Sunday, November 4, 2012

እግዚአብሔርን መምሰል - የመዳናችን ፍጻሜ!!!!!


ሰው “ዳነ” የሚባለው መቼ ነው??? ይህን ጥያቄ አጭርና ግልጽ በሆነ መንገድ ስንመልስ፣ ሰው “ዳነ” የሚባለው አስቀድሞ በእግዚአብሔር ወደተፈጠረበት መልክና ምሳሌ ሲመለስ ነው። ይሄ ደግሞ የቀናት ወይም የዓመታት ውጤት ሳይሆን በዘመናት መካከል በሚከናወን መንፈሳዊ ሂደት (Spiritual Process) የሚፈጸም የእግዚአብሔር ድንቅ ሃሳብ ነው። ይሄ ሃሳቡም እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ!! እደግመዋለሁ፤ ለሰው ሁሉ ያለውና የማይለወጥ ብቻ ሳይሆን ሳይፈጸም የማይቀር ዘላለማዊ ሃሳቡ ነው። ይህንንም ሃሳቡን ነው ገና በማለዳ "ሰውን በመልካችን እንደምሳሌአችን እንፍጠር" በማለት የገለጠው። ምንም እንኳን የመጀመሪያው ሰው ምሉዕና ፍጹም በሆነ መልኩ ባይሆንም በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ እንደተፈጠረና፣ ነገር ግን በሰይጣን ተንኮል ተታልሎ ከዚህ መልክ እንደወደቀ መጽሐፍ ቢነግረንም ቅሉ፣ እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ እንደምሳሌው የመፍጠርና የማግኘት ዓላማው በሰይጣን ሴራ ተበላሸ ወይም ከሸፈ ማለት አይደለም። ይልቁንም ተገለጠ እንጂ!!!!

እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር በክርስቶስ ባቀደው ዘላለማዊው ሃሳቡ መሠረት፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ወንጌል ለዚህ የከበረ የእግዚአብሔር ዓላማ ቀድመው የተጠሩ (The called – out = Church)
ዛሬ በዚህ ሕይወት - በሥጋ ሳሉ በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስና በጸጋው አሰራር ወደዚህ መልክና ምሳሌ ለመድረስ እየተሰሩና እየተዘጋጁ ነው። ከእነዚህ ኣማኞች መካከል በሥጋ ይኖሩ ዘንድ እግዚአብሔር በሰጣቸው ዘመን ፍጹም በሆነ መታዘዝ ወደዚህ የከበረ የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የሚደርሱቱ “የእግዚአብሔር መንግስት ወራሾች” ወይም “በኩራት” ወይም “ድል ነሺዎች” ይባላሉ። እነዚህ ድል ነሺዎች ከአጠቃለዩ የሰው ልጆች ቁጥር አንጻር ብቻ ሳይሆን፣ በቤተክርስቲያን ካሉ አማኝ ወንድሞች መካከል ሲታዩ እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። ለዚህም ነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “ታናሽ መንጋ” ብሎ የጠራቸው።

“የክብር
አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው” (ኤፌ.1፡17-19)

ዛሬ በዚህ ዘመን ከሚኖሩ የሰው ልጆች ሁሉ መካከል በክርስቶስ ወንጌል እንደተጠሩ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን ራሳችንን ስናይ፤ የተጠራነው የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ ፍጹም ሙላት ለመድረስ ነው። ርስታችንም እርሱ ነው። በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን መምሰል!!! መዳናችንም “ተፈጸመ!” የሚባለው እዚህጋ ስንደርስ ነው። በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን ስንመስል!!!!  እግዚአብሔር ማንን ይመስላል?? የማይታየው ባህሪው ደግሞም አምላክነቱ በተፈጠሩት ሁሉ ግልጥ ሆኖ እንደታየ መጽሐፍ ይመሰክራል። ወንድማችን ደረጀ ከበደ በመዝሙሩ እንደተቀኘው፡- የጠራው ሰማይ፣ በጠራው ሰማይ ላይም የተበተኑት የማይቆጠሩ ከዋክብት፣ የተራሮች ግርማ፣ የውቅያኖስ ስፋትና ጥልቀት... እነዚህና ሌሎች ሊቆጠሩ የማይችሉ የእግዚአብሔር  ፍጥረታት ሁሉ የእርሱን ጥበብ፣ እውቀትና ማስተዋል፣ ኃይልና ችሎታ፣ ቸርነትና ደግነት፣ ጽድቅና ቅድስና፣ ርህራሄና ፍቅር፣ ፍርድና ምሕረት፣ .... የሚሰብኩ መጻሕፍት ናቸው።

