Monday, July 30, 2012

ወንጌል የረገማት ምድር በወንጌል ትባረካለች!!!

መቼስ እኛ ኢትዮጵያውያን ራሳችንን ከዓለም የለየንባቸው ምክንያቶች አጅግ ብዙ ናቸው። ሌላው ሕዝብ የራሱ የሆነ ወግና ባህል የሌለው ይመስል በወጎቻችንና በባህሎቻችን ያለመጠን እንመካለን። በሌላው ዓለም ተራራና ሸለቆ፣ ወንዝና ተረተር፣ ሜዳና ኮረብታ…. የሌለ ይመስል በመልክዓ ምድራችን ሳይቀር እንኮፈሳለን። …. ዓለምንና ሞላዋን የፈጠረው እግዚአብሔርስ ቢሆን፣ ከሌሎቹ አገሮች ይልቅ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የተለየ አጀንዳ፣ የተለየ እንክብካቤ፣…. የተለየ ጉዳይ እንዳለው እናስባለን። የብሉይ ኪዳኑ የእግዚአብሔር ሕዝብ እስራኤላውያን እንደነበሩ ሁሉ፤ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ያደረገው አዲስ ኪዳን በዓለም ከሚኖሩ ሕዝቦች ይልቅ ከእኛ ከኢትዮጵውያኑ ጋር እስኪመስል ድረስ “የክርስቲያን ደሴት” የሚል “የክርስትና ስም” ለራሳችን አውጥተናል።

ሰሞኑን በአንድ የውጭ አገር ኤምባሲ ቢሮ ውስጥ ድንገት የተገናኝን ስድስት የምንሆን ኢትዮጵያውያን ያደረግነው ውይይት ነው ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ። ከስድስታችን ውስጥ ሁለቱ ከሃያ ዓመታት በፊት ዩኒቨርስቲ ውስጥ አብረው ይማሩ የነበሩና ይኖሩበት ከነበረው “የባዕድ ምድር” ከረዥም ጊዜ በሗላ ተመልሰው በድንገት እዚያው ቢሮ ውስጥ የተገናኙ ጓደኛሞች ናቸው። የሌሎቹን ጓደኞቻቸውን ስም እየጠሩ ያሉበትን ይጠያየቃሉ፤ በጣም በሚገርም ሁኔታ ሁሉም ከኢትዮጵያ ውጪ ናቸው። “ከሁሉ በላይ እኔን የሚያበሳጨኝ” አለ አንደኛው፤ “ከሁሉ በላይ እኔን የሚያበሳጨኝ ፊደል ቆጥሬ ዲግሪዬን እስከምይዝ ድረስ በነጻ ያሰተማረችኝን አገሬን መጥቀም ያለመቻሌ ነው።”

ከዚህ ወንድም የቁጭት ንግግር ቀጥሎ፣ ኢትዮጵያ ለአያሌ ዘመናት በድህነትና በችግር እየማቀቀች ባለችበት ሁኔታ ውስጥ፣ አገራቸውን በእጅጉ ሊጠቅሙና የሕዝባቸውን ኑሮ ሊለውጡ የሚችሉ አያሌ ኢትዮጵያውያን ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ለየባዕድ አገሩ በዶላር የሚሸጡበትን ምክንያት እየተነተነና የአገሪቱን የፖለቲካ ሥርዓት እየኮነነ ውይይቱ ቀጠለ። በዚህ መኸል አንዲት እህት፡- “እኔ ግን ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ላለው መከራና ችግር ምክንያቱ የፖለቲካ ሥርዓቱ ብቻ አይመስለኝም” አለች። ሌላ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ የጓጉ ወደ አሥር የሚጠጉ አይኖች ልጅቷ ላይ አፈጠጡ። “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴትና ቅድስት አገር ከመሆኗ የተነሳ ዲያብሎስ ያመጣብን ፈተና ነው” አለች። የሁሉም ሰው ስሜት ሟሸሸ። አሁን እኔን የሚመለከተኝ ርዕስ በመከፈቱ ጉሮሮዬን ጠራረኩና- “አይደለም የኔ እሕት፤ ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው” ከማለቴ እነዚያ አይኖች በሙሉ እኔ ላይ አፈጠጡ። “በምድራችን ላይ ዘመናትን ላስቆጠረው ችግርና ጉስቁልና ምክንያቶቹ፣ ጠንክረን ካለመስራታችን ጋር ተዳምሮ፣ በክርስትና ስም የሚደረገው ባዕድ አምልኮ ያመጣብን መርገም ነው” አልኩ ፍርጥም ብዬ።

