by Tibebe Belay on Friday, June 15, 2012 at 8:45am ·
የዕብራውያን ጸሐፊ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን “የአዲስ ኪዳን መካከለኛ” ብሎታል። አዲሱ ኪዳን የዘመኑ እርዝመት ከመቼ እስከ መቼ ይሆን?? አዲሱ ኪዳን ባለበትና በጸናበት ዘመን ሁሉ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱሰ ክርስቶስ የኪዳኑ መካከለኛ ነው። ሐዋርያው ጳወሎስም “አንድ እግዚአብሔር አለና፣ በእግዚአብሔር በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፤(እዚህ ላይ ልብ በሉ!! ‘በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የነበረው መካከለኛ ደግሞ አንድ ነበር’ አላለም) እርሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።” በማለት የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኝነት የነበረና ዛሬም ያለ እንዲሁም ከእግዚአብሔር የተለየው ፍጥረት ሁሉ ወደእግዚአብሔር ተመልሶ ፍጻሜ እስከሚሆን ድረስ ወደፊትም የሚቀጥል እንደሆነ ነግሮናል። ታድያ በዚህ መልዕክቱ ላይ ጳወሎስ “ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ” በማለት ስለአንድ ያለፈ፣ ያለቀና የተጠናቀቀ ሂደት በሚጠቁም ቃል የተናገረው ስለምንድነው?? ስለመካከለኝነቱ?? በጭራሽ!!! ራሱን ለሁሉ ቤዛ አድርጎ ስለመስጠቱ ነው እንጂ!!! “…ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፣ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ፣….”
የዛሬ 2000 ዓመት አካባቢ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ በመምጣቱ የተፈጸመና የተጠናቀቀ የእግዚአብሔር ሀሳብ አለ። ይሄ ክርስቶስ ከአብ የተሰጠውና በሥጋ በመምጣቱ የፈጸመው የከበረ ሥራ ደግሞ ነፍሱን ለሰው ልጆች ሁሉ ቤዛ አድርጎ በመስጠት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን ጠላትነት በሞቱ ያስወገደበት የማስታረቅ ሥራ ነው። ይሄ የማስታረቁ ሥራ አንድ ጊዜ የተጠናቀቀና የማያዳግም ሥራ ነው። ደግሞም ይህን በሥጋ የመጣበትን ስራ ፈጽሞ በክብር በአባቱ ቀኝ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ፣ “የኁዋለኛው ጠላት” (The last enemy) የተባለው ሞት ከእግዚአብሔር ፍጥረት ሁሉ ላይ ተሽሮና እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ሆኖ ፍጻሜ እስከሚሆን ድረስ፣ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ ባለው የሊቀክህነት አገልግሎቱ የሚፈጽመውና ገና ያልተጠናቀቀ የማዳን ሥራ አለ። ይሄ እውነት ሲበራልን ነው፣ የክርስቶሰ የአዲሰ ኪዳን መካከለኝነት በሥጋ በመምጣቱና ቤዛውን በመክፈሉ ብቻ “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” የተጠናቀቀ እንዳልሆነ የምንረዳው።
“ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፣ ይልቁንም ከታረቅን በህዋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን።” (ሮሜ.5፡10-11)
ልብ በሉ!! መታረቃችን በሞቱ የተጠናቀቀና የተፈጸመ ነው፣ ክርስቶስ ኢየሱሰ ዛሬ ስለመታረቃችን አንዳች የሚያደርገው ነገር የለም፣ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ ያለው ሊቀ ካህን እንደቀደሙት ካህናት ዕለት ዕለት ስለበደልና ስለኃጢአት የሚሆን ማናቸውንም አይነት መስዋዕት አያቀርብም፣ ለመስቀል ሞት ራሱን አሳልፎ ሲሰጥ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎታል፣ እግዚአብሔርም ይህንን መስዋዕት ወዶ ተቀብሎታል፣ እንዲያውም እርሱ ራሱ በክርስቶስ ሆኖ ዐለሙን ሁሉ ከራሱ ጋር አስታርቆአል፣ ከእንግዲህ የማንንም በደል አይቆጥርም….. እኛም ዛሬ ሰዎች ሁሉ ይህን በመስቀል ላይ የተከፈለላቸውን ዋጋ እንዲያዩና፣ በእነርሱና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው ጠላትነት በክርስቶስ ሞት እንደተወገደ እንዲረዱ የተሰቀለውን ክርስቶስን እየሰበክን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ እንላለን። ስለዚህ የክርስቶስ የማስታረቅ ሥራ የተጠናቀቀ ነው ማለት ነው። ይህ ማለት ግን መካከለኝነቱ ተጠናቅዋል ማለት ነው?? አይደለም!!! “… ይልቁንም ከታረቅን በህዋላ በሕይወቱ እንድናለን!!”
