by Tibebe Belay ·
የክርስቶስ የሊቀ ክህነት አገልግሎቱ የጀመረው ለዓለም ሁሉ የኃጢአት ማስተሰሪያና ቤዛ አድርጎ ራሱን በመስቀል ላይ ባቀረበ ጊዜ ቢሆንም፣ በመልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ የተጠራው ግን ሁሉን ፈጽሞና ከሞት ተነስቶ በእግዚአብሔር ቀኝ ከተቀመጠ በሁዋላ ነው። ለዚህም ነው “በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህን አለን፣ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛቱ ድንኩዋን አገልጋይ ነው…” በማለት የዕብራውያን ጸሐፊ የነገረን።
ክርስቶስ በዙፋን ላይ የተቀመጠ ሊቀ ካህን የሆነበትን ምክንያት መረዳቱ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። እርሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “ሊቀ ካሕናት” ተብሎ የተጠራበት ሥርዓት የአሮን ሳይሆን የመልከ ጼዴቅ መሆኑ ይህን የከበረ እውነት ለመረዳት የሚያስችለንን አንዳች ምሥጢር ይዞአል። በብለይ ኪዳኑ ሥርዓትና አገልግሎት የክህነቱ ሥልጣን የሌዊን ዘር ብቻ ተከትሎ የሚሄድ ሲሆን፣ ነገሥታት የሚሾሙት ደግሞ ከይሁዳ ነገድ ብቻ ነበር። በዚህ በአዲሱ ኪዳን መንፈሳዊ ሥርአት ግን አንዱ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለቱንም ማለትም ንጉሥነቱንም ሆነ ክህነቱን በአንድነት የጠቀለለበት ምክንያት፣ የክህነት ሹመቱ በመልከ ጼዴቅ ሥርዓት በመሆኑ ነው። በእግዚአብሔር ልጅ የተመሰለው መልከ ጼዴቅ ደግሞ “የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን” ነው። (ዕብ.7፡1-3)
ስለዚህ እግዚአብሔር “አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ” ብሎ የማለለት አንድያ ልጁ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዙፋን ላይ ሲቀመጥ የነገሥታት ንጉስ ወይም ፈራጅ ሆኖ ብቻ ሳይሆን፣ ስለሕዝቡ ድካም የሚማልድ ሊቀ ካህንም ሆኖ ነው ማለት ነው። ይህ የከበረ እውነት ከብዙ ወንድሞቻችን አእምሮ በመሰወሩ ምክንያት ነው “ዛሬ ክርስቶስ የሚፈርድ ንጉሥ እንጂ የሚማልድ ካህን አይደለም” ወደሚል ስሕተት ውስጥ የገቡት። የገዛ ስህተታቸውን ለማጽደቅ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ በግልጽ የተጻፉትን ቃላት እስከ መለወጥ የሚደርስ ሌላ ትልቅ ስህተት መፈጸማቸው ግን ወደ ፍርድ የሚመራ ድፍረት በመሆኑ “ከተጻፈው አትለፍ” የሚለው ሐዋርያዊ ምክር ከዚህ ፍርድ እንዲያድናቸው እንጸልያለን።
በራዕይ መጽሐፍ ምዕራፍ አምስት ላይ እንደምናነበው፣ መጽሐፉን የዘረጋውና ማሕተሙን የፈታው ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፤ በዙፋኑ፣ በአራቱ እንሰሶችና በሽማግሌዎቹ መካከል እንደታረደ በግ ቆሞ መታየቱ የሚገርም ነው። አንበሳው በግ ነው፤ በጉም አንበሳ ነው። ንጉሡ ካህን ነው፣ ካህኑም ንጉሥ ነው። የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የነገሥታት ንጉስና የካህናት አለቃ ነው። እነዚህ ሁለት መጠሪያዎች ግን የተሰጡት ያለ አገልግሎት አይደለም። በአብ ቀኝ የተቀመጠው የነገሥታት ንጉሥ የአካሉ - የቤተ ክርስቲያን ራሰ በመሆኑ አካሉን በመንፈሱ እየገዛና እያስተዳደረ መሆኑ የማያጠራጥር እውነት እንደሆነ ሁሉ፤ ይህቺኑ አካል ነውርና ነቀፋ የሌላት ቅዱስ አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ለማቅረብ እየተጋ መሆኑም ልንረዳው የተገባ እውነት ነው። በሰማያት በግርማው ቀኝ የተቀመጠውና በመልከ ጼዴቅ ሹመት የዘላለም ሊቀ ካህን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “የእውነተኛይቱ ድንኩዋን አገልጋይ” የሆነበትም ምሥጢር ይኸው ነው። ሆኖም አገልግሎቱን የሚፈጽምባት ማለትም በንግሥናው የሚገዛትና በክህነቱ የሚያነጻት ይቺ ድንኩዋን ከብዙዎች ዓይን ተሰውራለች።
“ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኩዋን የዘላለም ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፣ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን??” (ዕብ.9፡11-14)
ክርስቶስ የገዛ ደሙን ይዞ የገባው፣ ደሙ የፈሰሰበት የማንጻትና የመቀደስ ዓላማ ወደሚፈጸምበት ሥፍራ ነው። በዚሁ በዕብራውያን ምዕራፍ ዘጠኝ ከቁጥር አሥራ ዘጠኝ ጀምሮ እንደምናነበው፣ በቀደመው ኪዳን ሙሴ የጥጆችንና የፍየሎችን ደም የረጨው በድንኩዋኒቱና በማገልገያው ዕቃ ሁሉ ላይ ነው። በመሆኑም ድንኩዋኒቱም ሆነ የማገልገያ ዕቃዎቹ ሁሉ ከተረጩት ደም የተነሳ በመንጻታቸውና በመቀደሳቸው እግዚአብሔር ይመለክባቸውና ይከብርባቸው ዘንድ ብቁ ይሆኑ ነበር ማለት ነው። የሙሴ ድንኩዋን ምሳሌና ጥላ ሆና ያገለገለቻትና የምትበልጥ፣ የምትሻል፣ በሰው እጅ ያልተተከለችና ያልተሰራች፣ ለዚህ ፍጥረት ያልሆነች… የተባለችውም እውነተኛይቱ ድንኩዋን እግዚአብሔር ይመለክባትና ይከብርባት ዘንድ፣ ከፍየሎችና ከጥጆች ደም እጅግ በሚበልጥና በከበረ ደም መንጻት አለባት። ታድያ፣ ክርስቶስ የዘላለም ቤዛነትን አግኝቶና ነውር የሌለበትን ክቡር ደሙን ይዞ የገባው ወዴት ነው?? ይሄ ክቡር ደም የፈሰሰውስ ማንን ሊያነጻና ሊቀድስ ነው??
“ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን??”
No comments:
Post a Comment