by Tibebe Belay
በቀደመው ኪዳን በነበረው አገልግሎትና የአገልግሎት ሥርዓት ምሳሌነትና አስረጂነት የተገለጠው የእግዚአብሔር መንፈሳዊና ዘላለማዊ ሥርዓት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንፈስ የሆነው አምላካችን እጅግ ጥልቅ የሆነውን ሰማያዊ ሀሳቡን ለእኛ ለማስረዳት በዙሪያችን ያሉና በፍጥረታዊ አዕምሮ ልንረዳቸው የምንችላቸውን ቃላት ይጠቀማል። የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፣ የእግዚአብሔር መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤት፣ የእግዚአብሔር ሕንጻ፣ የእግዚአብሔር እርሻ፣ የእግዚአብሔር ድንኩዋን፣ የእግዚአብሔር ከተማ፣ የእግዚአብሔር ገነት፣ የእግዚአብሔር መንግሥት፣ የእግዚአብሔር ዙፋን------ እነዚህ ሁሉ ስለአንድ መንፈሳዊ አካል የተነገሩ የተለያዩ መገለጦች (Manifestations)፣ በተለያየ መንፈሳዊ ከፍታ ላይ ስለሚገኝ አንድ ሕዝብ - የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚናገሩና እጅግ የጠለቀ መንፈሳዊ ምሥጢር የያዙ፣ ነገር ግን በፍጥረታዊ ቁዋንቁዋ የተነገሩ መንፈሳዊ እውነታዎች መሆናቸውን የምትረዱበትን የጥበብና የመገለጥ መንፈስ እንዲሰጣችሁ በአምላኬ ፊት እንበረከካለሁ።
እግዚአብሔር መንፈስ በመሆኑ ምክንያት፣ እርሱ የሚኖርበትን የመንፈሳዊ ዓለም እውነታዎች በፍጥረታዊ አእምሮ ሊረዱትም ሆነ በፍጥረታዊ ቃላት ሊገልጡት አስቸጋሪ ነው። መንፈስ የሆነው እግዚአብሔር የሚኖረው ማንም ሊያየው በማይችል ብርሐን ውስጥ - በሰማያት - በመንፈሳዊ ከፍታዎች ላይ ነው። እኛ ደግሞ በአዳም በሆነው አለመታዘዝ ምክንያት ከእርሱ ተለይተን ወደዚህ ድቅድቅ ጨለማና ኃጢአት ወደሞላበት ምድር ወድቀናል። ሰለዚህም መንፈሳዊውን እውነታ የምንረዳበትም ሆነ የምናስተውልበት አቅም የለንም። አዳም ከመውደቁና ከእግዚአብሔር ከመለየቱ በፊት ያደርግ እንደነበረውም የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት አንችልም።
የሰው ቁዋንቁዋ መንፈሳዊውን እውነታ እንዳንረዳ በእኛና በመንፈሳዊው ዓለም መካከል ቆሞ የሚከላከል ትልቅ አጥር (barrier)ነው። መንፈሳዊውን ነገር በፍጥረታዊ ቃል ለመግለጽም ሆነ ለመረዳት አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ሕገ ወጥም ነው። ጳውሎስ ወደ ሦስተኛው ሰማይ - ወደ ገነት - ከፍ ወዳለው መንፈሳዊ መገለጥ በተነጠቀ ጊዜ “ሰው ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል” (Inexpressible words which is NOT LAWFUL for a man to utter) እንደሰማ ተናገረ። ስለዚህም “ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል፣ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም። እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።” በማለት አንድ ሰው መንፈሳዊውን ነገር ሊረዳም ሆነ ሊመረምር ስለሚችልበት አንድ ልብ ወይም መንፈሳዊ አእምሮ - ስለክርስቶስ ልብ - the mind of Christ. ተናገረ። (2ቆሮ. 12፡1-5 1ቆሮ.2፡14-16)
