነፆር ከፍተኛው የትዕቢት ደረጃ ላይ የደረሰ ማንም አልነበረም። በትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበውን ታሪኩን እንደምናነበው ከአሕዛብ ነገሥታት መካከል እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ ያደረገው ደግሞም ያለ ልክ ያዋረደው እንደ ናቡከደነፆር ያለ ንጉስ ማንም የለም።

የንጉሱ ናቡከደናፆር ትዕቢት እጅግ በጣም ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረሱ የታወቀው፣ ከፍ ባለው የቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ቆሞ ፣ “… ይህቺ እኔ በጉልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራህዋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?” ብሎ በተናገረበት ጊዜ ነበር። እጅግ አስፈሪውም የእግዚአብሔር ፍርድ በዚህ ትዕቢተኛ ንጉስ ላይ የመጣው ይሄው የትዕቢት ቃሉ ከአፉ በወጣበት ቅጽበት ነበር። ልቡ ከሰው ልብ ተለወጠ፣ የአውሬም ልብ ተሰጠው፣ ጠጉሩም እንደንስር ጥፍሩም እንደወፎች እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፣ እንደበሬም ሳር በላ፣ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ! ፍርድህ እንዴት አስፈሪ ነው!! ደግሞም ጽድቅ የተትረፈረፈበት ነው!!!!

እግዚአብሔር ሥራውን የሚመዝን፣ በጥበብና በማስተዋል የተሞላ፣ ለዕውቀቱም ወሰን የሌለው ድንቅ አምላክ ነውና በዚህ ትዕቢተኛ ንጉስ ላይ እንዲህ አይነቱን አስፈሪ ፍርድ ሲበይን ግን ያለ ዓላማ አልነበረም። በዚህ አስፈሪ ፍርድ ውስጥ የነበረው የልዑሉ ዓላማና ፍርዱም የሚጸናበት ጊዜ ለንጉሱ እንዲህ ተነቦለት ነበር።
“ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፣ ለሚወደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፣ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፣ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፣ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል።” (ዳን.4፡32)

የሰው ልጆች፣ በተለይም ሐይማኖተኞች ስለ እግዚአብሔር ፍርድ ሲያስቡ ቶሎ ብሎ ወደልባቸው የሚገባው ማለቂያና ፍጻሜ የሌለው የእግዚአሔር ቁጣና ጭካኔው እንጂ፣ ጽድቅ በተትረፈረፈበት ፍርዱ ውስጥ የሚያገኝው ክብርና በትዕቢተኞችና በዐመፀኞች ሕይወት ውስጥ የሚያመጣው የከበረ የማንነትና የሕይወት ለውጥ አይደለም። የዚህ ስህተት መነሻና ምንጩ ደግሞ ከሰባኪዎቻቸው የሚሰሙት ቅጥ የሌለው ዛቻና ማሰፈራሪያ ነው። ከእግዚአብሔር የፍርድ እጅ በታች የመውደቅን አስፈሪነትም ሆነ ከዚህ ክቡር እጅ በታች ከወደቁ በህዋላ የሚገኘውን የሕይወት ለውጥ ሊናገር የሚችል እንደናቡከደናፆር ያለ ሰው ማንም የለም። ለሰባት ዘመን (የዘመኑ ቁጥር ፍጹሙን የእግዚአብሔር አሰራር ያሳየናል) የቆየው የእግዚአብሔር ፍርድ አዲሱን ናቡከደነፆር እንዲህ ይገልፀዋል፡-
“ዘመኑም ከተፈጸመ በህዋላ እኔ ናቡከደነፆር ዓይኔን ወደሰማይ አነሳሁ፣ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፣ ልዑሉንም ባረክሁ፣ ለዘላለም የሚኖረውን አመሰገንሁ፣ አከበርሁትም፣ ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነውና። በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደምናምን ይቆጠራሉ፣ በሰማይም በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፣ እጁንም የሚከለክላት ወይም፡- ምን ታደርጋለህ የሚለው የለም። በዚያን ጊዜም አእምሮዬ ተመለሰልኝ፣ ለመንግሥቴም ክብር ግርማዬና ውበቴ ወደ እኔ ተመለሰ፣ አማካሪዎቼና መክዋንንቶቼም ፈለጉኝ፣ በመንግሥቴም ውስጥ ጸናሁ፣ ብዙም ክብር ተጨመረልኝ። አሁንም እኔ ናቡከደነፆር የሰማይን ንጉሥ አመሰግናለሁ፣ ታላቅም አደርገዋለሁ፣ አከበረውማለሁ። ሥራው ሁሉ እውነት፣ መንገዱም ፍርድ ነውና፣ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና።” (ዳን.4፡34-37)

ከሰባቱ ዘመን ፍርድ በህዋላ የተገኘው ናቡከደነፆር ይሄ ነው። ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ የሚሰለጥን፣ መንግሥትንም ለሚወደው የሚሰጥ፣ ግዛቱም የዘላለም ግዛት የሆነ፣ በሰማይና በምድር መካከል እንደ ፈቃዱ የሚያደርግ፣ ትዕቢተኞችን የሚያዋርድ፣ ለትሁታኑ ፀጋን የሚሰጥ አምላክ መሆኑን የሚያውቅ ናቡከደነፆር!! እግዚአብሔርን የሚያመልክ፣ የሚያከብርና የሚያመሰግን ናቡከደነፆር!! አዲሰ ልብና አዲስ አእምሮ ከውበት ከመንግሥት ክብርና ግርማ ጋር የተመለሱለት ናቡከደነፆር!! እጅግ በጣም የሚገርመው ነገር ግን እንዲህ አይነቱ ሰው የተገኘው “የእግዚአብሔር ሕዝብ” ተብለው ከሚጠሩት እሥራኤላውያን መካከል አልነበረም!!!!!

“አትታበዩ ፣ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፣ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና…..
እግዚአብሔር ይገድላል ============  ያድናልም፣
ወደ ሲዖል ያወርዳል ==============  ያወጣል።
እግዚአብሔር ድሀ ያደርጋል ========= ባለጠጋም ያደርጋል፣
ያዋርዳል========================  ደግሞም ከፍ - ከፍ - ከፍ - ከፍ ያደርጋል”  (1ሳሙ.2፡3-7)

በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ በጽድቅ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣንን ከአባቱ የተቀበለው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱሰ ክርስቶሰ እንዲህ ይላል፡-
“… ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፣ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ሕያው ነኝ ፣ የሞትና የሲዖል መክፈቻ አለኝ።”  (ራዕ.1፡18)

No comments:

Post a Comment