Thursday, June 28, 2012

የእግዚአብሔር ምስክር!!!

by Tibebe Belay ·

"አብ አባት ያልሆነበት ቅጽበት እንደሌለ ሁሉ ወልድም ልጅ ያልሆነበት ቅጽበት እንደሌለ እወቁ ተረዱ፤ በአብና በወልድ መካከል የጊዜ መቀዳደም እንደሌለ እወቁ ተረዱ፡፡" የሚለው ምስክርነት የማን ነው???

‘አባቶች’ ስለክርስቶስ ሲናገሩ፡- "ከብርሐን የተገኘ ብርሐን፣ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣... ነው" ብለውናል። እዚህ ላይ ጥያቄዎችን እንጠይቅ፡- "ተገኝ - ተወለደ" ሲሉ ምን ማለታቸው ነበር? 'መቼ' ተገኘ?? 'መቼስ' ተወለደ?? የዛሬ 2000 ዓመት? ወይስ "ዓለም ሳይፈጠር?"  ከተወለደስ እንዴት በአባትና በልጅ መካከል "የጊዜ መቀዳደም" የለም ተባለ?? ካልተወለደስ እንዴት "ልጅ" ተብሎ ተጠራ?

በእርግጥ ክርስቶሰ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እናውቃለን፣ ነገር ግን "መቼና እንዴት ተወለደ?" የሚለውን ጥያቄ ከመጠየቅ በቀር መልስ ማግኘቱ ስለከበደ ነው ክርስቶስ የማይመለስ ጥያቄና የማይደረስበት ምሥጢር ደግሞም በዘመናት መካከል እየበዛና እየጨመረ ለመጣው የክርሰቲያኖች መከፋፈልና መለያየት ምክንያት የሆነው። አይደለም ይሄን የጠለቀውንና ከሰው አስተሳሰብና አዕምሮ በላይ የሆነውን የመለኮት ምሥጢር ቀርቶ፣ የሥነ - ሕይወት ምሁራን ከሚሰጡን ጥቃቅን መረጃዎች በቀር የእኛም አጥንት በእናቶቻችን ማሕጸን ውስጥ እንዴት እንደተዋደደ የምናውቀው ነገር የለም።

ነገር ግን ይህ የዘመናት ምሥጢር የማይገለጥ አይደለም። አብ ከሳበው በቀር ወደ ወልድ ሊመጣ የሚችል ማንም እንደሌለ ሁሉ፣ አብ ካልገለጠለት በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም። አብ ራሱን ለሰዎች የሚገልጠው ደግሞ በልጁ ስለሆነ "ወልድ ካልገለጠለት በቀር አብን የሚያውቅ የለም፣"። ሰለዚህ ከሁሉ አስቀድሞ አብ ወልድን የገለጠልን ውይም ደግሞ እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረው፣ "በርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፣ እርሱን ስሙት" ብሎ ነው። ይሄንኑ መገለጥ፣ ይኸው የሰማይ አባት ለጴጥሮሰ ሲገልጥለት፣ በዚያ መገለጥ ላይ የእያንዳንዳችን እምነትና ሕይወት - ቤተ ክርሰቲያን ተመሰረተች። "አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ።"  ወንድሞቼ ሆይ!! ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር እንዴትና በምን ሁኔታ እንደነበር፣ ወይም ደግሞ "በዓለም ፍጻሜ" እነዴት እንደሚገለጥ ለማወቅ ከመጣራችሁ አስቀድሞ፣ ዛሬ እምነታችሁና ሕይወታችሁ የቆመበትን መሠረት እወቁ። ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?... ሰዎች የሰውን ልጅ ማንም ይበሉት፣ ምክንያቱም የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይበልጣልና። ዋናውና ተፈላጊው ነገር እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረው ነው። ስለዚህ እናንተስ ማን እንደሆነ ትላላቸሁ?? ለዚህ ጥያቄ የምትሰጡት መልስ ነው እግዚአብሔር በጽዮን በመሠረተው፣ ነቢያቱ አስቀድመው በተናገሩትና ሐዋርያቱ በሰበኩት ጠንካራ ዐለት ላይ እንድትቆሙ፣ በእምነታችሁም ሆነ በሕይወታችሁ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ እንድትኖሩ የሚያደርጋችሁ።

“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- እነሆ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፣ የከበረውን መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ የሚያምንም አያፍርም።” ኢሳ.28፡16

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የሰማው ወንጌል የመሠረተውም በዚህ ጠንካራ ዐለት ላይ ነበር። ሓዋርያው የነገረውን ሁሉ በጥንቃቄ ከሰማ በህዋላ፣ “እነሆ ውሀ እንዳልጠመቅ ምን ይከለክለኛል??” ብሎ በጠየቀ ጊዜ፣ የፊሊጶስ መልስ “በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዶልሀል፤” ነበር። ኢትዮጵያዊውም፡- “ኢየሱሰ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ።” በማለት የሰማው ወንጌል በውስጡ የፈጠረለትን እምነት በአንደበቱ መስክሮ፤ ሕይወቱንም ሆነ እምነቱን በተፈተነው፣ በከበረውና በጸናው ዐለት ላይ አገኘ።

ወንድሞች ሆይ! ስለ ክርሰቶስ ማንነት የሚኖረን ትክክለኛ እውቀትና መረዳት የሚነሳው ክዚህ መሠረት ላይ ነው። ማንም እምነቱንና ሕይወቱን ብቻ ሳይሆን ስለክርስቶስ ያለውን እውቀትና መረዳት ከዚህ እግዚአብሔር ስለልጁ ከመሰከረው መገለጥ ላይ ካልጀመረ፣ ክርስትናው ሐይማኖት ይሆነው እንደሁ እንጂ፣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርስና በሰዎች ትምሕርት ያልተበከለ እውነተኛና “ቀጥተኛ” እምነት አይሆነውም። የተመሠረተ ይታነጻል፣ ደግሞም ይደመደማል። የተወለደ ያድጋል፣ ብሎም ሙሉ ሰው ይሆናል። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱሰ የሰጠን የዘላለም ሕይወትም ሆነ፣ ስለ እግዚአብሔር ልጅ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖረን ዕውቀትና መረዳት ሙሉና ፍጹም የሚሆነው፣ ሰዎች የራሳቸውን ግምትና አስተሳሰብ ስለነገሩን ሳይሆን፣ አንደኛ ክርስቶስ ራሱ በትንሳዔው ሀይል አማካኝነት ለቤተክርስቲያን በሰጣቸው ስጦታዎች መጠቀም የቻልን እንደሁ፤  (ኤፌ.4፡11-16) እንዲሁም ክርስትና ማለት ክርስቶስን መከተል ወይም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆን ነውና፤ ስለ ሕያው እግዚአብሔር ልጅ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖረን ዕውቀትና መረዳት ሙሉና ፍጹም የሚሆነው፣ በየዕለት - ከዕለት ሕይወታችን እርሱን በመታዘዝ መከተል ከሆነልን ነው። (ዮሃ.14፡21)             

No comments:

Post a Comment