by Tibebe Belay on Thursday, May 31, 2012 at 7:21am ·
ይህን ጥያቄ የተጠየቁት፣ አንዲትዋ የክርስቶስ አካል - ቤተክርሰቲያን ጠላት በዘራው ክፉ የመለያየት ዘር፣ ሰዎችም ራሳቸው በፈጠሩዋቸው የተለያዩ እንግዳ ትምሕርቶች ሰበብ ወደተለያዩ ሐይማኖታዊ ቡድኖች ከመከፋፈልዋ የተነሳ ሕዝቅኤል በሸለቆው ውስጥ እንዳያቸው የደረቁ አጥንቶች በየስፍራው ተበታትና እና ሕይወት አጥታ ባለችበት በዚህ ዘመን ያሉት እርሰዎ ቢሆኑ ምን ብለው ይመልሳሉ???
በግምት ከአሥራ አምስት አመታት በፊት፣ የሚያራምዱት ሐይማኖት ለምድራችን መፍትሔ ያመጣ ዘንድ እግዚአብሔር ለዘመኑ የወሰነውና የሰጠው ሐይማኖት እንደሆነ ከሚሰብኩ ወገኖች ጋር የመነጋገር ዕድል አግኝቼ ነበር። ዋናው ስብከታቸው “ፍቅርና አንድነት” ነው። “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” የሚለውን የክርስቶስ ትምሕርት ጠቀሱልኝና፡- “ይሄ ምልክት በዚህ ዘመን ባሉ ክርሰቲያኖች ዘንድ ይታያልን?? ዛሬ ‘ክርስትና’ በሚለው ስም የሚታወቁ ቢያንስ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሐይማኖቶች አሉ። በተለያዩ ጊዜያት በሐይማኖት ሰበብ ሌሎችን መግደላቸውን፣ እርስ በእርስም መገዳደላቸውን እና በፍቅር ተስማምተው አለመኖራቸውን ትተን፣ አንዳቸው ካንዳቸው ጋር የሚግባቡበት አስተምህሮ አላቸው??....” እያሉ በጥያቄ ያጣድፉኝ ጀመር። ከዚህም የተነሳ ‘ክርስትና’ ‘የዓለም ብርሐን’ ሊሆን ቀርቶ ራሱም በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደሚገኝ ሰበኩኝ። ጨምረውም አንድ ምሳሌ ነገሩኝ፡-
“አንድ ሰው፣ አንድ ብርጭቆ በእጁ ይዞ ነበር። ይህም ሰው የያዘውን ብርጭቆ ከእጁ ቢለቀው ከወለሉ ላይ ወደቀና አንዱ ብርጭቆ ወደ ብዙ ስብርባሪነት ተለወጠ። ክርስትናም እንዲሁ ነው። ከእግዚአብሔር እጅ ወድቆ ወደብዙ ስብርባሪነት ተለውጦአል።” ሰዎቹ በድል አድራጊነት መንፈስ ስብከታቸውን ቀጠሉ። “እስቲ አንድ ‘ሎጂክ’ እንጠይቅህ፣ እነዚያ የብርጭቆ ስብርባሪዎች ተመልሰው ውሀ ሊይዝ የሚችል አንድ ብርጭቆ ሊሆኑ ይችላሉን??”
