Sunday, October 21, 2012

“የዘላለም ፍርድ” 2


“ያመኑትም ያላመኑትም ፍጻሜ በሌለው የፍርድ እሳት ይቀጣሉ”

በዚህ የዘላለም ፍርድ ጉዳይ ላይ በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ ብቻ “ዩኒቨርሳሊዝም” የሚባለውን ሳንጨምር ቢያንስ አራት አይነት አስተምህሮዎች አሉ። እነርሱም፡-

1.
አርሚኒያኒዝም፡- እግዚአብሔር ፍቅር ነው። ከዚህም የተነሳ የሰው ልጆችን ሲፈጥር ዓላማው ለስቃይ አልነበረም። ነገር ግን ሰይጣን የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ሲያስት ኃጢአት በኃጢአትም ምክንያት ሞት ወደ ዓለም ገባ። በዘመናት ሁሉ መካከል እግዚአብሔር የሰውን ልጆች ከዚህ ጥፋት ለማዳን የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል። እንዲያውም ልጁን ለመስቀል ላይ ሞት አሳልፎ የሰጠው እንኳን ሰዎችን ከዚህ ጥፋት ለማዳን ካለው ፍላጎቱ የተነሳ ነው። በእነዚህ በሁለት ሺኅ ዓመታት ውስጥ ወንጌል የተዳረሰው እጅግ በጣም ጥቂት ለሚሆኑ የሰው ልጆች ብቻ ነው። ነገር ግን ሌሎች ጥቂት ሺህ ዓመታት ቢጨመሩ ቤተክርስቲያን ያላትን ኃይልና አቅም ሁሉ አስተባብራ ወንጌልን ለዓለም ሁሉ ማዳረስ ትችላለች። በዚህም እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ፍቅር ሰዎች እየተረዱ፣ የመዳን ዕድላቸውን እየተጠቀሙና ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ እየወጡ ይመጣሉ። ወንጌል ያልሰሙትን እና እንዲሁም ሌሎች ብዙ የዋሃን ሰዎችን ካለማወቃቸው የተነሳ እግዚአብሔር ይቅር እንደሚላቸው እናምናለን።

2. ”ካልቭኒዝም”፡-  እግዚአብሔር በጥበብ የተሞላ አምላክ በመሆኑ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለውን ሁሉ ያውቃል። በመሆኑም የዓላማው ፍጻሜ የሚሆነውና በዘላለም ሃሳቡ መሠረት የሚያድናቸው አስቀድሞ የወሰናቸውን ጥቂት አማኞች ብቻ ነው። እነዚህ አማኞች አስቀድሞ የተመረጡ በመሆናቸው ለዘላለም ይድናሉ። የተቀሩት ሁሉ ግን አስቀድሞም ቢሆን ለጥፋት የተመረጡ በመሆናቸው በዘላለም እሳት ውስጥ ተጥለው ይቀጣሉ። አሁንም ብዙዎች በዚህ የማይጠፋ እሳት ውስጥ ተጥለው በስቃይና በሰቆቃ ውስጥ ከመሆናቸውም በላይ ከዚያ የመውጣት ተስፋም የላቸው።  

 3. የይሆዋ ምስክሮች፡- ሰዎች ሁሉ የትንሳኤ ተስፋ አላቸው። በዚህ የመጀመሪያ ሕይወታቸው ወንጌልን ያላመኑና ያልተቀበሉ ሁሉ በሚመጣው ትንሳዔ ወንጌል ስለሚሰበክላቸው የመዳን ተስፋ አላቸው። በዚህኛውም ጊዜ ከአመጻቸው ያልተመለሱ ግን ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጽንፈ ዓለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳሉ። ሕልውናም አይኖራቸውም። ምክንያቱም ሁለተኛው ሞት የተባለው የገሃነም ፍርድ የሚያመለክተው በዚያ ለዘላለም መሰቃየትን ሳይሆን ፈጽሞ ከሕልውና ውጪ መሆንን ስለሆነ። ይህም ከእግዚአብሔር አምላካዊ ባህርዩ ጋር የሚስማማ ነው።   

