Thursday, June 28, 2012

"ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ...!" (ክፍል 1)


እግዚአብሔር ሁሉን የሰራው በልጁና ለልጁ ነው:: ዓለማትን የፈጠረውም ሆነ በአዳም አመጽና በደል ምክንያት ከርሱ የተለየውን ፍጥረት የዋጀው ደግሞም በዘመናት መጨረሻ ሁሉን የሚጠቀልለውና ወደራሱ የሚመልሰው በልጁ ነው:: ይሄ ምሥጢር ታላቅ ነው!! ከዘላለም ዘመናት ጀምሮ ክርስቶስ - የሕያው እግዚአብሔር ልጅ በእግዚአብሔርና በፍጥረቱ መካከል ቆሞአል:: እርሱ የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነውና, የማይታየው እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ራሱን የገለጠው በእርሱ ነው:: ደግሞም ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነውና እግዚአብሔር ፍጥረቱን ሁሉ ያጋጠመውም በእርሱ ነው:: እግዚአብሔር ከእርሱ የሆነውን ሁሉ የሰጠን በክርስቶስ ነው:: እኛም ከእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ የምንቀበለው ብቻ ሳይሆን እርሱ ያለንን ሁሉ የምንሆነው በክርስቶስ ነው:: ምንም እንኳን ሓይማኖት በሃሰተኛ ምላሱ ሌላ ትርጉም ቢሰጠውም, ያኔ - ያዕቆብ በካራን ምድር, ድንጋይ ተንተርሶ በተኛበት ስፍራ ባለመው ሕልሙ እግዚአብሔር የገለጠለትም ይሄንኑ ምሥጢር ነው:: (ዘፍ.28:10-13)

"መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ: ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከርሱ የሆነ እኛም ለርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን: ነገር ሁሉ በርሱ በኩል የሆነ እኛም በርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን::" (1ቆሮ.8:5-6)

ከክርስቶስ ውጪ እግዚአብሔርንና ከእግዚአብሔር የሆነልንን ነገር መፈለግ ከንቱ ድካም ነው:: ለዚህም ነው የቀደሙት ሓዋርያት እግዚአብሔርን በአገለገሉበት የሕይወት ዘመናቸው ሁሉ "የእግዚአብሔር ምሥጢር" የተባለውን ክርስቶስን ለሰዎች ሁሉ ለመግለጥ የተጋደሉት:: ለዚህም ነው ክርስቶስን እንጂ ራሳቸውንም፣ እናቱንም፣ መላእክትንም... ያልሰበኩት:። የጽድቅና የሕይወት ጠላት የሆነው ዲያብሎስ ግን በዋና ሠራተኛው ሓይማኖት በኩል በዘመናት መካከል ዛሬም በእኛ ዘመን ብዙዎችን ከእውነትና ከሕይወት መንገድ ያወጣው ይሄን ምሥጢር - ክርስቶስን በተለያየ ዘዴና ብልሃት በመሸፈን ነው። ዛሬ የብዙዎች ቅንዓት ሓይማኖታቸውና እርሱም ቀርጾ የሰጣቸው "ቀኖና" የሆነበትም ምሥጢር በዚህ የወንጌል ጠላት ከመጭበርበራቸው የተነሳ ነው።

እግዚአብሔር ለእኛ የወሰነውና ክብር የሞላበት ሕይወት ያለው በክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ ራሱ ነው። ወንድሞቼ በዮሃንስ ወንጌል ምዕራፍ 1:1-5 ላይ የሰፈረውን ጥልቅ ትምሕርት የሚጠቅሱት ሓይማኖት ቀርጾ ስለሰጣቸው "የሥላሴ ምስጢር" ለመሟገት እንጂ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ለነርሱ የወሰነላቸውንና የሰጣቸውን የከበረ ሕይወት - ክርስቶስን ሊያዩበት አይደለም:: "በርሱ ሕይወት ነበረች ሕይወትም የሰው ብርሓን ነበረች" የሰው ልጅ ክርስቶስን ማየት ካልሆነለት በቀር በጨለማ ይኖራል እንጂ ወደብርሃንን አይመጣም። ክርስቶስን ካላገኘ በቀር ዕረፍትም ሆነ ሰላም፣ ሕይወትም አይሆንለትም:: "እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው:: ልጁ ያለው ሕይወት አለው: የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም::" (1ዮሃ.5:11-12)

ሕይወታችን ክርስቶስ ነው:: በክርስቶስ ያለው ሕይወት የኛ ሕይወት ነው:: ግንድና ቅርንጫፎቹን ማን ሁለት አደረጋቸው?? አካልና ራስስ ተለያይተው መኖር ይችላሉን?? "አካልም አንድ እንደሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደሆኑ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው::" (1ቆሮ.12:12) ክርስቶስም ደግሞ እንዲሁ ነው!! ክርስቶስም ደግሞ እንዲሁ ነው!! ክርስቶስ እንዴት ነው??? ክርስቶስ ብዙ ብልቶች ነገር ግን አንድ አካል ነው:: ክርስቶስንና ቤተ ክርስቲያንን - አካሉን - እኛን ማን ነው ሁለት ናቸው ብሎ የሰበከው?? "ሰው አባቱንና አናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ስጋ ይሆናሉ:: ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው!!! እኔ ግን ይህን ስለክርስቶስና ስለቤተ ክርስቲያን እላለሁ::" ኤፌ.4:31-32

ክርስቶስ የአካሉ ራስ ነው:: ራስነቱም ጌትነቱንና ገዢነቱን ብቻ ሳይሆን የሕይወት ምንጭነቱንም የሚያመለክት ነው። ምንም እንኳን ዛሬ ሓይማኖት በነሰነሰው መርዝ በቤተክርስቲያን መካከል መለያየት ሆኖ በአካሉ - በእኛ ያለው ሕይወት ሲታይ ይህን ባይመሰክርም, እግዚአብሔር ግን በእውነት በልጁ የጠራቸውን ልጆቹን በከበረው የክርስቶስ ሕይወት ከዚህ መርዝ ሊያነጻና ሊቀድስ በቅዱስ መንፈሱ እየተጋ ነው:ዓይናችን ተከፍቶ ማየት ከሆነልን, እኛ ባለንበት በዚህ ዘመን እግዚአብሔር ይህን የከበረ ሥራውን በቅዱሳኑ መካከል እየፈጸመ ነው:: "ከቤቱ መድረክ በታች" የሚወጣው የሕይወት ውኃ (ሕዝ.47፡1-12)፣ ሐይማኖት በተለያዩ እንግዳ ትምሕርቶች የበከለውንና ያረከሰውን የልጆቹን አእምሮ እየፈወሰ, ሃሳባቸውንም እየቀደሰ ነው:: ይህ ሥራው ሲፈጸም, ሕይወታችን የሆነው ክርስቶስ በቃላችንም በኑሮአችንም መገለጥና መታየት ይጀምራል:: አሜን ይሁን!!!!!
· ·  


No comments:

Post a Comment