በዚህ ቅጽበት ነው ሕዝቅኤልን የተበታተኑና የደረቁ አጥንቶች ወደሞሉበት ሸለቆ የወሰደው የእግዚአብሔር መንፈስ እኔንም በእጄ የያዝኩትን መጽሐፍ እንድከፍት ያነሳሳኝ። እኔም በተራዬ ቀጠልኩ፡-
“ልክ ናችሁ ወንድሞቼ፣ በ’ሎጂክ’ የብርጭቆው ስብርባሪዎች ተመልሰው ውሀ ሊይዝ የሚችል አንድ ብርጭቆ ላይሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ግን እስቲ በእጄ በያዝኩት መጽሐፍ ቅዱሰ ውስጥ እግዚአብሔር ነቢዩ ሕዝቅኤልን የጠየቀውን አንድ ተመሳሳይ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡- በሸለቆ ውስጥ ወዲያና ወዲህ የተበታተኑና የደረቁ አጥንቶች እንደገና ተመልሰው በሕይወት ሊኖሩ ይችላሉን?” የሰዎቹን መልስ ትተን የሕዝቅኤል መልስ ግን፡- “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ታውቃለህ!!” የሚል ነበር። በ'ሎጂክ' ለሚያምን ሰው የደረቁ አጥንቶች ተመልሰው በሕይወት አይኖሩም። ለዓለም ሁሉ ብርሐን እንድትሆን እግዚአብሔር በምድር ላይ ያስቀመጣት አንዲት አካል - ቤተ ክርስቲያንም ወደ ተለያዩ ሐይማኖታዊ ቡድኖች ተለውጣና እዚህና እዚያ ተበታትና ስትታይ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለችውንና፣ የሕይወት ምንጭ አድርጎ ለዓለሙ ሁሉ የሰጠውን አንድያ ልጁን ክርስቶስን ለሌሎች ልታካፍል ቀርቶ፣ ለራስዋም ይህን የሕይወት ራሰ ገፍታ ሕይወት የሌላት ደረቅ አጥንት ሆናለች። ነገር ግን እግዚአብሔር ዘመን አመጣ!! በራሳቸው የማመዛዘን ችሎታ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ቃልና መንፈስ ተመርተው በደረቁ አጥንቶች ላይ ትንቢት የሚናገሩ ሕዝቅኤሎችን በስፍራ ሁሉ እያስነሳ ነው። እግዚአብሔርም ሕዝቅኤልን እንዲህ አለው፡- “በነዚህ የደረቁ አጥንቶች ላይ ትነቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፡- እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ!! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፣ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤….” ሕዝቅኤል እግዚአብሔር እንደተናገረው በነዚያ የደረቁ አጥንቶች ላይ ትንቢት ሲናገር፣ በመጀመሪያ የሆነው ነገር ድምጽና መናወጥ ነበር። ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ በክርስቲያኖች መካከል ያለው ድምጽና መናወጥ የእግዚአብሔር ቃልና መንፈስ የፈጠረው ነው። ለአንዳንዶች በዚህ ግሩፕ ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ግራ ይገባቸዋል። እንዲያውም “የክርስቲያኖች ሕብረትና አንድነት” የሚለው ስም እንደማይገባውም ይናገራሉ። ምክንያቱም የሚታየው ነገር አንድነት ሳይሆን፣ በቀድሞው ዘመን በሰናዖር ምድር እንደሆነው አይነት የቁዋንቁዋ መደበላለቅና ትርምስ ነው። ይህ ትርምስና መናወጥ የተፈጠረው በእግዚአብሔር ቃልና መንፈስ መሆኑን የተረዱት ግን ጥቂቶች ናቸው። እግዚአብሔር ዛሬ በቃሉ የብዙዎችን አሮጌ ሰማያት (ሐይማኖት የፈጠረውን አሮጌ አስተሳሰብና አመለካከት) እያናወጠ ነው። በዚህ ግሩፕ ውስጥ የምንሰማውም ድምጽ ይሄ መናወጥ የፈጠረው ነው። ነውጡ በጠላት የተዘራውንም ክፉ የመለያት ዘር ከሥሩ ይነቅላል። ከእግዚአብሔር ያልሆነውንና ሰዎች ከሕያው ቃሉ ውጪ በራሳቸው የፈጠሩአቸውን እንግዳ ትምሕርቶች፣ በእነዚህም ትምሕርቶች የተገነባውን አሮጌ አስተሳሰብና አመለካከት፣ ይሄ አስተሳሰብና አመለካከት የሰራውንም ቅጥር ያፈርሳል።
ሕዝቅኤል በተናገረው ትንቢት አማካኝነት ከተፈጠረው ድምጽና መናወጥ በህዋላ የሆነው ነገር የሚያስደንቅ ነው። “አጥንቶችም አጥንት ከአጥንት ጋር ተቀራረቡ።” (የሚቀጥል)
No comments:
Post a Comment