ለመላእክትና ለሰዎች በተሰጡት ሰላሣ ቀናት ውስጥ የሚከበሩት በዓላት፣ ወደመላእክትና ወደሰዎች የሚደረጉት የልመናና የምልጃ ጸሎቶች፣ ስለ መላእክትና ስለሰዎች የተጻፉትና ‘በየእለተ ቀናቸው’ የሚነበቡት ድርሳናት፣ ለመላእክትና ለሰዎች ምስል የሚደረጉት ስግደቶች፣ ለመላእክትና ለሰዎች የሚቀርቡት የምስጋና እና የውዳሴ መዝሙሮች፣ በመላእክትና በሰዎች ስም የተሰሩት ሕንጻዎችና ሕንጻዎቹም የሚታጠኑት የዕጣንና የሰንደል መዓዛ፣ በመላእክትና በሰዎች ስም ለተሰየሙ “ታቦታት” የሚቀርበው እልልታና ዝማሬ፣ ሽብሸባና ውዳሴ፣ መስዋእትና ስለት፣ አምልኮና ስግደት….. የአገራችንን ክርስትና ለየት ያለና “ቀለመ - ደማቅ” አድርገውት “ነጫጭ ቱሪስቶችን” ወደ አገሪቱ ከመጥራታቸው ቀጥሎ፤ የኢትዮጵያውያኑ እጆች ወደ እግዚአብሔር ሳይሆን ወደ “ነጫጮቹ ለጋሽ አገሮች” እንዲዘረጋ ያደረጉና፣ አገራቸውን በእጅጉ ሊጠቅሙና የሕዝባቸውን ኑሮ ሊለውጡ የሚችሉ አያሌ ኢትዮጵያውያንን በዓለም ዙሪያ ሁሉ የበተኑ የምድሪቱ መርገሞች ናቸው።

ደግሜ ልናገር!! ‘ኢትዮጵያ’ ተብላ የምትጠራው ምድር ከላይ በተዘረዘሩትና በክርስትና ስም ከሚደረጉት ባዕድ አምልኮዎች የተነሳ፣ የእግዚአብሔር እጅ የከበደባትና ከእርግማን በታች የወደቀች ምድር ነች። ከዚህ እርግማን ነጻ የሚያወጣት ደግሞ በአጭሩ የክርስቶስ ወንጌል ነው። ክርስትና የምንለው ክርስቶስ የመሠረተውንና ሐዋርያት የሰበኩትን እምነት ከሆነ፤ “የእምነታችን ጀማሪና ፈጻሚ” የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማራቸው ትምሕርቶችም ሆነ እግር - ከእግር የተከተሉት ሐዋርያቱ በሰበኳቸው ወንጌላትና በጻፏቸው መልእክቶች ውስጥ፤ ከላይ እንዳየናቸው ያሉ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የምናገኛቸው ክርስቲያናዊ “ልማዶች” የሉም። እንግዲያውስ ከእውነተኛው ክርስትና አንጻር “መጤ” የሆነውም ሆነ በምንፍቅና ሊፈረጅ የሚገባው፣ ደግሞም የምድሪቱና የሕዝቧ መርገም ምክንያት፣ ይኸው በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት እግሩን አንፈራጦ የሚገኘው በክርስትና ስም የሚደረገው “ባዕድ አምልኮ” ነው።