4. ፈንዳሜንታሊዝም፡- በዚህ ሕይወትና አሁን በሥጋ ያሉ ሰዎች ብቻ እውነተኛ ንስሐ ከገቡና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደግል አዳኛቸው አድርገው ከተቀበሉ ለዘላለም ይድናሉ። ነገር ግን የተቀሩት (ወንጌል የሰሙትም ያልሰሙትም) ሁለተኛ ዕድል የሚባል ነገር ስለሌለ ምሕረትና ተስፋ ወደሌለው የገሃነም እሳት ይጣላሉ፤ በዚያም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሰቃያሉ።
ይሄኛው ማለትም የፈንዳሜንታሊዝም አስተምህሮ አብዛኛው የክርስትናው ዓለም የተቀበለው ሲሆን የትምሕርቱ ምንጭ የሆነችው የሮማ ካቶሊክ ለረጅም ዘመናት በዓለም ሁሉ ላይ ከነበራት ጠንካራ ተጽዕኖ የተነሳ ስር የሰደደና በቀላሉ ሊታረም የማይችል አደገኛ ስህተት ነው። ምንም እንኳን በዚህኛው አስተምህሮ መሰረት “ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው ያመኑና የተቀበሉ ለዘላለም ይድናሉ” ቢባልም፤ እንደገና በዚሁ ተቃራኒ ከነዚህም አማኞችም መካከል በሕይወት ሳሉ ከአሮጌው ማንነታቸው ፈጽመው ነጻ ያልወጡና ድል ያልነሱ ክርስቲያኖች ልክ እንዳላመኑት ወገኖች ሁሉ ወደ እሳት ባህር እንደሚጣሉና በዚያም ከዘላለም እስከ ዘላለም እንደሚሰቃዩ ይታመናል። ለዚህም ነው ለዚህኛው መልዕክቴ እንደ ርዕስ የመረጥኩት “ያመኑትም ያላመኑትም ፍጻሜ በሌለው ፍርድ ይቀጣሉ” የሚለውን የወገኖቼን አስተምህሮ የሆነው።

ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ከሳራውን የማይቈጥር ማን ነው?ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት፥ ሊደመድመውም ቢያቅተው፥ ያዩት ሁሉ። ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ።” ሉቃ.14፡28-30

የዘላለምን ፍርድ በሚመለክት እነዚህ ከላይ ያየናቸው ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችና አስተሳሰቦች ሁሉ የሚያሳዩን ብዙዎቹ ወገኖቻችን ሳያውቁ የሚያመልኩት አምላክ ዓለምን ሳይፈጥር አስቀድሞ ‘ተቀምጦ’ ከሳራውን ያልቆጠረ፣ ምን ሊሰራ እንዳሰበ የማያውቅ፣ እቅድና ዓላማ የሌለው፣ ጥቂት ዕቅዶች ቢኖሩት እንኳን እነርሱን ለመፈጸም የማይችል ዓቅመ ቢስ “አምላክ” እንደሆነ ነው። በተለይም በአራተኛው ተራ ቁጥር ላይ የምናየውን የፈንዳሜንታሊዝም አስተምህሮ የሚያራምዱ ወገኖች (ትኩረቴ በተለይ በእነርሱ ላይ የሆነው አሁን የሚሰሙኝ እነርሱ ስለሆኑ ነው) ቁጭ ብለውና ረጋ ብለው ሊያስቡት የሚገባ ነገር አለ። ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን ከእግዚአብሔር ዳግመኛ ሲወለዱ፣ የተወለዱት “ከማይጠፋው ዘር” ነው። ይሀም የማይጠፋ ዘር በእነርሱ ያለው ክርስቶስ ነው። እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል በእያንዳንዳቸው ሕይወት የጀመረው ሥራ አንድ ቦታ ላይ ሲደርስ የሚቆም ወይም የሚበላሽ፣ ተበላሽቶም የሚጣል አይደለም። ይህ ደግሞ የሆነው ከእነርሱ ማንነትና ብቃት ሳይሆን ሥራውን የጀመረው እግዚአብሔር በመሆኑ ነው። “በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና” እያለ ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩትን ክርስቲያኖች ያበረታታ እንደነበር የምናነበው፣ የሚያመልከውን አምላክ በሚገባ ያውቀው ስለነበር ነው።

