by Tibebe Belay ·
በሥጋው ወራት ይፈጽመው ዘንድ ከአባቱ የተቀበለውን ሥራ ፈጽሞ በምድር ያከበረው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ዛሬም በሰማያት በግርማው ቀኝ የተቀመጠ የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኩዋን አገልጋይ ነው። እግዚአብሔር በክርስቶስ ይፈጽመው ዘንድ የጀመረው የከበረ ሥራ የዛሬ 2000 ዓመት አካባቢ ልጁን ወደዚህ ምድር በላከበት ወቅት የተጠናቀቀ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱሳችንን ጠጋ ብለን ስናነብ፤ እግዚአብሔር ዓለማትን ሁሉ የፈጠረው በክርስቶስና ለክርስቶስ (በልጁና ለልጁ) መሆኑን፣(ቆላ.1፡15-16 ዕብ.1፡2) በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ከእርሱ ተለይቶ የነበረውን ፍጥረቱን ሁሉ ወደራሱ የመለሰውም ቤዛውን በከፈለው አንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ፣ እንዲሁም ደግሞ “በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል”(ኤፌ.1፡10) መሆኑን እንረዳለን። ታድያ ከዚህ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ አንጻር፣ እርሱ በክርስቶስ ሊያደርገው ያሰበው ሥራ ሁሉ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ በሥጋ ሆኖ በተመላለሰባቸው 33 ½ ዓመታት ውስጥ ተጠቃሎ ተፈጽሞአል ማለት ይቻላል??
ነቢዩ ዳዊት በመዝ.(40) ላይ ስለ ክርስቶስ በተናገረው ትንቢት መሠረት፣ ክርስቶስ የዛሬ 2000 ዓመት አካባቢ በተዘጋጀለት ሥጋ ወደዚህ ምድር ሲመጣ፣ “እነሆ አምላክ ሆይ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ” ማለቱ ተጽፎአል። ታድያ ክርስቶስ በሥጋ በመምጣቱ የፈጸመው የእግዚአብሔር ፈቃድ ምንድነው?? ይህን ጥያቄ እጅግ ሰፊ በሆኑ የተለያዩ መልሶች መመለስ ቢቻልም፣ ዋናው ግን ራሱን ስለኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቅበትንና ወደ እግዚአብሔር የሚመለስበትን ቤዛ ለመክፈልነው። (ዕብ.10፡5-10) ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣበትን የእግዚአብሔር ፈቃድና ዓላማ ለማጠናቀቅ በተቃረበበት ጊዜ እንዲህ አለ፡- “እኔ ላደርገው ዘንድ የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርኩህ፤ አህንም አባት ሆይ ዐለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ።” (ዮሃ.17፡4-5)
ታድያ ክርስቶስ በምድር ይሠራው ዘንድ ከአብ የተቀበለውን ሥራ ከፈጸመ በሁዋላ ነገር ሁሉ አበቃ ማለት ነው?? አይደለም። የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ሁሉ ሞትን ከቀመሰ በሁዋላ እግዚአብሔር ከሙታን ሲያስነሳው፤ “ጠላቶችህን ሁሉ ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” የሚል ተስፋ ሰጥቶት እንደሆነ በመጽሐፋችን በግልጽ ተጽፎ እናገኛለን። አሁን ሁሉ ከእግሩ በታች እንደተገዛለት ገና አናይም። ለዚህም ነው ጌታ ኢየሱስ ክርሰቶስ ዛሬም በግርማው ቀኝ በተቀመጠበት የሊቀ ክህነት አገልግሎቱ በሥራ ላይ ነው የምንለው። በተደጋጋሚ እንዳልነው፣ ክርስቶስ በምድር - በሥጋው ወራት የሠራው ሥራ ስለኃጢአት ሥርየት የሚሆነውን ፍጹም መሥዋዕት አንድ ጊዜ ማቅረብ ነው። ይሄ ዛሬ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ ያለው ሰማያዊ ሥራውና አገልግሎቱ ግን፣ በዚህ አንድ ጊዜ ባቀረበው ፍጹም መሥዋዕት በኩል ወደእግዚአብሔር ለሚቀርቡት ሕይወትን ማካፈልና መስጠት ነው። ከእግዚአብሔር ጋር መታረቃችን በሞቱ፣ መዳናችን ደግሞ በሕይወቱ በማያልፍ ሕይወት ኃይል በመልከ ጼዴቅ ሹመት የዘላለም ሊቀ ካህን ተብሎ በተጠራበት ሰማያዊ አገልግሎቱ የሆነበትም ምክንያት ይኸው ነው።
“ስለእነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና፤ ስለዚህ በእርሱ ወደእግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።” (ዕብ.7:25)
“ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፣ ይልቁንም ከታረቅን በህዋላ በሕይወቱ እንድናለን።" (ሮሜ.5፡10)
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው ኃይል የሞትን መውጊያ ሰብሮ በሰማያት በግርማው ቀኝ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ እጁን አጣምሮ የመላዕክትን ዝማሬ እየሰማ አይደለም። ይልቁንም በሥጋው ወራት ቤዛውን ከፍሎ ጠላቶች የነበርነውን እኛን ከእግዚአብሔር ጋር በማስታረቅ የጀመረውን የመዋጀት፣ የመቀደስና የማንጻት ሥራ እየሰራ ነው። ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን - የኣካሉ ራስ ነው ስንል፣ አካሉን የሚገዛና የሚያስተዳድር ነው ማለታችን ብቻ ሳይሆን፤ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን በፍጥረቱ መካከል የምታወርድ - የምትገልጥ መቅደስና ድንኩዋን እንድትሆን፤ በሕይወቱ ሙላት፣ በቅድስናው ውበት፣ በጽድቁ ልክና መጠን… የሚያንጻትና የሚያዘጋጃትም እርሱ ራሱ ነው ማለታችን ነው። በሞቱ ከእግዚአብሔር ጋር ያስታረቀንን እኛን በሕይወቱ ያድነናል - ቅዱሳንና ፍጹማን አድርጎም በአባቱ ፊት ያቀርበናል። ይሄ ደግሞ የማንም ልመናና ምልጃ የሚፈጽመው ሳይሆን፣ ክርስቶስ ራሱ በሰማያት (በመንፈሳዊ ክብሩ) ባለው የሊቀ ክህነት አገልግሎቱ ብቻ የሚከናወን ነው።
“እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁ ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፣ (to present you holy and without blemish and UNREPROVEABLE before him) በፊት የተለያችሁን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ፣” (ቆላ.1።21-22)
በዚህም የከበረ ሰማያዊ አገልግሎቱ በምድር ያከበረውን አባቱን ዛሬም በሚበልጥ ክብርና ኃይል በመንፈሳዊ አካሉ - በቤተ ክርስቲያን - በወንድሞቹ መካከል ሆኖ እያከበረው ነው። “የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና፤ ስለዚህም ምክንያት፡- ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ…” ያለው ክቶ ማነው??? (ዕብ.2፡13)
No comments:
Post a Comment