በሌላው ዓለም እንደሚገኙት ሕዝቦች ሁሉ ወደ እውነት የሚመራቸውን የክርስቶስ ወንጌል ካለመስማታቸው ወይም ሰምተው ካለመቀበላቸውና ካለማመናቸው የተነሳ፤ በፈጣሪ ፈንታ የተፈጠሩትን የሚያመልኩ ሰዎች በኢትዮጵያም ውስጥ በብዛት ይገኛሉ። እነዚህም ሰዎች አወቁትም - አላወቁትም ለራሳቸውና ለምድራቸው የመርገም ምክንያቶች ናቸው። ነገር ግን በአንድ እጃቸው ነጻ የሚያወጣውን ወንጌል፣ በሌላ እጃቸው ደግሞ “ልዩ ወንጌል”ይዘው፤ በአንዱ ምላሳቸው ክርስቶስን፣ በሁለተኛው ደግሞ መላእክትንና ሰዎችን የሚሰብኩት፣ ባለማወቃቸው ወይም ባለማመናቸው ምክንያት ዛፍና እንሰሳ የመሳሰሉትን ከሚያመልኩት ሰዎች ይልቅ በራሳቸውም ሆነ በምድራቸው ላይ የከፋ ፍርድንና መርገምን በሚያመጣ ባእድ አምልኮ ውስጥ ናቸው።

በቀደመው ኪዳን በእግዚአብሔር በራሱ ተሰጥቶ የነበረውን የግርዘት ሕግ ወደ አዲሱ ኪዳን የጸጋ ሥርዓት ሊቀላቅሉ የነበሩትን እነ ኬፋን ፊት ለፊት የተቃወመው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለገላትያ ክርስቲያኖች በጻፈው መልክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውስጥ፡- “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፣ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን!” እያለ መላእክት እንኳን ሳይቀሩ ሌላ ወንጌል ቢሰብኩ ከመርገም እንደማያመልጡ ካስጠነቀቀ፤ እንኪያስ! በሕጉና በነቢያት ያልተጻፈውን፣ በክርስቶስ ወንጌል ያልተሰበከውን እንዲህ ያለ እንግዳ ትምሕርት ወደ ክርስትና ጨምረው፣ ዛሬም ድረስ ያለ እፍረት እየሰበኩና እያስተማሩ፣ እያሳቱና እየሳቱ የክርስቶስን ወንጌል የሚያጣምሙት የሐይማኖት ልጆች፣ ምድራቸውም ሆነች ራሳቸው ከዚህ ሐዋርያዊ እርግማን እንዴት ሊያመልጡ ይችላሉ?? በጭራሽ አይችሉም!!!!!

ስለዚህ ወንጌል የረገማትን ይህችን ምድር ከዚህ እርግማን ነጻ ሊያወጣት የሚችለው ያው የረገማት ወንጌል ብቻ ነው። የወንጌሉ ባለቤት የሆነውና ከሰማይ በታች ያሉ ሰዎች ሁሉ (ኢትይጵያውያንም ሳይቀሩ) በእምነት እየጠሩ ይድኑበት ዘንድ የተሰጣቸው አንድ ስም ነው። ክርስቶስና ጌታ የሆነው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ስም!!! ይህ በምድርም ሆነ በሰማያት ከሚጠሩት ስሞች ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያለው የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በምድሪቱ ሰማያት ላይ ብቻውን መንገስ፣ ብቻውን መወደስ፣ ብቻውን መጠራት፣…. ሲጀምር፤ በኢትዮጵያ ምድር ላይ እውነተኛው የእግዚአብሔር ክብር ይመጣል። ብዙዎች ከጨለማው ገዢ እሥራት ማምለጥ ይሆንላቸዋል፣ የምድሪቱ መርገም መሰባበር ይጀምራል፣ በሥፍራ ሁሉ የተበታተኑ፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ለባዕዳን አገሮች እየሸጡ ያሉና ሕዛባቸውንና ምድራቸውን በእጅጉ ሊጠቅሙ የሚችሉ አያሌ ኢትዮጵያውያን ወደ ምድራቸው መመለስ ይጀምራሉ። ከዚህም በላይ፤ ኢትዮጵያውያንም የወንጌል ትሩፋት የሆነውንና በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው እምነት በኩል ብቻ ሊገኝ የሚችለው ሰማያዊ በረከት ተካፋይ ይሆናሉ። እግዚአብሔር ሆይ!! በዚህ በእኛ ዘመን በምድራችን ላይ ይህን ለማድረግ ቆርጠህ ስለተነሳህ ተመስገን!!! በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለዘላለሙ አሜን!!!!!                     

Monday, July 16, 2012

እግዚአብሔር በአንድያ ልጁ ወደ ምድር ወረደ - ብዙ ልጆችንም ይዞ ወደ ሰማይ አረገ!!!

“የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ሕዝቡ ነው፤ ያዕቆብም የርስቱ ገመድ ነው። በምድረ በዳ በጥማት፣ የነፋስ ጩኸትም በሞላበት ውድማ አገኘው፤ ከበበው ተጠነቀቀለትም፤ እንደ አይን ብሌን ጠበቀው። ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ፣ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ፣ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፣ በክንፎቹም አዘላቸው። እግዚአብሔር ብቻውን መራው፤ ከእርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም።” (ዘዳግም.32፡9-12)  

በቀደመው
ዘመን በግብጽ ምድር የነበረውን የሕዝቡን መከራ በእውነት ያየ፣ ጩኸታቸውንም የሰማና ሥቃያቸውንም ያወቀ  እግዚአብሔር …  የባርነት ቀንበራቸውን ሰብሮ ከግብፃውያን እጅ ያድናቸው ዘንድ፣ ከጠላት እጅ አምልጠውና ከመከራቸው አርፈው በተትረፈረፈ በረከት ወደሚኖሩበት - ወተትና ማር ወደምታፈሰው፣ ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ ምድር የሚወስዳቸውን መንገድ ይመራቸው ዘንድ ወረደ። (ዘፀአት3፡8) …. እስቲ እዚህ ላይ አንዲት ጥያቄ እንጠይቅ፡- የሕዝቡን መከራ በእውነት ያየ፣ ጩኸታቸውንም የሰማ፣ ሥቃያቸውንም ያወቀ እና መንፈስ የሆነው እግዚአብሔር ወደ ግብፅ እንዴት ወረደ???

“አሁንም ና፣ ሕዝቤን የእሥራኤል ልጆች ከግብጽ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ። ሙሴም እግዚአብሔርን፡- ወደ ፈርዖን የምሄድ የእሥራኤልንም ልጆች ከግብጽ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? አለው። እርሱም፡- በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም እንደላክሁህ ምልክትህ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብጽ ባወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ ለእግዚአብሔር ትገዛላችሁ አለ።” (ዘፀአት3፡ 10-12)


በግብጽ ምድር ሳለ በወንድሞቹ ላይ የደረሰውን መከራ ተመልክቶ ጥቃታቸውን ለመከላከል የገዛ ጉልበቱንና ብርታቱን በመጠቀም ግብፃዊውን የገደለው ሙሴ፤ ከፈርዖን ፊት ኮብልሎና እጅግ ትሁት ሆኖ የአማቹን የዮቶርን በጎች በሚጠብቅበት በምድያም ምድር ነበር እግዚአብሔር ለዚህ የከበረ ተልዕኮ የጠራው። በግብጽ ሳለ የነበረው ጉልበቱና ብርታቱ አሁን የለም። ስለዚህም፡- ወንድሞቹን ከግብጽ ያወጣ ዘንድ እግዚአብሔር በእርሱ እጅግ የላቀውን ኃይልና ብርታቱን ሊገልጥ ትክክለኛው ጊዜ ደርሶ ወደፈርዖን ሊልከው እንዳሰበ ሲነግረው “የእሥራኤልን ልጆች ከግብጽ የማወጣ እኔ ማን ነኝ??” ብሎ ነበር የጠየቀው። የአባቶቹ የአብርሐም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክም፡- “በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” አለው። የሕዝቡን መከራ ያየ፣ ጩኸታቸውንም የሰማ፣ ሥቃያቸውንም ያወቀ እግዚአብሔር፣ በጸናችና በበረታች ክንድ የባርነት ቀንበራቸውን ሰብሮ ከፈርዖን አገዛዝ ነጻ ያወጣቸው ዘንድ፣…. ሙሴን ላከው፣ የእሥራኤል ቅዱስ፣ በሙሴ ወደ ግብፅ ወረደ!!!!!

“የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፣ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፣ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፣ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ፣…. ልኮኛል።” (ኢሳ.61፡1-3)

“ጴጥሮስም አፉን ከፍቶ እንዲህ አለ፡- እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ በእውነት አስተዋልሁ። የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ። ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፣ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስ የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፣ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረና።” (ሥራ፣10፡34-38)

በአዳም ከሆነው በደልና መተላለፍ የተነሳ፣ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ከዲያብሎስና ከገዛ ሥጋቸው ቀንበር ሥር ሆነው በኃጢአትና በሞት የሚሰቃዩትን የሰው ልጆች መከራ ያየ እግዚአብሔር፣ ከዚህ ጽኑ እሥራትና መከራ ነጻ ያወጣቸው ዘንድ፣ በእርሱ መልክ ይኖር የነበረውንና እጅግ የሚወደውን አንድያ ልጁን የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት አካባቢ ወደዚህ ምድር ላከው። ሁሉን ወራሽ ያደረገውና እግዚአብሔር ዓለማትን የፈጠረበት ይህ አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ ወደዚህ ምድር የመጣው፣ ቀድሞ በአባቱ ዘንድ በነበረው ክብር ሳይሆን፣ ስለ አባቱ ፈቃድ ሲል እጅግ ትሁት በመሆን ራሱን ባዶ አድርጎና ፍጹም ሰው ሆኖ ነበር። ለዚህም ነው በእግዚአብሔር ለተላከበት - ነፍሱን ስለሰው ልጆች ኃጢአት ቤዛ አድርጎ የመስጠትና ሰዎችን ሁሉ ከዲያብሎስ እሥራት ነጻ አውጥቶ ወደ እግዚአብሔር ክብር የመመለስ ዓላማ ብቁ ይሆን ዘንድ ፤ በሰላሳ ሶስት ዓመቱ በአጥማቂው ዮሃንስ እጅ ሲጠመቅ በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም የተቀባው።

የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ለ33 ½ ዓመታት በምድር ላይ ስለነበረው ቆይታ እጅግ በተለየና ጥልቅ በሆነ መንገድ የጻፈው፣
“ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር” ዮሐንስ ነው። ከዚህ በታች የተጠቀሱት የክርስቶስ የራሱ ቃላት ከዚሁ ወንጌል የተወሰዱ ናቸው።
“…..ነፍሴን ደግሞ አነሳት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታልሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሳት ሥልጣን አለኝ፤ ይህችን ትዕዛዝ ከአባቴ ተቀበልኩ።…… እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፣ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።….. እኔ ስለራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው…. የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁምና እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው።….. በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም፣ እኔን የሚያይ የላከኝን ያያል። በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሐን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቼአለሁ።…. እኔ ከራሴ አልተናገርኩምና ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትዕዛዝ ሰጠኝ። ትዕዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።….. እኔን ያየ አብን አይቶአል…. እኔ የምናገረው ቃል ከራሴ አልናገረውም፣ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፣ ባይሆንስ ስለራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ። …… እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”

በግብጽ ምድር የነበረውን ጩኸት ሰምቶ ሕዝቡን ከባርነት ቀንበር ነጻ ለማውጣት በሙሴ ወርዶ የነበረው፣ መንፈስ የሆነውና “የማይታይ አምላክ” የተባለው እግዚአብሔር፤ ከዘላለም ዘመናት በፊት ያቀደውን ሰዎችን ሁሉ የማዳንና ወደክብሩ የመመለስ ዓላማ ይፈጽም ዘንድ፣ በአንድያ ልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ወደዚህ ምድር ወረደ። ሐዋርያው ጳውሎስም “እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ…“ በማለት የተናገረውም ይህንን እውነት ነው። ሙሴ በቀደመው የእግዚአብሔር ሃሳብ ላይ የሰለጠነውና የታመነው “እንደ ሎሌ” ነበር። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሁሉ ወራሽ፣ የሁሉም ጌታ ነውና እርሱ የእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ላይ እንደ ልጅ የታመነ ነው። ስለዚህም እግዚአብሔር በልጁ ይፈጽመው ዘንድ ያሰበውን ፈቃዱን ለማድረግ ከእርሱ ጋር (WITH Him) ነበረና “የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው” አለ። ደግሞም አብ በእርሱ (IN Him) እርሱም በአባቱ ነበረና፡- “እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ” በማለት መሰከረ። ስለዚህም የዘመናት ሃሳቡን ይፈጽም ዘንድ በልጁ ሆኖ ወደምድር የወረደው - በሥጋ የተገለጠው እግዚአብሔር፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ያደርግ ዘንድ የወደደውን ፈቃዱን ሁሉ ከፈጸመ በሁዋላ፣ ከሙታን ባስነሳው ከልጁ ጋር በልጁም ሆኖ አረገ - በክብር ከፍ ከፍ አለ።

