by Tibebe Belay on Wednesday, April 18, 2012 at 9:50pm ·
ሓዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ሁለተኛው መልእክቱ በምዕራፍ 10፡1-13 ላይ ስለ እስራኤላውያን በተናገረው ክፍል ላይ እንዲህ የሚል ጠንካራ ቃል ተጽፎ እናገኛለን፡-
“እግዚአብሔር ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም በምድረ በዳ ወድቀዋለና።…. ይህም ሁሉ እንደምሳሌ ሆነባቸው፣ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገስጸን ተጻፈ።”
አንድ ኢየሱሰ ክርስቶሰን እንደ ግል አዳኙ በመቀበል ዳግመኛ የተወለደ ከርስቲያን፣ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ምድር ለመውረስ በባሕር መካከል የተሻገሩትንና ከሙሴ ጋር ለመተባበር በደመናና በባሕር የተጠመቁትን እስራኤላውያንን ይመስላል። እስራኤላውያኑ ሙሴን ለመተባበር መጠመቃቸው፣ እርሱ የሚላቸውን በመስማትና በመታዘዝ ደግሞም ቀን በደመና ሌሊት በእሳት አምድ የሚመራቸው የእሥራኤል ቅዱስ በሚያሳያቸው መንገድ ሁሉ እየተጉዋዙ ወደተሰጣቸው የበረከት ምድር ለመግባት ነበር። ከላይ ባነበብነው የጳውሎስ መልእክትም ሆነ ከአጠቃላዩ የእሥራኤላውያን ታሪክ እንደምናነበው ግን ከግብጽ ክወጡት መካከል ኢያሱና ካሌብ ብቻ ድል በመንሳት የተሰጣቸውን ተስፋ ሲወርሱ በብዙ ሺዎች የሚቆጠረው ሕዝብ የምድረ በዳውን ፈተና አላለፈም። ክፉ ነገር ተመኙ፣ ጣዖትን አመለኩ፣ ሴሰኑ፣ ጌታን ተፈታተኑ፣ አንጎራጎሩ ወይም አጉረመረሙ…. ስለዚህም የተሰጣቸውን ተስፋ ሳይወርሱ በምድረ በዳ ወድቀው ቀሩ፡፡ ይህም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን እኛን ሊገስጸን ተጻፈ።
ጌታ ኢየሱስ ከርሰቶሰ ከኣባቱ ከይሖዋ በተቀበለውና መልአኩን ልኮ ለዮሓንስ በገለጠለት በራዕይ መጽሓፍ ውስጥ ለሰባቱ አብያተ ክርሰቲያናት የላከውን ደብዳቤ ስናነብ፣ በእያንዳንዱ ደብዳቤ መዝጊያ ላይ፣ “መንፈስ ለኣብያተ ከርሰቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፣ ድል ለነሳው….” የሚል የከበረ ተስፋ የያዘ ቃል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ እስቲ በሰምርኔስ ወዳለው የቤተ ክርስቲያን መልአክ በተጻፈው መልእክት መዝጊያ ላይ ድል ለሚነሱት የተገባላቸውን ተስፋ እንመልከት።
“መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል የነሳው በሁለተኛው ሞት አይጎዳም።”
ሁለተኛው ሞት ምንድነው???
“ድል የሚነሳ ይህን ይወርሳል፣ አምላክም እሆነዋለሁ፣ እርሱም ልጅ ይሆነኛል። ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ፣ የርኩሳንም የነፍሰ ገዳዮችም (በቅዱሱና በጻድቁ አምላክ ሚዛን፡ ነፍሰ ገዳዮቹ ቢን ላደንና ሒትለር ብቻ ሳይሆኑ ወንድማቸውን የሚጠሉቱም ጭምር ሁሉ ናችው) የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም፣ ጣዖትንም የሚያመልኩ የሓሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፣ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው።” ራዕይ 21፡7- 8
ክርስቲያን ሆይ! እስራኤላውያኑ በግብጽ ምድር ላይ መጥቶ ከነበረው የሞት መቅሰፍት በበጉ ደም ተሸፍነው ወይም ፋሲካ ሆኖላቸው እንዳመለጡ፣ ነገር ግን የአምላካቸው ግብና ዓላማ የምድረ በዳውን ፈተና አልፈውና ሰባቱን የአሕዛብ ነገሥታት በጦርነት ድል ነስተው ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር እንዲወርሱ እንደነበር፣ ለአንተም ያለው ዓላማ ይኸው ነው። በእምነት መንገድህ ላይ ልዩ - ልዩ ፈተና አለ። የነዚህ ፈተናዎች ምንጩ በሥጋና በደምህ ውስጥ ያሉት “የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ስለ ገንዘብ መመካት (the pride of life) ናቸው። እነዚህን ፈተናዎች የቀደመው አባትህ በዔደን ገነት ተፈትኖት ወድቁዋል፣ እስራኤላውያኑ በምድረ በዳ ጉዞአቸው ወቀት ተፈትነውት ወድቀዋል። እነሆ የምሥራች!! የእምነትህ ጀማሪና ፈጻሚ የሆነው የህያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱሰ ክርስቶሰ እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች በሥጋ ዘመኑ ተፈተኖ በድል አልፎአቸዋል። ዛሬም በአንተው ውስጥ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆኖ በሥፍራ ሁሉ ድል በመንሳቱ ሊያዞርህና በነዚሀ ጠላቶችህ ራሰ ላይ ሊያቆምህ የታመነ ነው። ታዘዘው! የተሰጠህ የዘላለም ሕይወት ተስፋ በእምነት፣ በትዕግስት፣ በጽናትና በመታዘዝ የሚወረስ ነውና!!!!
“የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድትወርሱ መጽናት ያስፈልጋችሁዋል።” ዕብ.10፡36
No comments:
Post a Comment