መታረቃችን በሞቱ ነበር። መዳናችን ግን በሕይወቱ ነው። ለመታረቃችን መካከለኛ የነበረው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ዛሬም ለመዳናችን መካከለኛ ነው። መዳናችን በሕይወቱ - “በማያልፍ ሕይወት ኃይል” በመልከ ጸዲቅ ሹመት የዘላለም ሊቀ ካህን በሆነበት ሰማያዊ አገልግሎቱ ነው። ለዚህም ደግሞ “የእውነተኛይቱ ድንክዋን አገልጋይ” ተብሎአል። እዚህ ላይ ጨምረን ልናውቅ የሚገባው፣ ምልጃውም ከማያልፈው ሕይወቱና በግርማው ዙፋን ቀኝ ካለው ሰማያዊ አገልግሎቱ ጋር የተቆራኘ መሆኑ ነው፤ “የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሳው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፣ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።” እንዲሁም፣ “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ በእርሱ ወደእግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።” የተባልነውም በዚሁ ምክንያት ነው ። (ሮሜ.8፡34 ዕብ.7፡25)
እንግዲህ ከዚህ በላይ ሐዋርያቱ በግልጽ ባስተማሩት የክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መካከለኝነትና ምልጃ ላይ፣ የወንጌል ጠላት በተለይ በአገራችን ኢትዮጰያ የፈጠረው ውዥንብር ዓላማው፤ እንደተለመደው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን አንዱን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሰው ልብና አእምሮ በማውጣት፣ ይሄ የመካከለኝነት ስልጣንና ኃላፊነት ያልተገባቸውን ሰዎችና መላእክት በቦታው ላይ ለማስቀመጥ ነው። በዚህ ተንኮልና ሴራው ደግሞ፣ በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው ጠላትነት እንዲቀጥልና ሰዎች ከኃጢአትና ከሞት ሕግ እየዳኑ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ተካፋዮች እንዳይሆኑ በብርቱ እየተጋ ነው። ከሁሉ በላይ እጅግ በጣም የሚያሳዝነውና ልብ የሚሰብረው፣ ወንድሞቻችን በሐይማኖት ቅናት ተነሳስተውና ማርያምን፣ ቅዱሳን ሰዎችንና ቅዱሳን መላእክትን ያከበሩ እየመሰላቸው የዚህ ክፉ ጠላት መሳሪያ መሆናቸው ነው። ነገር ግን ከዚህ የጥፋት መንገድ ተመልሰው የጽድቅ አገልጋዮች እንዲሆኑ በቃልም፣ በጸሎትም ተጋድሎአችን ይቀጥላል።
ከእግዚአብሔር ጋር የነበረን ጠላትነት በሞቱ ተወግዶ መታረቃችን ከተፈጸመ ጊዜ ጀምሮ፤ በመንፈስ፣ በነፍስና በሰውነታችን - በሁለንተናችን መዳና ሆኖልን በአዳም ውድቀት የተነጠቅነውን የልጅነት ክብር ፈጽሞ እስክንለብስ ድረስ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ያለ መካከለኛ፣ የአዲስ ኪዳን ዋስ፣ ጠበቃ፣ አማላጅ፣ ጌታ፣አዳኝ፣ ሊቀ ካህን፣ የበጎች ትልቅ እረኛ፣ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ…. አማራጭና አቁዋራጭ የሌለው ብቸኛ የሕይወት መንገድ ነው። ስለዚህ ዛሬም፣ ነገም… በዚህች ምድር ላይ እንመላለስባቸው ዘንድ እግዚአብሔር ቆጥሮ በሰጠን ጥቂቶቹ ዓመታቶቻችን ሁሉ እርሱን ብቻ እንሰብካለን!!!!!!!!!!!!
No comments:
Post a Comment