Thursday, June 28, 2012

የራዕይ አስራ ሁለትዋ ሴት ማርያምም፣ እሥራኤልም አይደለችም፤ ቤተ ክርስቲያን ናት!!

by Tibebe Belay on Saturday, June 9, 2012 at 6:07am ·

በምዕራፍ 1፡19 ላይ ያለው ሀሳብ የራዕይ መጽሐፍን ለማጥናት የመጀመሪያው ቁልፍ ነው። “… ያየኸውን፣ አሁንም ያለውን ከዚህም በህዋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ።” በነዚህ ሦስት የጊዜ ሰሌዳዎች መሰረት የመጽሐፉን ምዕራፎች በጠቅላላ በሦስት ክፍሎች ከፍለን ስናጠና፣ ምዕራፍ አስራ ሁለትን የምናገኘው “ከዚህም በህዋላ” በሚለውና ዮሐንስ ራዕዩን ከመጻፉ በፊትም ሆነ እየጻፈ ያለበትን ጊዜ ሳይሆን ወደፊት የሚፈጸሙ ክስተቶችን (Future events) በያዘው በሦስተኛው ክፍል ውስጥ ነው። ከዚህም የተነሳ ምዕራፍ አሥራ ሁለት እስራኤልንም ሆነ ማርያምን የሚመለከት ሊሆን አይችልም።

ሁለተኛውን ቁልፍ የሚገኘው በዚሁ የመጀመሪያ ምዕራፍ ቁጥር 20 ላይ ነው። “በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላዕክት (Messengers) ናቸው፣ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።” በዚህ ጥቅስ መሰረት የራዕይ መጽሐፍ የጠለቀውን መንፈሳዊ እውነታ (Spiritual reality) በምልክታዊ አገላለፆች (Symbolic expressions) የሚገልጥና፣ ለማጥናትም ሆነ ለመተርጎም እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ዮሐንስ “በጌታ ቀን በመንፈስ” ሆኖ የተቀበለው ራዕይ በመሆኑ፣ ልንረዳው የምንችለውም በዚያው ዮሐንስ በጻፈበት ቅዱሱ የእግዚአብሔር መንፈስ ገላጭነት ብቻ ነው።

እነዚህን ሁለት ቁልፎች ይዘንና ወደ ዋናው ሀሳባችን ተመልሰን እጅግ በጣም ጠቃሚና ገላጭ የሆኑትን ጥቂት ሀሳቦች ብቻ እንመልከት፡- “ታላቅም ምልክት በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጎናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። እርስዋም ፀንሳ ነበር፣ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጨንቃ ጮኸች።…. አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደእግዚአብሔር ዙፋን ተነጠቀ…”

ልብ በሉ! ምልክቱ የታየው በሰማይ ነው። ይህም የሚያመለክተን የተዘረዘሩት ነገሮች ሁሉ የተገለጡት በመንፈሳዊው ክበብ  (Spiritual realm) መሆኑን ነው። ስለዚህም የተከሰቱት ነገሮች ሁሉ “በመደዴው” (Literally) የማንትረጉማቸው፣ የማንረዳቸውም ናቸው ማለት ነው። ሴቲቱ አንዲት ግለሰብ (ይህ ቃል ቅድስት ማርያምን የሚመለከት አይደለም) ፣ ጭንቀትዋና ምጥዋም ሴት እናቶቻችን ልጅ ሊወልዱ ሲሉ እንደምናየው ዐይነት፣ በብዙ ጭንቅና ምጥ የወለደችውም ወንድ ልጅ እንዲሁ አንድ ጨቅላ (ይህም ስለ ኢየሱስ የተነገረ አይደለም) … እንደሆኑ ልናስብ አይገባንም ማለት ነው።

ሴቲቱ የተጎናጸፈችው ፀሐይ ==== “የፅድቅ ፀሐይ” የተባለው ክርስቶስ በመሆኑ ይህን “ለሰው ሁሉ የሚያበራ እውነተኛው ብርሃን” የለበሰች ሴት ከቤተ ክርስቲያን ሌላ ማን ልትሆን ትችላለች?

በአስራ ሁለት ከዋክብት የተመሰሉት አክሊሎችዋ ===== በዘመንዋ ጅማሬ ላይ በምድር ላይ ደምቀው የነበሩት የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው።….

