Tuesday, November 20, 2012

የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ የሚገኝ አንድነት!!


“እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።” (ኤፌ.4፡1-6)

“ለምንድነው ዛሬ ‘ክርስቲያኖች’ ተብለን በምንጠራው ወንድማማች የእግዚአብሔር ልጆች መካከል በቀድሞው ዘመን በሰናዖር ምድር እንደሆነው አይነት የቋንቋ መደበላለቅና ትርምስ የሆነው?” የሚለው ጥያቄ በአእምሮዬ ውስጥ መጮህ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። “የክርስቲያኖች ሕብረትና አንድነት” የሚለው የውይይት መድረክም የተጀመረው ይሄን ጥያቄ በክርስቲያን ወንድሞቼም አእምሮ ውስጥ ለመጫርና፤ ለዚህ ግራ መጋባት፣ መበታተንና መከፋፈል ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ሕያው በሆነው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ለመመርመርና ለመለየት፣ ከዚያም ከማይጠፋው ዘር የተወለዱት ነገር ግን ሐይማኖት በፈጠራቸው ልዩ ልዩ “ጎሳዎች” ተከፋፍለው ወዲያና ወዲህ የተበታተኑትን “የደረቁ አጥንቶች” እርስ በርሳቸው ለማቀራረብ ነበር። በእርግጥ ዛሬ ስንቶቹ ወንድሞቼ ይህን ጥያቄ እየጠየቁ እንደሆነ አላውቅም።

ከላይ ባነበብነውና የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ለኤፌሶን ቅዱሳን በጻፈው መልእክቱ ውስጥ እንደገለጠው፤ አንድ ተስፋ፣ አንድ አካል፣ አንድ መንፈስ፣ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት እና ከሁሉ በላይ የሚሆን፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። ይሄ አንድ አምላክ እና የሁሉም አባት የተባለው እግዚአብሔር ለሰዎች ሁሉ የሰጠው አንድ ተስፋ እርሱም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ነው። ሰዎች ይህን የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሚቀበሉት ደግሞ፤ እግዚአብሔር ለዓለም ሁሉ የኃጢአት ሥርየትና የሕይወት ምንጭ እንዲሆን የላከውን አንድያ ልጁን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አምነው ሲቀበሉ ነው። ክርስትና የተባለው አንድ እምነት የተመሠረተው በዚህ ሕያው እውነት ላይ ነው። “አንድ ጌታ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ማመን!!! እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ከመሠረተው ከዚህ የእምነትና የሕይወት መሠረት በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልም። ዛሬ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት፣ የይሖዋ ምስክር፣ “ኦንሊይ ጂሰስ”፣ አድቬንቲስት፣ ሙሉ ወንጌል፣ …. በሚሉና ሐይማኖት በፈጠራቸው የተለያዩ ቅጥሮች ውስጥ ሆነውና በተለያየ አስተምህሮ ተከፋፍለው በጎሪጥ የሚተያዩትን ወንድሞቼን አንድ ጥያቄ ልጠይቅ እወዳለሁ፡- የእምነታችሁና የሕይወታችሁ መሠረት ዬትኛው የእምነት መግለጫ ወይም አስተምህሮ ነው????????

ማንም ይህን ጥያቄ ከክርስቶስ ትምሕርትና ከሐዋርያቱ መልእክቶች ውጪ በሆኑ ሌሎች አስተምህሮዎች ለመመለስ ከሞከረ፣ እግዚአብሔር ከመሠረተው የእምነትና የሕይወት መሠረት ውጪ ራሱን ያገኛል። በመሆኑም “እኔ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር - ክርስቲያን ነኝ” ለማለት ካለመቻሉም በላይ እግዚአብሔር የሰጠውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ለመቀበሉ እርግጠኛ ሊሆን አይችልም። የመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የነበሩት ሐዋርያት አስቀድመው ራሳቸውን በዚህ እግዚአብሔር በመሠረተው የእምነትና የዘላለም ሕይወት መሠረት ላይ ካቆሙ በኋላ ነው ለእኛ ይህንን አንድ የእምነትና የሕይወት መሠረት ያኖሩልን።
“ስምዖን ጴጥሮስ፡- ጌታ ሆይ ወደማን እንሄዳለን?? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆንክ አምነናል፣ አውቀናልም ብሎ መለሰለት” (ዮሃ.6፡28-29)

የክርስቶስ ሐዋርያትም ሆኑ የእነሱን እግር ተከትለው ወንጌልን ለዓለም ሁሉ መስበክ የጀመሩት የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የእግዚአብሔር መንግሥት ሠራተኞች፣ የሰዎችን እምነትና ሕይወት የመሠረቱት በዚህ በተፈተነው፣ በከበረውና መሠረቱም በጸናው ሕያው ዓለት - በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነበር። ሐዋርያቱ ወንጌልን ከኢየሩሳሌም ጀምረው በሰበኩበት በዚያ ዘመን በመጀመሪያው የሐዋርያት አገልግሎት ወደዘላለም ሕይወት ተስፋ ከተጠሩት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ተርታ የምናገኘው፣ ለእሥራኤል አምላክ ለመስገድ ወደ ኢሩሳሌም ሄዶ የነበረው ኢትዮጵያዊውን የመንግሥት ባለሟል ነው። ፊሊጶስ በቀጥታ ከእግዚአብሔር መንፈስ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ለዚህ ኢትዮጵያዊ የክርስቶስን የመስቀል ላይ ሕማም ከሚናገረው ከኢሳያስ መጽሐፍ ጀምሮ ስለኢየሱስ ወንጌልን ከሰበከለት በኋላ፣ ኢትዮጵያዊው በውኃ ተጠምቆ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ሲወስን ከፊሊጶስ የቀረበለት አንድ ቅድመ ሁኔታ ነበር፡- “በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዶልሃል!” ኢትዮጵያዊው የመለሰው መልስ፣ ወይም በአንደበቱ የተናገረው የእምነቱ መግለጫ ልክ ሐዋርያቱ አስቀድመው እምነታቸውንና ሕይወታቸወን የመሠረቱበት የእምነት መግለጫ ነበር፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ!!!”     

