Thursday, June 28, 2012

"ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ..." ክፍል 3.

by Tibebe Belay on Thursday, March 29, 2012 at 6:11am ·

"ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና የሰማነውን: በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም: እጆቻችን የዳሰሱትን እናወራለን:: ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን: ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለም ሕይወት እናወራላችኋለን: እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወአላችኋለን:: ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው:: ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን::" (1ዮሃ.1:1-5)

በእርሱ በነበረው የእውነት መንፈስ, ሓዋርያው ዮሃንስ በወንጌሉም ሆነ በመልዕክቶቹ ውስጥ ትኩረት ሰጥቶ ይጽፍ የነበረው, በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለነበረውና እግዚአብሔርም ለእኛ ስላዘጋጀው, ኋላም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ስለገለጠውና በእኛም ይገለጥ ዘንድ ስለወደደው ሕይወት ነው። እኛም በዚህ መልዕክታችን ውስጥ ትኩረት ሰጥተን እያየን ያለነው, እንኖረውና እንተነፍሰው ዘንድ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት የወሰነልን ሕይወት ክርስቶስ መሆኑን ነው። በእርግጥ ዮሃንስ በመልዕክቱ ላይ ሲናገር እንደምናገኘው በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለነበረው ስለዚህ ዘላለማዊ ሃሳብ ለመረዳት በመንፈሳዊ አዕምሮ እያደጉና እየየበለጸጉ ወደመንፈሳዊ አባትነት ደረጃ ማደግን ይጠይቃል:: በመጀመሪያ የነበረውን ሊረዱ ብቃትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኙት "አባቶች" ናቸውና:: (1ዮሃ.2:14)

በመጽሓፍ ቅዱሳችን ውስጥ በግልጽ ተጽፎ እንደምናገኘው, የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ሃሳብ ሰውን በመልኩ እንደምሳሌው መፍጠር ነው:: በእርግጥ በዘፍጥረት መጽሃፍ በምዕ.1:26-28 ላይ ያለውን ቃል ስናነብ, ወይም ደግሞ እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ሰው ከምድር አፈር አበጅቶ በዔደን ገነት እንዳኖረው የሚናገረውን የመጽሃፉን ሁለተኛ ምዕራፍ ስንመለከት, ይሄ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ሃሳብ ማለትም ሰውን በመልኩ እንደምሳሌው መፍጠሩ ያለቀና የተጠናቀቀ ጉዳይ እንደሆነ እናስባለን:: እንዲያውም ብዙዎቻችን በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረው ሰው ያ ከምድር አፈር የተበጀው ሰው እንደሆነም እናምናለን:: ነገር ግን መንፈሳዊ ዓይኖቻችን ተከፍተው ወይም ደግሞ እጅግ የጠለቀውን የመለኮት ሃሳብ በመልዕክቶቻቸው እየጻፉ ለእኛ እንዳስተላለፉልን ሓዋርያት በእግዚአብሔር ጥበብና ማስተዋል የበለጸገ መንፈሳዊ አዕምሮ ቢሆንልን; "በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው" - ዓለም ሳይፈጠር - ከዘላለም ዘመናት በፊት እግዚአብሔር ለክብራችን የወሰነውን የከበረ ሕይወት ክርስቶስ መሆኑን መመልከት እንችል ነበር::

"እንዲሁ ደግሞ:- ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል: ኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ:: ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም:: የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው: ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው:: መሬታዊው እንደሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው: ሰማያዊው እንደሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው:: የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን::" (1ቆሮ.15:45-49)

በእግዚአብሔር ዕቅድና ሃሳብ መሰረት ሰው አስቀድሞ ይኖረውና ያውቀው ዘንድ የተወሰነው ፍጥረታዊውንና ምድራዊውን ሕይወት ነው:: እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ሰው ከምድር አፈር አበጅቶ በዔደን ገነት ሲያኖረው የዚህ ሰው ኑሮ የጀመረው ፍጥረታዊና ምድራዊ ከሆነው ሕይወት ነው:: ምንም እንኳን የዚህ ሰው ሕይወት ገና ሰማያዊና መንፈሳዊ ባይሆንም ነገር ግን ወደዚህ የላቀ ሕይወት የሚወስደው መንገድ ለእርሱ ዝግ አልነበረም:: እግዚአብሔር ይህንን ሰው በሁለት ምርጫዎች መካከል ማለትም በሕይወትና በሞት መካከል ሲያስቀምጠውም ለሕይወት በሚሆን መታዘዝ እግዚአብሔር ወደወሰነለት የከበረ መልክ እንዲደርስ ነበር:: ነገር ግን ያ ሰው በራሱ ምርጫና አለመታዘዝ ከዚህ የከበረ ሕይወትና መልክ እንደወደቀ እናውቃለን:: በዚህም ምክንያት እኛ ሁላችን ከዚህ ሰው የተካፈልነው ፍጥረታዊውንና ምድራዊውን ሕይወት ብቻ ሳይሆን ሞት ያለበትን ስጋዊውንና በኃጢአት የተበላሸውን የወደቀ ሕይወት ነው::

የዛሬ 2000 ዓመት አካባቢ በሥጋ የመጣው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ, ከላይ ባነበብነው የጳውሎስ መልዕክት መሰረት በሁለት የተለያዩ ስሞች ተገልጦ እናገኘዋለን:: "ኋለኛው አዳም - The last Adam" እና "ሁለተኛው ሰው - The second Man":: የመጀመሪያው ሞቱን የሚያመለክት ሲሆን በመስቀል ላይ ሞቱ በኃጢአት ምክንያት የተበላሸውንና የወደቀውን ሰው አሮጌ ሕይወት ከመንገድ ጠርቆ በማስወገዱ ለዚያ አሮጌ ትውልድ እርሱ የመጨረሻው ሰው ሆኖአል:: በመሆኑም በእግዚአብሔር አቆጣጠር ያ የወደቀው ሰው ዛሬ የለም:: "አሮጌው ነገር አልፎአል!!!" በትንሳኤው ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ በመጀመሪያ የነበረውና እግዚአብሔር ለክብራችን የወሰነው የከበረ ሕይወት - ክርስቶስ - ሕይወትና አለመጥፋት - የዘላለም ሕይወት ወደ ብርሃን ወጥቶአል:: በእርግጥ ሁለተኛው ሰው ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው, ሰማያዊ ነው, መንፈሳዊ ነው, የእግዚአብሔር መልክ ነው... ሕይወታችንም እርሱ ነው - ክርስቶስ!!!

No comments:

Post a Comment