Thursday, December 13, 2012

የክርስቶስ ልደት - “የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ”!!


በዚያኛው ዓለምወቅታዊ መግለጫየሚሉት ነገር አለ። በዓለማችን ላይ በየዕለቱ በተለያየ መጠንና ሁኔታ የሚነፍሰውን የፖለቲካ አየር እየተከተለ የሚሰጥ መረጃ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ሰሞኑን በሐይማኖት ቤት መነገር የጀመረ ዓመታዊ ዜና አለ። እርሱም የዛሬ 2000 ዓመት አካባቢ ከድንግሊቱ ማርያም  ስለተወለደው ሕፃን የሚነገረው ነው። አስቀድሞ በመላእክት የተበሰረውና ክርስቶስና ጌታ የሆነው የኢየሱስ መወለድ፣ የሰውን ልጅ ታሪክ የለወጠ ታላቅ ዜና በመሆኑ በተለይም ገና በጨለማው ዓለም ላሉ ሁሉ ሳያሰልሱ - በየዕለቱ ሊናገሩት የተገባ መልካም የምሥራች ነው። ነገር ግን ሐይማኖት በወደደው መንገድ ቀኑንና ወራቱን ራሱ ወስኖ በተለይ በዚህ ሰሞን የሕጻኑ መወለድ በተለየ መልኩ ይነገራል እንጂ፣ ኢየሱስ ከድንግል ማርያም በምን ወርና በየትኛው ቀን እንደተወለደ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መረጃ የለም። ይህም የሆነው በእግዚአብሔር በራሱ ፈቃድና ሃሳብ ነው። ቀን እንዳይከበር!! እኔምየክርስቶስ ልደትበማለት ጌታ ወደልቤ ያመጣውን ሃሳብ ለመጻፍ መነሳቴ የሕፃኑንየልደት ቀን” በማስመልከትወቅታዊ መግለጫለመስጠት አይደለም። ይልቁንም የዛሬ 2000 ዓመት አካባቢ በእሥራኤል ምድር የሆነው የኢየሱስ ልደት ልክ እንደሞትና ትንሳኤው ሁሉ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ የሚያገኘውን መንፈሳዊ ፍጻሜ ለማሳየት ነው።

በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ። ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት።  ” (ሉቃ.126-27)

“የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ”

በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በግልጽ እንደምናነበው የሰው ስም ባህሪይን የሚገልጽና የሚወስንም ጭምር በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው። ገና በፍጥረት ጅማሬ ላይ እግዚአብሔር ለፈጠራቸው ፍጥረታት በሙሉ ስም የማውጣቱን ኃላፊነት ለአዳም ሲሰጠውና ፍጥረታቱን በፊቱ ሲያሳልፍ፣ በእርሱ በነበረው የጥበብና የመገለጥ መንፈስ አዳም የሰየመው ወይም የገለጠው የእያንዳንዱን ፍጥረት ባህሪይ ነበር። “አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ።” ከዚህም የተነሳ በተለይ በቀደመው ኪዳን ሰዎች የልጆቻቸውን ስም እንዲሁ “ከመሬት ተነስተው” አይሰይሙም ነበር። እግዚአብሔር ያደረገላቸውን አይተው፣ ወይም ደግሞ በልጁ ወይም በልጅቷ ሕይወት ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔር ዓላማ ተመልክተውና የመሳሰሉትን ሁኔታዎች መሠረት አድርገው ነበር የልጆቻቸውን ስም የሚሰይሙት።

ያዕቆብ አታላይነቱ የታወቀው ገና ሕጻን ሳለ "ያዕቆብ" የሚል ስም ሲሰጠው ነው። ስሙ የተሸከመው ባህሪይም በወጣትነት ዘመኑ የታላቅ ወንድሙን የዔሳውን ብኩርና - በብኩርናውም ይገኝ የነበረውን በረከት አታሎ በመውሰዱ ተገለጠ። ሁለቱ መንታዎች ገና በርብቃ ማሕጸን ሳሉና “በጎ ወይም ክፉ ሳያደርጉ” ያዕቆብን ለይቶ የወደደው እግዚአብሔር ግን በዚህ ባህሪው እንዲተወው ፈቃዱ አልነበረም። ከዔሳው ፊት ሸሽቶ በስደት ይኖርበት ከነበረበት ከካራን ምድር ተመልሶ፣ ከወንድሙ ጋር ለመገናኘት ወደ ሴይር ምድር ጉዞ በጀመረበት ሌሊት አገኘው። ስሙንም ለወጠለት፡- “ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፤ ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና።” ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጠውም፡- “ከጠሪው እንጂ ከሥራ ሳይሆን በምርጫ የሚሆን የእግዚአብሔር አሳብ ይጸና ዘንድ” አታላዩ ያዕቆብ ስሙ ተለወጠና “የእግዚአብሔር ልዑል” ተባለ። ይህም ስም የያዘውን ክብርና በረከት ሁሉ አገኘ።

“የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር”

“ማርያም ማርያም ብዬ ስምሽን ስጠራ….” የሚል ዜማ መስማት በአገራችን የተለመደ ነው። እንዲያውም “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” የሚለው ወንጌል - በወንጌሉም የሚሰበከውና ከሰማይ በታች ሰዎች ሁሉ ሊጠሩት የተገባው አንዱና ብቸኛው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተሸፍኖ፤ የማርያም ስም የገነነባት ምድር ናት ኢትዮጵያ! የምንጠራው ስም የተሸከመውን ባህሪይ ወይም ኃይልና ሥልጣን ጠንቅቀን ልንረዳ ይገባል። ማርያም የምትወልደው ሕጻን ስሙ ማን ተብሎ መጠራት እንደነበረበት በመልአኩ አማካኝነት የተነገረው እንደ ወንጌላዊው ሉቃስ አጻጻፍ ለማርያም ደግሞም ማቴዎስ እንደመዘገበው ለዮሴፍ ነበር፡- “እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ!!” የሚገርመው ነገር ይህን አዳኝ የጸነሰችውና የወለደችው ድንግል ስም ግን “ማርያም” ነበር።


እዚህ ላይ ይህን መልእክት ለሚያነቡ ሁሉ አስቀድሜ የማሳስበው፣ ማርያም እግዚአብሔር በእርሷ ሕይወት ሊሰራ ላሰበው የከበረ ሃሳቡ ከመጠራቷ በፊት ስለነበራት ሕይወት ዮሴፍ ለሚባል ሰው የታጨች አንዲት ድንግል መሆንዋን ከመግለጥ ውጪ መጽሐፍ ምንም የሚለው ነገር ባለመኖሩ፤ የዚህ መልእክት ዋና ዓላማ ማርያም እንዲህና እንዲያ ነበረች ለማለት ፈጽሞ አይደለም። የማርያም የስሟ ትርጉም ግን ምን እንደሆነ ለብዙዎቻችን የተገለጠ አይመስለኝም። ምክንያቱም ስለ ማርያም የሚነገሩና ሐይማኖት የፈጠራቸው አፈ ታሪኮች በአእምሮአችን ውስጥ ከመጠቅጠቃቸው የተነሳ ነው። የዚህ እውነት መገለጥ  የብዙዎችን አእምሮ ሊጎዳ ቢችልም፣ የስሜታቸው መጎዳት ለነፍሳቸው ደህንነት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የእኔም ዓላማ የማርያምን ስም ማብጠልጠል እንዳልሆነ ሊረዱት ይገባል። “ማርያም” የሚለው ሰም የሂብሪው ትርጓሜው፡- “መራርነት” እና “ዓመጽ” ወይም “መራራ” እና “ዓመጸኛ” ማለት ነው።

ከላይ እንዳልኩት የዚህ መልእክት ዓላማ የዛሬ 2000 ዓመት አካባቢ በእሥራኤል ምድር የሆነው የኢየሱስ ልደት ያለውን አንድምታና በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ እንዴት መንፈሳዊ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ለማሳየት በመሆኑ፤ በመልእክተኛው በኩል የመጣላትን ቃል “እነሆኝ የጌታ ባርያ እንደቃልህ ይሁንልኝ” በማለት ተቀብላ አዳኙን የጸነሰችውና የወለደችው “ማርያም” የዓመጸኛዋና የመራራዋ ነፍሳችን ምሳሌ እንደሆነች መረዳቱ፣ እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ሕይወት ይፈጽመው ዘንድ
በክርስቶስ ኢየሱስ የጀመረውን የማዳን ሥራ መረዳት እንድንችል የሚሰጠን ጠቀሜታ ቀላል አይባልም። ጌታ ቢፈቅድና ብንኖር ወደፊት ይህን ሃሳብ ሰፋ አድርገን ኣናየዋለን!!!!

No comments:

Post a Comment