by Tibebe Belay on Thursday, May 10, 2012 at 10:30am ·
ለኣራት መቶ ዓመታት ያህል በግብጽ ምድር በአስከፊ ባርነት ውስጥ ኖረው የነበሩት እሥራኤላውያን፣ በኃይለኛው የእሥራኤል አምላክ ክንድ ከዚህ ባርነት ተፈትተው ይግዋዙበት በነበረበት ምድረ በዳ ውስጥ በአምላካቸውና ከፊት ሆኖ ይመራቸው በነበረው ነቢይ ላይ ከተናገሩት ክፉ ቃል የተነሳ የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ። እየተነደፉ ይሞቱም ዘንድ እግዚአብሔር እባቦችን በሕዝቡ መካከል ሰደደ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ሞቱ። ነገር ግን የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ስለ ሕዝቡ ወደእግዚአብሔር ጸለየ። “እግዚአብሔርም ሙሴን፡- እባብን ሠርተህ በኣላማ ላይ ስቀል፤ የተነደፈውም ሁሉ ሲያዩት በሕይወት ይኖራል አለው። ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፣ እባብም የነደፈችው ሰው የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ።” (ዘኁ. 21፡8-9)
ንጉሱ ዳዊት፡- “እነሆ በዓመፃ ተፀነስሁ፣ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ።” ብሎ መናገሩ፣ ከአዳም የተገኘ የሰው ዘር በሙሉ - ነጩ ጥቁሩ፣ ዓረቡ አበሻው፣ እስላሙ ቡዲስቱ፣ 'ክርሰቲያኑ' 'አረመኔው'፣ ሳይነቲስቱ 'ጎዳና ተዳዳሪው'፣ ፕሬዝዳነቱ የቀን ባለሙያው፣... ወደዚህ ዓለም የሚወለድበትን የኃጢአትና የዓመፅ ሕግ ወይም ዘር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ይህ የኃጢአትና የዓመፅ ዘር ደግሞ በዔደን ገነት ሴቲቱ የተባበረችውና ከእርስዋም ጋር ጋብቻ የፈጠረው እባብ ነው። እርሱ የኃጢአትና የሞት ምንጭና ምክንያት ነው። እርሱ የእግዚአብሔር => የሕይወት - የጽድቅ - የቅድስና… ጠላት ነው። “የኃጢእት ደመዎዝ ሞት ነው === ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነው ==== ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነው ==== በሀሳባችሁ ጠላቶች ነበራችሁ === እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና===
እግዚአብሔር በሰው ሁሉ ላይ የሆነውን ይህን የኃጢአትና የዓመፅ ዘር ከምንጩ ለማድረቅ የእባቡን ራስ የቀጠቀጠው፣ ጠላትነትን ያስወገደውና ሞትን የሻረው… በውጤቱም ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሐን በማውጣት የጽድቅንና የቅድስናን ምንጭ የከፈተው…. ሙሴ፣ እሥራኤላውያን እየተነደፉ የሞቱበትን እባብ በምድረ በዳ በዓላማ ላይ ከፍ አድርጎ እንደሰቀለ፤ የዛሬ ሁለት ሺኅ ዓመት አካባቢ “የምድር እምብርት” በተባለችው በቀራንዮ ከፍታ ላይ፣ አንድያ ልጁ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ” በመስቀል መከራ እንዲሞት በፈቀደ ጊዜ ነው። እግዚአብሔር በመካከላቸው በሰደደው እባብ የተነደፉ ሁሉ ሙሴ በዓላማ ላይ ከፍ አድርጎ የሰቀለውን የናስ እባብ ሲመለከቱ በመካከላቸው ከገባው የሞት መቅሰፍት እያመለጡ በሕይወት እንደኖሩ፣ ዛሬም የኃጢአትና የሞት ምንጭ በሆነው “የቀደመው እባብ” የተነደፉ ሁሉ፣ በቀራንዮ መስቀል ላይ ከፍ ብሎ የተሰቀለውን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያዩ - ሲያምኑ በሕይወት ይኖራሉ።
=>“ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል።” (ዮሐ.3፡14-15)
=>“ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቆአልና።” (ሮሜ.6፡6)
No comments:
Post a Comment