ስለዚህ ሰው በዳግመኛ ልደት ብቻ ሊገኝ በሚችለው በዚህ አዲስ ልብና መንፈስ ጎልምሶና ጠንክሮ የእግዚአብሔርን መንፈስ ነገር በሙላት ወደሚረዳበት መንፈሳዊ ከፍታ እስኪወጣ ድረስ፣ እግዚአብሔር በዙሪያችን የሚገኙትን ፍጥረታዊ ነገሮች እየተጠቀመ ስለመንፈሳዊው ዓለም እውነታዎች ያስረዳናል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይከተለው ለነበረው ሕዝብ የእግዚአብሔር መንግሥት ምን እንደምትመስል ለማስረዳት “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እንመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን?” እያለ፣ በዙሪያቸው ሊያዩአቸው በሚችሉ እና ከየዕለት ኑሮአቸው ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ነገሮችን እየተጠቀመ ሲያስረዳቸው እናያለን። ሰማይ፣ ምድር፣ ወንዝ፣ ቤት፣ በር፣ ገበሬ፣ ዘር፣ እርሻ፣ ውሀ፣ ባህር፣ በግ፣ ፍየል፣ ተራራ፣ ሸለቆ፣ እባብ፣ ዘንዶ፣ ባል፣ ሚስት፣ ጋለሞታ፣ ሴት፣ ወንድ ልጅ፣ ከተማ፣ አውሬ፣ ዙፋን…. እነዚህና የመሳሰሉት ሌሎች በዙሪያችን የምናውቃቸው ነገሮች ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱሳችን (በተለይም በዮሃንስ ራዕይ መጽሐፍ ውስጥ) በተለያየ ጊዜ የተጠቀሱና መንፈሳዊውን ነገር ማየት እንድንችል የእግዚአብሔር መንፈስ እንደምሳሌነት የተጠቀመባቸው የሰው ቃላቶች ናቸው።
ታድያ እነዚህን መንፈሳዊውን እውነታ እንድናስተውል የሚጠቅሙንን ምልክታዊ ቃላት፣ በመደዴው (Literally) ከተረዳናቸው ወይም አጣመን ከተረጎምናቸው እግዚአብሔር ሊገልጥልን ከሚፈልገው እውነት እንስታለን። ለዚህም ነው ዛሬ በዚህ “በመጨረሻው ዘመን” የምንገኝ ክርስቲያኖች በተለይም የዮሃንስን ራዕይ መጽሐፍ የተረዳንበት መንገድ በእጅጉ የተዛባ በመሆኑ፣ ….በቅርብ ዓመታት ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “በአምባላይ ፈረስ” ላይ ተቀምጦና ዕልፍ አዕላፍ ሰራዊቱን አስከትሎ ወደዚህ ምድር በመምጣት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ በምትገኘው የኢየሩሳሌም ከተማ የመጨረሻውንና “አርማጌዶን” የተባለውን ጦርነት ከታላለቅ የአሕዛብ ነገሥታት ጋር አድርጎና ድል ነስቶ፣ ከዚያም መንግሥቱን በእሥራኤል ምድር እንደገና መስርቶና “በዳዊት ዙፋን ላይ” ተቀምጦ ዓለምን ሲያስተዳድር ለማየት የምንጠብቀው። ወይም ደግሞ ሌሎቻችን በዚህ ምድር ላይ ሊመጣ ካለው “ታላቅ መከራ” ለማምለጥ “በአየር ተነጥቅን”፣ በሰማያት ካለው ንጉሳችን ጋራ “በአየር ተገናኝተን” እና፣ በሰማያዊው ንፍቀ - ዓለም (Universe) ውስጥ በምትገኝና “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ተብላ በምትጠራ አንዲት በወርቅና በተለያዩ የከበሩ ድንጋዮች በተንቆጠቆጠች ከተማ ውስጥ ዘላለማዊ ኑሮአችንን ለመጀመር “የመነጠቃችንን” ወይም ደግሞ ቀናችን ደርሶ የምንሞትበትን ጊዜ በጉጉት የምንጠብቀው።
“አዲስ ሰማይና አዲሰ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፣ ባሕርም ወደፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምጽ ከሰማይ፡- እነሆ የእግዚአብሔር ድንኩዋን በሰዎች መካከል ነው፤ ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።” (ራእይ.21፡1-4)
No comments:
Post a Comment