አሁንም ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት፣ የይሖዋ ምስክር፣ “ኦንሊይ ጂሰስ”፣ አድቬንቲስት፣ ሙሉ ወንጌል፣ …. በሚሉና ሐይማኖት በፈጠራቸው የተለያዩ ቅጥሮች ውስጥ ሆነውና በተለያየ አስተምህሮ ተከፋፍለው በጎሪጥ የሚተያዩትን ወንድሞቼን ደግሜ አንድ ሌላ ጥያቄ ልጠይቅ፡- ከእናንተ መካከል ክርስቶስና ጌታ የተባለው ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ፣ ደግሞም ይህ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ በመስቀሉ ላይ የከፈለውን ቤዛ፣ ሞቱንና ትንሣኤውን የማያምን ማነው??? በእርግጥ ልክ እንደሐዋርያቱና ከላይ እንዳየነው ኢትዮጵያዊ እምነታችሁ ከዚህ እግዚአብሔር ራሱ ከመሠረተው የእምነትና የሕይወት መሠረት ከጀመረ፣ አንዳችሁ ሌላኛችሁን “አንድ እምነት” ከተባለው ክርስትና ውጪ አድርጋችሁ እንድታዩ፣ ደግሞም እንድትከፋፈሉና እንድትከፋፉ፣ እንድትበታተኑና እንድትለያዩ አዚም ያደረገባችሁ ማነው???

“አንድ እምነት” የተባለው ክርስትና የሚጀምረው የእግዚአብሔርን ልጅ በማመን ነው። ይሄ እምነት ደግሞ መንፈስ ከሆነው እግዚአብሔር ይወልደናል። “ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ከእግዚአብሔር ተወልዶአል” የሚለውን ሐዋርያዊ ትምሕርት ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ማመካኘት (Reasoning) እንቀበለው ዘንድ ግድ ነው። ከመንፈስ የተወለደ ደግሞ መንፈስ ነው። ክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በማመን ዳግመኛ የተወለድነውም ሆነ በዚህ ዳግመኛ ልደት በአንድ ተስፋ ወደ አንድ አካል የተጠመቅነው በዚሁ በተወለድንበት አንዱ መንፈስ ነው። አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት፣ አንድ አካል፣ አንድ መንፈስ፣ አንድ ጌታ፣ አንድ አምላክ የሁሉም አባት ነው ያለው። ታድያ የእምነታችንና የሕይወታችን መሠረት በሆነው ሕያው ዓለት - በአንዱ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መቆማችንን፣ “የማይጠፋ” ከተባለው ከአንዱ ዘር መወለዳችንን፣ በአንድ የዘላለም ሕይወት ተስፋ መጠራታችንን፣ አንዱን መንፈስ ጠጥተን በአንዱ መንፈስ ወደ አንድ አካል መጠመቃችንን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ልናመልከው የተገባውም “አንድ አምላክ የሁሉም አባት” የተባለውን እግዚአብሔርን መሆኑን እንዳናይ ማን አዚም አደረግብን????

ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት፣ የይሖዋ ምስክር፣ “ኦንሊይ ጂሰስ”፣ አድቬንቲስት፣ ሙሉ ወንጌል…. መባባላችን ባይከፋም፣ እነዚህ ስሞች የመቀባበላችን ወይም የመለያየታችን ምክንያት መሆናቸው ግን በእጅጉ የሚያሳዝን ነው። ደግሞም እርስ በእርሳችን በክርስቶስ እንዳንተያይ ሐይማኖት በዓይናችን ፊት የሰፋቸው መጋረጃዎች፣ የገነባቸው ግንቦች ሆነው እርስ በእርሳችን ላንያያዝ ተከፋፍለን መቆማችን፣ አንዳችን በአንዳችን ላይ ጣታችንን እየቀሰርን፣ እያወገዝንና እየተሰዳደብን በቅናትና በክርክር እድሜአችንን መጨረሳችን፤ ያኔ በመጀመሪያው ክ/ዘመን እንደነበሩትና “አንተ የጳውሎስ፣ እኔ ደግሞ የአጵሎስ፣ እሷ ደግሞ የኬፋ….” እየተባባሉ እንደተለያዩት ሥጋውያኑ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መሆናችንም አይደል??? ያኔስ እግዚአብሔር የላከው ጳውሎስ “ክርስቶስ ተከፍሎአልን?” በማለት በአንዲት ቃል መልሶ ሰበሰባቸው። ዛሬስ????


“እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፣ ሙሉ ሰውም ወደመሆን፣ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፣ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።” (ኤፌ.4፡11-13)


               

No comments:

Post a Comment