የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ በተደጋጋሚ በወንድሞች የሚደርስብኝን ክስና ውንጀላ ለማስቆም አይደለም። ስለራሴ ለመሟገትም አይደለም። ይልቁንም ነገሩን በጽሞና ለሚከታተሉ ወገኖች በዚህ ጉዳይ ላይ ዛሬ ያለኝንና የደረስኩበትን ግልጽ መረዳት ለማሳየት ብቻ ነው። ክርስቲያኖች አንዱ ሌላውን ሳይነቅፍ ወይም ሳያወግዝ በየደረሱበት የመረዳት መጠንና ልክ እንዲመላለሱ ይህ ሐዋርያዊ ምክር ነው። ዛሬ ክርስቶስን በሚመለከት ፍጹምና ምሉዕ የሆነ መረዳት አለኝ አልልም። ምክንያቱ ደግሞ እርሱ በዋናነት የእግዚአብሔር ምሥጢር ከመሆኑ ጋር፣ ክርስቶስን በሙላት የሚረዱትና የሚያውቁት በተጻፉ የሐይማኖት መግለጫዎች ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ብቻ ሳይሆን እንደ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ቃሉን በመጠበቅ፣ በፍጹም መታዘዝና በፍቅር ወደእርሱ ማደግ ሲቻል በመሆኑ ነው።
ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር የተገኘ ወይም የተወለደ አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ። ወንድሞች “የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር” እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገራሉ። እኔ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ - የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እየመሰከርኩ ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳችንም ውስጥ “እግዚአብሔር ወልድ - God the Son” የሚል ቃል በአንድም ቦታ ላይ ተጽፎ እንደማይገኝ የታወቀ ነው። እርሱ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር አንድያ ልጅ ነው። ይህንን “አንድያ” የሚለውን ቃል ለማስረዳት ወንድሜ Solomon Girmatsion በአንድ የውይይት መድረክ ላይ ያሰፈረውን ሃሳብ ከዚህ በታች ልጥቀሰው። (በዚህ አጋጣሚ ወንድሜን ሳላስፈቅድ ይህን መረዳቱን እንደምሳሌ መጠቀሜን ይቅርታ እጠይቃለሁ።)
“መጽሐፍ ቅዱስ እየሱስን አንድያ ልጅ ብሎ ሲጠራው እናያለን (ዮሐ 1፡14, 18፣3፡16, 18 እና 1 ዮሐ 4፡9) እነዚህ ቦታዎች ላይ ያለው የግሪክ ቃል (monogenes)ነው የሚለው። ትርጉሙም “monos” በእንግሊዘኛ “only” በአማርኛ “ብቻ” ማለት ሲሆን ፡ የግሪክ ቃል “genos” ደግሞ በእንግሊዘኛ “stock” “a class” “kind” በአማርኛ “ሸቀጥ” ወይም “አንድ አይነት ተመሳሳይ ወይም ነገር ክምችት” ማለት ነው። monogenes የሚለውን በአንድ ላይ ስንተረጉመው በእንግሊዘኛ unique, one of a kind, one and only ማለት ሲሆን፡ በአማርኛ ደግሞ “አንድ ብቸኛ የራሱ አይነት ” “ከዛው ነገር አንድ ብቸኛ ” ወይም “የተለየ የዛ ነገር ብቻ ” ማለት እንችላለን። ስለዚህ ይህን የግሪክ ቃል ተመርኩዘን አንድያ ልጅ የሚለውን ስንረዳው ትርጉሙ “እንደእግዛብሔር አይነት የሆነ” “አንድና ብቸኛ የእግዛብሔር ልጅ” ብለን እንረዳዋለን።” የጥቅሱ መጨረሻ
በአብዛኛዎቻቸን ዘንድ እንደ ክርስቲያን የማይቆጠሩት “የይሆዋ ምስክሮች” በዮሃንስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ከቁጥር አንድ እስከ ሦስት ላይ ያለውንና “ሎጎስ” የሚለውን ቃል መሠረት አድርገው ስለ ኢየሱስ ሲያስረዱ “እንደ አምላክ ያለ፣ የመለኮትን ባህሪይ የተላበሰ” የሚል ትርጓሜ ይሰጣሉ። ለእኔ፤ “እንደ እግዚአብሔር ዓይነት የሆነ” የሚለው የወንድሜ ሰሎሞን መረዳትና “እንደ አምላክ ያለ” የሚለው የነዚህ ወንድሞቼ አገላለጥ አንድ ነው። በመሆኑም ይሄ እውነት ዓለም ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር ስለተወለደውና ስለተገኘው፣ ደግሞም በእግዚአብሔር ሃሳብና ዓላማ መሠረት ኃጢአተኞችን ለማዳን ራሱን ባዶ አድርጎ ከድንግሊቱ ማርያም በመወለድ ወደዚህ ዓለም ስለመጣው፣ ስለሞተውና በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ስለተነሳው፣ በክብር ስላረገውና በአባቱ ቀኝ ስለተቀመጠው…. አንድና ብቸኛ ስለሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ስለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ያለንን ግራ መጋባት ያስወግዳል ብዬ አምናለሁ። እርሱ የሕያው እግዚአብሔር አንድያና ብቸኛ ልጅ ነው። ለዚህም ነው የእምነታችንም ሆነ የሕይወታችን መሠረት "አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ" የሚለው ከሰማያት ከአባቱ ዘንድ የመጣው ምስክርነት የሆነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ “እግዚአብሔር ነው” ለማለት ከሚጠቀሱ ጥቅሶች ውስጥ በአራቱ ላይ ያለኝንና የደረስኩበትን መረዳት ደግሞ ከዚህ በታች ላቅርብ፤ በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ያለኝን ሃሳብ ከመናገሬ በፊት ግን “እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድም ሦስትም ናቸው” በሚሉና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ቃላት የተዋቀረውን የሥላሴ ትምሕርት ለማጠናከርና እውነት እንደሆነ ለማስመሰል የካቶሊክ እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከፈጸመቻቸው ግልጽ ስህተቶች አንዱን ብቻ እንደምሳሌ ላንሳ፤
“ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም። መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው። የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ።” 1ዮሃ.5፡5-8
በቁጥር ስምንት ላይ የተጠቀሰውንና “የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ” የሚለውን ቃል፤ ወደ እንግሊዝኛ ከተተረጎሙት መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ ሦስተኛ የሆነውና በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በስኮትላንድና በኢንግላንድ ላይ ነግሦ በነበረው “ኪንግ ጀምስ ስድስተኛ” ትዕዛዝ መሠረት በተተረጎመው “አውቶራይዝድ ቨርዥን” ወይም “ኪንግ ጀምስ ቨርዥን” ላይ፡- For there are three that bear record in heaven, the Father, the Word, and the Holy Ghost: and these three are one. ተብሎ መቀመጡን እናነባለን። ከዚያ በኋላ የተተረጎሙ አብዛኛዎቹ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሳት ግን For there are three who bear witness, the Spirit, and the water, and the blood: and the three agree in one. በማለት እንደገና አስተካክለው እንዳስቀመጡት እናነባለን። በዚህ አጋጣሚ በኢትዮጵያው ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስን ሁሉም ሊያነበው በሚችለው አማርኛ የተረጎሙትን ሰዎች ታማኝነትና ጥንቃቄያቸውን ላደንቅ እወዳለሁ።
1. ዮሃ.1፡1-3 “… ቃልም እግዚአብሔር ነበር”
በዚህ ጥቅስ ላይ ያለኝ መረዳት ከላይ ወንድም ሰሎሞን ከተናገረውም ሆነ ወንድሞቼ የይሆዋ ምስክሮች ከሚሉት ጋር የሚስማማ ነው። በዚህ ክፍል “ሎጎስ” ተብሎ የተጠቀሰውና ዓለም ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር የተወለደው አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ፣ አብሮት ከነበረው ከእግዚአብሔር ዘንድ አምላካዊ ባህሪይን ያገኘ ወይም የተካፈለ፣ እንደ አምላክ ያለ፣ እንደ “እግዚአብሔር ዓይነት” ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሃንስ ወንጌል በጸለየው ጸሎት ላይ “ዓለም ሳይፈጠር እንደወደድከኝ፣ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ…” ማለቱ ከአባቱ ዘንድ ስለነበረው ክብር መናገሩ ነበር። በዚህም ማንነቱ በእግዚአብሔር መልክ ይኖር እንደነበር፣ ደግሞም እርሱ የማይታየው አምላክ ምሳሌ እንደሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ አስተምሮናል።
2. “…. ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን።” ሮሜ.9፡5
የግሪክኛውን ቅዱሳን መጻሕፍት አመሳከርን የሚሉ አንዳንድ ትርጉሞች ይህንን ጥቅስ እንዲህ አድርገው ያስቀምጡታል፡-
