Thursday, June 28, 2012

“ያለ ድንግል ማርያም አማላጅነት አለም አይድንም??”

by Tibebe Belay on Thursday, June 14, 2012 at 8:39am ·

በመሰረቱ ጥያቄው በራሱ የተሳሳተ ነው። ምክንያቱም “በማርያም አማላጅነት አለም ይድናል ወይስ አይድንም?” ተብሎ ከመጠየቁ በፊት፣ “ማርያም አማላጅ ናት??” የሚለውን ጥያቄ አስቀድመን መመለስ ይኖርብናል። የዚህን ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ ስናገኝ ደግሞ ከላይ በርዕሱ ላይ የተጠየቀው ጥያቄ በራሱ ከመንገድ ይወገዳል ወይም ጥያቄ መሆኑ ይቀራል።

ማርያም አማላጅ ናት?
ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ ሊሰጥ የሚገባው በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ከእርሱ ውጪ የሆኑት መልሶች ሁሉ መልሶች ሳይሆኑ ወንድማችን ያሬድ አሻግሬ እንዳለው፣ “ሰዎች አይናቸውን ከኢየሱሰ ላይ እንዲያነሱ የሚያደርግ” የጠላት ዲያብሎስ ስልት ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የተገለጠው፣ የክርስቶስ መካከለኝነትና ምልጃ (The mediating & intercession of Jesus Christ) እንጂ የማርያም ወይም የመላእክት ወይም የቅዱሳን መካከለኝነትና ምልጃ አይደለም። ስለዚህ ወንድሞቻችን “የማርያምን አማላጅነት” ብቻ ሳይሆን “ያለማርያም አማላጅነት አለም አለመዳኑን እንድንረዳ” ወደነአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የምስጋና ቃላት እና ወደ   “መፃህፍተ ቅዳስያትና አርጋኖ” የመሩንም ለዚሁ ነው።

=>“አንድ እግዚአብሔር አለና፣ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶሰ ኢየሱሰ ነው፤” 1ጢሞ.2፡5
=>“…የሞተው፣ ይልቁንም ከሙታን የተነሳው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፣ ደግሞ ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” (ሮሜ.8፡34)
=>“ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደእኛ የተፈተነ ነው እንጂ፣ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” (ዕብ.4፡15-16)  
=>“ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና፣ ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደእግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።” (ዕብ.7፡25)
=>“ክርስቶስ በእጅ ወደተሰራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፣ ነገር ግን ስለእኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደእርስዋ ወደሰማይ ገባ።” (ዕብ.8፡24)

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን የሓዋርያት ትምሕርቶች ያስቀመጥኩት ‘አይናቸውን በጨው አጥበው’፣ “ክርሰቶስ አሁን እየፈረደ ነው እንጂ እየማለደ አይደለም” ለሚሉት ጭፍን የሐይማኖት ጠበቃዎች ሳይሆን (እነርሱም አንድ ቀን ይሄ በአጉል የሐይማኖት ቅናት የደነደነ ልባቸው በቃሉ መዶሻ እንደሚሰበር አምናለሁ) ይልቁንም እንደቤርያ ሰዎች “ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን?” እያሉና ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ወደ እውነት - ወደ ክርስቶስ ለመመለስ የተዘጋጀ ልብ ላላቸው ሁሉ ነው።

ወገኖቼ ሰሙኝ!! “ያለ ድንግል ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም??” የሚል ጥያቄ ፈጽሞ አይጠየቅም። “ማርያም አማላጅ ናት፣ ያለማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም…” የሚለው “ትምሕርት” ፤ ስለመተላለፋችን ቆስሎ ስለበደላችን የደቀቀው ፣ ደግሞም “ደዌን የሚያውቅ - የህማም ሰው” የተባለውና በድካማችን ሁሉ ሊራራልን የሚችለው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “እናንት ደካሞች ሸክም የከበደባችሁ ሁሉ፣ ወደእኔ ኑ ፣ እኔም አሳርፋችሁዋለሁ” እያለ የዚህ ዓለም ደካሞችን የሚጣራበትን የርህራሄ ድምፅ ሰዎች እንዳይሰሙ ጠላት ዲያብሎስ በፈጠረው ግርግርና ሁካታ መሀል የሚነገር የሐሰተኛ ነቢያት ቃል ነው። በክርስትና ውስጥ እንዲህ አይነት ትምሕርት የለም። እውነተኛ ክርስቲያኖችም ይሄን የመሰለ ጥያቄ አያነሱም። ምክንያቱም ጥያቄ የሚነሳው የተማርነው አልገባ ሲለን ነው። የተከተልነው ክርስቶስም ሆነ፣ ክርስቶስን የሰበኩን ሐዋርያት እንዲህ አይነት ትምሕርት አላስተማሩንም።   

በየዘመናቱ የተነሱና ዛሬም ያሉ የወንጌል ባለአደራዎችስ “እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል??” እያሉ ለሚጠይቁአቸው የዚህ ዓለም ጎሰቁዋሎች ሁሉ፤ “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፣ አንተና ቤተሰቦችህም ትድናላችሁ” እያሉ መልካሙን የምሥራች ይሰብካሉ። በእውነት የክርስቶስ ኢየሱስ ምስክሮች የሆኑና በእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል የተቀቡ የቃሉ ባለአደራዎችስ “መዳን በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” የሚለውን ግልጽና የማያሻማ የመዳን መንገድ ለሰዎች ሁሉ ያሳያሉ። በእውነት በእግዚአብሔር የተጠሩ የመንግሥቱ ሠራተኞች፤ ለሚጠይቁአቸው ሁሉ መልስ የሚሰጡት በልባቸው ውስጥ ተሰውሮ ከተቀመጠው ዘላለማዊው “የጥበብና የእውቀት መዝገብ” ነው እንጂ፣ በሕይወት በኖሩበት ጥቂት ዘመን የተናገሩት ነገር እውነት ይሁን ሐሰት ከማይታወቁ ሰዎች ማስታወሻ ላይ አይደለም። እነዚህ የወንጌል ባለአደራዎች ቃላቸውም ሆነ ስብከታቸው ክርስቶስ ነው።

“በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆረጬ ነበርና።” (1ቆሮ.2፡2)                
· · · Share · Delete

No comments:

Post a Comment