by Tibebe Belay on Wednesday, June 13, 2012 at 6:16am ·
ሰው ሰራሽዋ ሐይማኖት፤ ሰዎች በአንድ እግራቸው በአግባቡ ባልተነገረ ወንጌል ላይ፣ በሌላ እግራቸው ደግሞ በአፈ-ታሪኮች ላይ እንዲቆሙና ዘመናቸውን በግራ መጋባት እንዲጨርሱ ስታደርግ፤ ከሐዋርያቱ የተቀበልናትና ክርስቶስ ብቻውን የእምነታችንንና የሕይወታችን መሠረት እንደሆነ በሚነግረን ወንጌል ላይ የተመሠረተችው እምነታችን ግን፣ ሰዎች በሁለቱም እግራቸው በጸናው ዐለት በክርስቶስ ላይ ብቻ ጸንተው እንዲቆሙ ታደርጋቸዋለች።
"ወንድሞች ሆይ!! የሰበክሁላችሁን፣ ደግሞም የተቀበላችሁትን፣ በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን፣ በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችሁዋለሁ።... እኔ ደግሞ የተቀበልኩትን ወንጌል ከሁሉ በፊት ሰጠሁዋችሁ፣ እንዲህ ብዬ፡- መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለኃጢአታችን ሞተ፣ ተቀበረም፣ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሳ..." (1ቆሮ.15:1-4)
በሐይማኖት አጥር ውሰጥ በግራ መጋባት ተዘግቶባቸው የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይህን ወንጌል በቃላቸው ያውቁታል። ነገር ግን ከራሳቸው ሕይወት ጋር ያለው ቁርኝት ምን እንደሆን በአግባቡ ስላልተነገራቸው በሁለት እግሮቻቸው አልቆሙበትም፣ ደግሞም አልዳኑበትም። ክርስቶስ ስለኃጢአታቸው ሞቶ፣ ስለበደላቸውም የከበረች ሕይወቱን ከፍሎ እያለ፤ ወደሰማዩ አባታቸው ፊት በድፍረት በመቅረብ የኃጢአት ይቅርታና ምሕረትን፣ ደግሞም እንዲሁ - በጸጋ የተሰጣቸውን የዘላለም ሕይወት ለመቀበል ይሸማቀቃሉ። ስለዚህም መምሕራኖቻቸው ሌላ ዘዴ፣ ሌላ መንገድ፣ሌላ አማራጭ ...በሌላ ሦስተኛ ወገን በኩል ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንደሚቻል ይነግሩዋቸዋል። ስለዚህም ከእምነት መንገድ ስተዋል። በክርስቶስ ወንጌል ከተገለጠው የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ሀሳብም በብዙ ሺህ ማይልስ ርቀው ቆመዋል።
በሐይማኖት አጥር ውስጥ በግራ መጋባት ተዘግቶባቸው የሚኖሩ ወገኖች ሁሉ፣ክርስቶስ ስለኃጢአታቸው እንደሞተ፣ እንደተቀበረ፣ በሦስተኛውም ቀን እንደተነሣ የሚናገረውን ወንጌል በቃላቸው ያንበለብሉታል እንጂ አልቆሙበትም፣ ደግሞም አልዳኑበትም። እግዚአብሔር ከሁሉ በሚበልጠው የኃይሉ ታላቅነት ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሳው፣ እነርሱም አብረው እንደተነሡ አያውቁም። ስለዚህም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሐት እየተሸማቀቁ ይኖራሉ። መምሕራኖቻቸው ስለትንሣኤ የሰበኩዋቸው "ሌላ ወንጌል" ነው። ሐዋርያቱ የሰበኩት የከበረ ወንጌል ግን እንዲህ ይላል፡-
"እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ፣ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሳ በበደላችን ሙታን እንክዋን በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ሰጠን፤ በጸጋ ድናችሁዋልና፣ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።" (ኤፌ.2፡4-7)
በሐይማኖት መቃብር ውስጥ የተዘጋባቸው ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምጽ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል። እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ!!!!
No comments:
Post a Comment