“አምላክ (Elohim) በእልልታ፣ እግዚአብሔር (Jehovah) በመለከት ድምጽ አረገ።” (መዝ.47፡5)

በዚህ የቆሬ ልጆች መዝሙር የተገለጠው ጥልቅ የመለኮት ሃሳብ ይህን መልእክት ለሚያነቡ ሁሉ የተገለጠ እንዲሆን ጸሎቴ ነው። በዚህ መዝሙር ላይ የምናገኛቸው ሁለት ስሞች እንዲሁ ተለያይተው የተቀመጡ አይደሉም። በአማርኛችን “አምላክ” ተብሎ የተጠቀሰው ቃል የሒብሪው አቻው “ኤሎሂም” ተብሎ የሚታወቀውና በትክክል ወደ አማርኛችን ብንመልሰው “አምላክ” ከሚለው የነጠላ መጠሪያ ስም ይልቅ “አማልክት” የሚለውንና ከአንድ በላይ ለሆኑ አካላት የምንጠቀምበትን ቃል ይሰጠናል። ይህን ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንውሰድ፡-
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” በማለቱ ከአይሁድ ለደረሰበት ተቃውሞ፡- “መጽሐፉ ሊሻር አይችልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት (ኤሎሂም) ካላቸው፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፡- ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?” በማለት የሰጠው መልስ ቀድሞ በመጽሐፋቸው እንዲህ ተብሎ የተጻፈውን በመጥቀስ ነበር፡-
 
“እግዚአብሔር በአማልክት (ሒብሪው ‘ኤል’ - ኃያላን) መካከል ቆመ፣ በአማልክትም (ኤሎሂም) መካከል ይፈርዳል።……. አኔ ግን፡- አማልክት (ኤሎሂም) ናችሁ፣ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤ ነገር ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ፣ ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ አልሁ። God standeth in the congregation of the mighty; he judgeth among the gods…. I have said, Ye are gods; and all of you are children of the most High. KJV (መዝ.82፡1 -6)

እንግዲህ በመለከት ድምጽ ከእግዚአብሔር(Jehovah) ጋር ያረጉት አማልክት(Elohim) የልዑል ልጆች ሁሉ ሲሆኑ፣ በእነዚህ ልጆች መካከል ቀዳሚና ራስ የሆነው ግን “ከሙታንም በኩር” የተባለው የሕያው እግዚአብሔር አንድያ ልጅ ጌታ ኢያሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ “የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ” ነው። ጌቶችና ነገሥታት የተባሉት፣ መከራውን የተካፈሉና ከእርሱ ጋር አብረው የሚነግሡት “የልዑል ልጆች” እንደሆኑ ያስተዋልን ስንቶች እንሆን??? እርሱ በነዚህ ብዙ ወንድሞቹ መካከል በኩር ሆኖ የቤተ ክርስቲያን ማለትም የአካሉ ራስ ሲሆን፣ እግዚአብሔርም “የክርስቶስ ራስ” እንደሆነ በመጽሐፋችን በግልጽ የተጻፈ ነው። (1ቆሮ.11፡3) እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሳውና በቀኙ ሲያስቀምጠው፣ ከእርሱ ጋር አብሮ ያስነሳቸውና በሰማያዊም ስፍራ ከክርስቶስ ጋር ያስቀመጣቸው ብዙ ልጆች አሉ። ይህንንም ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ቅዱሳን በጻፈው መልእክቱ ውስጥ እንዲህ ገልጦታል፡-
“ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ፣ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፤ በጸጋ ድናችሗልና፣ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ፣ ከእርሱ ጋር አስነሳን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን” (ኤ.ፌ.2፡4-7)

የክብር አባት፣ የጌታችንም የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ፣ በልጁም በኩል የገለጠውን ዘላለማዊ ሃሳቡንም ለመረዳት እንድትችሉ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲስጣችሁ እለምናለሁ። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን!!!!  


Thursday, July 12, 2012

በመጀመሪያ ቃል - ሎጎስ ነበር፣ በመጨረሻም እርሱ ነው!

“ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደሆን አስቀድሞ ተቀምጦ ኪሳራውን የማይቆጥር ማነው?? ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት ሊደመድመውም ቢያቅተው፣ ያዩት ሁሉ፡- ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘባበቱበት ይጀምራሉ።” (ሉቃስ 14፡28-30)

የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የነበረው ዮሃንስ፣ የወንጌሉን መልእክት መጻፍ በጀመረባቸው ጥቂት ዓረፍተ ነገሮች መካከል፣ ክርስቶስን በተመለከተ በዘመናት መካከል ላለው ግራ መጋባት ምክንያት የሆነና፣ ክርስቲያኖች - (ከእግዚአብሔር ዳግመኛ የተወለዱና ሁሉን የሚመረምሩበትና የሚረዱበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ የተቀበሉ የእግዚአብሔር ልጆች) ትኩረት ሰጥተውና ጊዜ ወስደው ሊያጠኑትና ሊረዱት የሚገባ አንድ ቃል አለ። ይኸውም በአማርኛችን “ቃል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ “ሎጎስ” ነው። በእርግጥ ይሄ “ሎጎስ” የሚለው የግሪክ ቃል ከክርስትናም ውጪ፣ በፍልስፍናው ዓለም ከክርስቶስ ልደት በፊት ይኖሩ የነበሩና እነ አሪስጦትልን የመሳሰሉ የግሪክ ፈላስፎች የተለያዩ ጽንሰ ሃሳቦችን ለመዘርዘርና ለማስረዳት የሚጠቀሙበት ቃል ነበር። የእኔ አነሳስ ይሄንን ጠንካራ የግሪክ ቃል በዝርዝርና በጥልቀት ለመተንተን ሳይሆን፤ ነገር ግን ቃሉ የያዛቸውንና “የእግዚአብሔር ምሥጢር” የተባለውን ክርስቶስን ለማወቅ የሚያስችሉንን ጥቂት ጭብጦች ለማሳየት፣ እንዲሁም “እንደ ፍቃዱ ምክር ሁሉን የሚሰራ” የተባለለት አምላካችን እግዚአብሔር በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የጀመረውንና ይፈጽመው ዘንድ የሚተጋበትን ዘላለማዊ ሃሳብ በመጠኑም ቢሆን ለመረዳት የሚያስችሉንን ጥቂት የመንደርደሪያ ሃሳቦች ለማንሳት ነው።     

የፍጥረት ሁሉ ባለቤትና ፈጣሪ፤ የጥበብ፣ የእውቀትና የማስተዋል ሁሉ ምንጭ የሆነው አምላክ፣ እንደ ፍቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራው ልዑል…. የፍጥረትን መሠረት ከማስቀመጡ - ‘ኅልቆ መሳፍርት’ የሌለውን ፍጥረቱን ከመፍጠሩ በፊት አስቦአል፣ ዕቅድ ዘርግቶአል፣ ፕላን አውጥቶአል፣…. “አስቀድሞ ተቀምጦ ኪሳራውን ቆጥሮአል - He counted – calculated – computed the cost” ዓለማት ሳይፈጠሩ - ምንም ነገር ሳይኖር - “በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ” የነበረው ሎጎስ፣ በ’ስትሮንግ’ የሒብሪውና የግሪክ መዝገበ ቃላት መሠረት የተተረጎመበትም አንዱ መንገድ ይኸው ነው። “ማሰብ፣ ማገናዘብ ወይም ምክንያቶችን ማስቀመጥ፣ ማስላት…” ሐዋርያው ጳውሎስ “በክርስቶስ ለማድረግ እንደወደደ እንደ አሳቡ….” በማለት ሲናገር፣ የእግዚአብሔር ኣሳብ ጅማሬ ክርስቶስ መሆኑን ለማሳየት ነው።

“በመጀመሪያ ቃል - ሎጎስ ነበር….” ዮሃ.1፡1

“እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፣ በቀድሞው ሥራው መጀመሪያ። ከጥንቱ ከዘላለም ጀምሮ ተሾምሁ፣ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ። ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፣ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ። ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፣ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፣ ምድሪቱንና ሜዳውን ገና ሳይፈጥር የመጀመሪያውንም የዓለም አፈር።” (ምሳ.8፡22-26)