ከሰዎች ሁሉ ይልቅ በተለይ በተለይ እግዚአብሔር በአንድያ ልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ ደም ዋጅቶ የራሱ እንዳደረጋቸው የሚመሰክሩ ወገኖች፣ በሕይወታቸው ላይ ከሚታይና ከሚገለጥ የሥጋ ድካም የተነሳ ከዕለታት አንድ ቀን ከእግዚአብሔር እጅ ተቆርጠው ለዘላለም እንደሚጣሉና በዚያው ለዘላለም እንደሚጠፉ ሲያስቡና ሲያምኑ ማየት እጅግ በጣም ልብ ይሰብራል። እውነት ነው፣ ዳግመኛ የተወለድነውና በክርስቶስ ደም የተዋጀነው እንደ ልባችን እየፋነንን ልንኖር አይደለም። እንደ እውነተኛ ክርስቲያኖች የምንኖረው በእኛና ለእኛ ሳይሆን በክርስቶስና ለክርስቶስ ነው። እግዚአብሔርም የጠራን ለእርኩሰት ሳይሆን በቅድስና እና ለቅድስና ነው። ስለዚህም የየራሳችንን ዕቃ (ማንነት) በቅድስና እና በክብር እንድናገኝ፣ መዳናችንንም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንድንፈጽም፤…. አለበለዚያ ግን እግዚአብሔር የሚበቀልና የሚቀጣም አምላክ እንደሆነ በመጽሐፍ በግልጽ ተነግሮናል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ስለእውነተኛው የወይን ግንድ የተናገረው ቃል የሚያመለክተንም ይሄንኑ ነው፡- “እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል ያቃጥሉአቸውማል።” ዮሃ.15፡5-6

እዚህ ላይ ግን በጥንቃቄ የምንመለከተው ነገር አለ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሌላ ስፍራ “አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” በማለት እንደተናገረ እናነባለን። (ዮሃ.6፡37) “በእኔ የማይኖር እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ==== ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም።” እግዚአብሔር በተለይም በክርስቶስ እምነት ዳግመኛ በወለዳቸው ልጆቹ ላይ በሚፈጽመው ቅጣት፣ ቁጣና ፍርድ፣ በፍርዱም ውስጥ ያለውን ዓላማውን በመረዳት ወደ ትክክለኛው የእግዚአብሔር ሃሳብ ለመድረስ እነዚህን ሁለት የጌታ ቃሎች ማስታረቅ ይጠበቅብናል።

በዘመኑ በአሕዛብ ዘንድ እንኳን የማይፈጸም ኃጢአት በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መካከል መፈጸሙን ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፈላቸው መልእክት ውስጥ ተጽፎ እናነባለን። ከዚህም የተነሳ ዝሙት የሚባለውን ክፉ ኃጢአት የሰራውና የአባቱን ሚስት ያገባው ሰው ከመካከላቸው እንዲወገድ ጳውሎስ ከሩቅ ሆኖ ያወጣው የፍርድ ቃል ይህ ነበር፡-
“እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን፥ መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው።”( 1ቆሮ.15፡3-5)  

ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል መወገዱ፣ ወደ ውጭ መጣሉ፣ ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን ታልፎ መሰጠቱ…. ጽድቅ የተትረፈረፈበት ትክከለኛ የእግዚአብሔር ፍርድ ነው። መንፈሱ በጌታ ቀን መዳኑም ጥበብና ማስተዋል የሞላው፣ ዕቅድና ዓላማ የነበረው የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ነው። ወደ ውጭ የተጣለው ለዘለላለም ፈጽሞ ሊጠፋ አልነበረም። ምክንያቱም፤ ያለው ሸክላውን እንደወደደ አድርጎ መልሶ ሊሰራ በሚችለው “ሸክላ ሰሪ” እጅ ነውና!!!!!!  


No comments:

Post a Comment