የሴቲቱ ምጥና ጭንቀት===== ቤተ ክርስቲያን በዘመናት መካከል ስለጽድቅ የምትቀበለው መከራ ምሳሌ ነው። “… ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል…” እያሉ የቀደሙት ደቀ መዛሙርት የተናገሩት ቃል፣ ቤተ ክርስቲያን - በየዘመናቱ ስለ እምነት የምትከፍለውን ዋጋ የምትቀበለውንም መከራ የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን፤ በውስጥዋ ያሉ የእግዚአብሔር ልጆች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዳይገቡ እንቅፋት ከሆነው “የሥጋ ስራ” ጋር በየግል ሕይወታቸው የሚያደርጉትን ግብ-ግብ የሚያመለክት ነው። በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ በውጭ ባለ ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን፣ በውስጣቸው ካለ ሥጋዊ ፍላጎትና ባሕሪይ የተነሳ በጽድቅ ለመኖር በሚያደርጉት ተጋድሎ መከራና ጭንቀት ይሆንባቸዋል።።          

የወለደችው ወንድ ልጅና ወደዙፋን መነጠቁ ======= ከላይ እንዳልኩት፣ ይሄ ወንድ ልጅ አንድ ጨቅላ ሕጻን እንደሆነ ካሰብን እንስታለን። በእንግሊዝኛው MAN CHILD ተብሎ የተተረጎመው ይህ ቃል “የበሰለ፣ ያደገ፤ ፍጹም የሆነ….” ማንነትን የሚያመለክት ሲሆን ይህ ደግሞ በየዘመናቱ የሥጋን፣ የዓለምንና የሠይጣንን ሀሳብ በሕይወት አካሄዳቸው እያሸነፉ፣ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራና በሙላት መግባት የሆነላቸውን “ድል ነሺዎች” (Overcomers) የሚያመለክት ነው። ቤተ ክርስቲያን - የብዙ ብልቶች ጥርቅም አካል (Corporate Body) እንደሆነች ሁሉ ከማህጸንዋ - ከመካከልዋ የሚወጣውም ወንደ ልጅ እንዲሁ የጥቂት ድል ነሺዎች ስብስብ ነው። ይሄ እውነት ደግሞ ከዘመናት በፊት ነቢዩ ዳንኤል “መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ ይሰጣል፤” በማለት ስለ አንድ ሕዝብ ከተናገረ በህዋላ “መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፣ ግዛቶችም ሁሉ ይገዙለታል ይታዘዙለታልም።” በማለት ከክርስቶስ ጋር አሕዛብን ሁሉ ስለሚገዛውና ስለሚያስተዳድረው አንድ አካል ትንቢት ተናግሮአል። (ዳን.7፡27)   

በተለይ ይሄንን የመጨረሻ ሀሳብ ለማጠናከር፣ በዚሁ በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት በላካቸው በእያንዳንዳቸው መልክዕቶች መደምደሚያ ላይ ድል ለሚነሱት የተሰጡትንና ብዙ ክብር የሞላባቸውን ተስፋዎች እናገኛለን። በተለይ በሎዶቅያ ቤተ ክርሰቲያን ስም፣ ነገር ግን በየዘመናቱ ላሉ ድል ነሺዎች የተገባውን ተስፋ እናንብበው፡-
“እኔ ደግሞ ድል እንደነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፣ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ።….” (ራዕይ.3፡21)

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ አማኞች ሁሉም ድል ነሺዎች አይደሉም። የተጠሩት (The called out – Ekklesia – Church) ብዙዎች ቢሆኑም፣ የታመኑትና መንግሥትን የሚካፈሉት፣ ወይም አሕዛብን ለመግዛትና ለማስተዳደር ብቃትና አመኔታን የሚያገኙት ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው። እነዚህ ወደ ጌታችንና ወደ መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችሁዋል የተባሉት፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ በሁለተኛው መልዕክቱ ምዕ.2፡2-11 እንዳመለከተን፣ በሕይወት ዘመናቸው መንፈሳዊውን ፍሬ በሙላት ማፍራት የሆነላቸው ብቻ ናቸው።

ይሄ ከላይ በጥቂቱ ለማሳየት የሞከርኩት በራዕይ 12 ላይ የሰፈረውን ሀሳብ በሙላት የመግለጽ አቅም ይኖረዋል ባይባልም ቅሉ፣ እስከ ዛሬ ድረስ ስለ ምዕራፉ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ስለ ራዕይ መጽሐፍ ያላችሁን ግንዛቤ ቆም ብላችሁ እንድታዩ ሊያደርጋችሁ እንደሚችል አልጠራጠርም። በመጨረሻም፣ በጳውሎስ ልመና ልመርቃችሁ!!! የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ ይስጣችሁ!!!!! 

No comments:

Post a Comment