ነገር ግን የዕብራውያን ጸሐፊ እንደመሰከረው እግዚአብሔር የዘመናት ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ የክብሩ መንጸባረቅና የባህሪው ምሳሌ በሆነው አንድያ ልጁ በኩል ፍጹም ልዩ በሆነ መንገድ ራሱን ገልጦአል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔን ያየ አብን አየ” በማለት የተናገረውም ለዚህ ነው። የእግዚአብሔር ዓላማም እነዚህን በክርስቶስ የተገለጡና የታዩትን ባህሪያቱን፤ ማለትም፡- ጥበቡን፣ እውቀትና ማስተዋሉን፣ ኃይልና ችሎታውን፣ ቸርነትና ደግነቱን፣ ጽድቅና ቅድስናውን፣ ርህራሄና ፍቅሩን፣ ፍርድና ምሕረቱን፣ ሰላሙን፣ በጎነቱን ... በሰው ሁሉ ውስጥ ማግኘት ነው። በዚህ ዘላለማዊ ሃሳቡም መሰረት፣ ዛሬ እኛ በምድር ከሚኖሩት አሕዛብ ሁሉ መካከል ይህን ባህሪውን ለመካፈል ብቻ ሳይሆን በሕይወት አካሄዳችንም በመግለጥ ለእግዚአብሔር ክብርን ለማምጣት ተለይተን ተጠርተናል። “የተጠሩ ብዙዎች የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸው” ተብሎ እንደተጻፈው፤ መዳናችን ፍጹም ሆኖ ከታመኑትና ከተመረጡት ወገኖች መካከል መቆጠር የምንችለው ግን፣ ዛሬ በተጠራንበት መጠራት እንደሚገባ እየተመላለስን በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን ወደመምሰል ማደግ ከሆነልን ብቻ ነው።

“እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ። እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ። እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤ በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፤ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” (ኤፌ.4፡17-24)

ይህን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነውንና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲስ ማንነት ፈጽመን መልበሳችን ነው የመዳናችን ዋስትና! ይሀም አዲስ ልብስ የመንግሥቱ ግብዣ እድምተኞች፣ የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም “ዜጎች” ያደርገናል። እዚህጋ ካልደረስን ወይም ይህን አዲስ ልብስ ፈጽመን ካለበስን በቀር አፋችንን ሞልተን “ድነናል!” ማለት አንችልም። የመዳናችን ፍጻሜ እግዚአብሔርን መምሰል ነውና!!! እግዚአብሔር በሰጣቸው በዚህ ዘመን ይህን በክርስቶስ የሆነውን አዲስና የከበረ ማንነት ፈጽመው የለበሱ ክርስቲያኖች ድል ነስተዋልና “በሁለተኛው ሞት አይጎዱም!” ነገር ግን ደግሞ የተጠሩት ብዙዎች የታመኑት ግን ጥቂቶች እንደመሆናቸው መጠን፣ በዚህ ሕይወት ድል ያልነሱትና ያልታመኑት ብዙዎች ግን በውጭ ወዳለው ጨለማ መጣላቸው አይቀሬ ነው። ለምን ቢሉ አሮጌውን ልብስ ለብሶ የመንግሥቱ ግብዣ እድምተኞች፣ የቅድሰቲቱ ከተማ “ነዋሪዎች” መሆን ስለማይቻል!!! በውጭ ያለው ስቃይና መከራ፣ ሐዘኑና ጥርስ ማፋጨቱ፣ በዲን የሚቃጠለው እሳት….. የቅጣቱና የፍርዱ ኃይለኝነት የተገለጠባቸው መንገዶች ናቸው። በውጭ መጣልና በዚህ ሁኔታ ውስጥ መገኘት የእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ ነውና እጅግ አስፈሪ መሆኑ የማይካድ ነው። ከዚህም ፍርድ በታች ላለመገኘት አማራጩ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራስን መዳን ለመፈጸም ክርስቶስ በሚሰጠን ኃይልና በጸጋው ጉልበት መጋደል ነው። የእግዚአብሔርን ጽድቅና ቅድስና፣ ይኸውም በክርስቶስ ያለውን መልኩና ምሳሌውን በፍርድና በቁጣው ከመካፈል ይልቅ፤ በጸጋው ትምህርትና በምሕረቱ ብዛት መካፈል ዛሬ ለእግዚአብሔር ልጆች ብቻ የተሰጠ
የእግዚአብሔር የአምላካችንና የአባታችን ውዴታና ቸርነት ነው።    

No comments:

Post a Comment