“ክርስቶስም በሥጋ የተገኘው ከእነርሱ ነው። የሁሉ የበላይ የሆነው የዘላለም አምላክ የተባረከ ይሁን። አሜን።”
ይህን ጥቅስ በተመለከተ ከእነዚህ ሁለት የተለያዩ አተረጓጎሞች ዬትኛው ታማኝ እንደሆነ ለማወቅ ሌሎች የሐዋርያት ትምሕርቶችን ማመሳከሩ አግባብ ነው። ለእኔ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ የለመድኩት ደግሞም የተጠቀምኩበት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ቅዱሳን በጻፈው መልዕክቱ ውስጥ “አንድ ጌታ፣ አንድ መንፈስ” እንዳለ ከጠቀሰ በኋላ፤ “ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ” በማለት ነግሮናል። (ኤፌ.4፡5-6) ስለዚህ ይሄ ከሁሉ በላይ የሆነው አምላክ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነው እግዚአብሔር ነው ማለት ነው።
3. “…..የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን…. “looking for the blessed hope and APPEARING of the glory of THE GREAT GOD and OUR SAVIOR JESUS CHRIST; ቲቶ.2፡12-13
“……በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ፤ through the righteousness of OUR GOD and OUR SAVIOR JESUS CHRIST. 2ጴጥ.1፡1
እነዚህ ሁለት ጥቅሶች ስለሁለት ማንነቶች የሚናገሩ መሆናቸውን አምናለሁ። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ በመልእክቶቹ መግቢያ ላይ በተደጋጋሚ “ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን” እያለ ከጠቀሰው ጋር የሚስማማ ነው። በተለይ በቲቶ.2፡12-13 ላይ የተጠቀሰውን ሃሳብ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቃሉን ለሚጠብቁ ታማኞች ከሰጠው ተስፋ ጋር አብሮ ማየቱ ተገቢ ነው። “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።” እዚህ ላይ፣ “እንመጣለን” የሚለው ቃል ‘erchomai’ የሚለው የግሪክ ቃል ሲሆን በእንግሊዝኛው APPEARING በመባል የሚታወቀው ነው።
4. የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው። And we know that THE SON OF GOD IS COME, and hath given us an understanding, that WE MAY KNOW HIM THAT IS TRUE, and WE ARE IN HIM THAT IS TRUE, EVEN IN HIS SON JESUS CHRIST. This is the true God, and eternal life. (1ዮሃ.5፡20)
የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ የመጣው፣ እውነተኛውን አምላክ እርሱም አባቱን ሊገልጥልን፣ ስለእውነተኛው አምላክ እውቀት እንድናገኝ ልቡናን ወይም መረዳትን ሊሰጠን ነው። እግዚአብሔርን ያየው እንድ ስንኳ የለም፣ በእቅፉ ያለው አንድያ ልጁ እርሱ ገለጠው እንጂ። ስለዚህም የዘላለም ሕይወት የመቀበላችን መሠረቱ፤ እውነተኛ አምላክ፣ ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ስለተባለው ስለ እግዚአብሔር ስለአባታችንና ስለልጁም ስለኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እውቀትና መረዳት፣ ደግሞም ከእግዚአብሔር ከአባታችንና ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለን ሕብረት ላይ የተመሠረተ ነው ማለት ነው። እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት ሰጥቶናል፤ ይህም ሕይወት ያለው በልጁ ነው። ለዚህም ነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሃንስ ወንጌል 17፡3 ላይ ከዚህ በታች ያለውን ግልጽና የማያሻማ ቃል የነገረን፡-
“እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። And this is life eternal, that THEY MIGHT KNOW YOU, THE ONLY TRUE GOD, and JESUS CHRIST WHOM YOU HAVE SENT.
No comments:
Post a Comment