እግዚአብሔር ማንም ሊያየው በማይችል ብርሐን ውስጥ የሚኖር፣ ከቅድስናው ክብር የተነሳ ምንም ‘ነገር’ በፊቱ ሊቆም የማይችል፣ ግርማው የሚያስፈራ አምላክ ነው። ሙሴ “እባክህ ክብርህን አሳየኝ” ብሎ በለመነው ጊዜ፣ “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አትችልም" ነበር ያለው። የእርሱን ባሕሪይና ማንነትስ ሊረዳው የሚችል ማነው?... ስለዚህ ይህ የማይታየው አምላክ ከሁሉ በፊት የሚታየውን ፍጥረት የሚፈጥርበትን፣ ለሚፈጥረው ፍጥረት ራሱን የሚገልጥበትን ወይም ከፍጥረቱ ጋር የሚገናኝበትን መንገድ ማዘጋጀት ነበረበት። አሁንም “ሎጎስ” የሚለው ቃል፤ የመለኮት መታየትና መገለጥን፣ አንድን አካል ወክሎ መናገርን፣ ከሁለተኛ ወገን ጋር የሚደረግ ግንኙነትን፣ መካከለኝነትን፣…. የሚያመለክት ቃል ነው። ዓለም ሳይፈጠር - ‘ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ፣ ቀላያት ገና ሳይኖሩ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ፣ ተራሮች ገና ሳይወለዱ …. እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ ያደረገውና አስቀድሞ የወለደው “ሎጎስ”፣ ዓለማትን ሁሉ “በእርሱ” ከመፍጠሩና ከማጋጠሙም በላይ፣ ከፍጥረቱ ሁሉ ጋር የሚገናኝበት፣ ራሱንም ለፍጥረቱ የሚገልጥበትና የሚያስተዋውቅበት መልኩና ምሳሌው ነው።

ወንጌላዊው ዮሃንስ፤ እግዚአብሔር ሥራውን ሁሉን ያቀደበትንና ያዘጋጀበትን ‘ብሉ ፕሪንት’፣ የፈጠረበትንና ያጋጠመበትን ሕይወት፣ ደግሞም የማይታየውን ማንነቱን ለፍጥረቱ ሁሉ የገለጠበትን “መልክ” - በመጀመሪያ በእርሱ ዘንድ የነበረውን ሎጎስ “እግዚአብሔር ነበር” ማለቱን በዚህ መንገድ ስንረዳው ብቻ ነው፣ ሃይማኖት የፈጠረውን ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘንድ ያለውን ክርስቶስን ማየት የሚሆንልን።   

“እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው
፣ የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፣ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው፣ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፣ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፣ ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል።” (ቆላ.1፡15-17)

“ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ነገር ያለእርሱ አልሆነም”  (ዮሃ.1፡3)

“እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ በዚህ በመጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕሪዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ በኃይል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዞአል፤….” (ዕብ1፡1-3 አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

እግዚአብሔር ፍጥረትን የፈጠረበትና የመሠረተበት፣ ያገናኘበትና ያዋቀረበት፣ እንዲሁም ደግፎ የያዘበት ሎጎስ - የመንገዱ መጀመሪያ ነበር። የማይታየው አምላክ የዘላለም መኖሪያው - የቤቱ መሠረት ያደረገውም “በእግዚአብሔር መልክ” ይኖር የነበረውንና፣ ነገር ግን የኃጢአታችንንና የበደላችንን ዋጋ ለመክፈል - ቤዛ ለመሆን፣ በቀደመው ክብሩና ማንነቱ ሳይሆን ራሱን ባዶ አድርጎና ፍጹም ሰው ሆኖ (ፍጹም ሰው የሆነበትም ዓላማ እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን በመቀበል እኛን ሊረዳና ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የታመነና የሚምር ሊቀ ካህን ለመሆን እንደሆነ ልብ ይሏል) ለ33 ½ ዓመታት በፕላኔታችን ላይ የተመላለሰውን ይሄንኑ አንድያ ልጁን ክርስቶስን ነው። ደግሞም በዘመናት ፍጻሜ ያደርገውና ይፈጽመው ዘንድ ከዘላለም ዘመናት በፊት ያቀደውና የወሰነው አሳቡም “በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።” (ኤፌ.1፡10)

የእግዚአብሔር ሥራ መሠረቱ፣ “የመንገዱ መጀመሪያ፣ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር፣ በእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው - አልፋ ….. ክርስቶስ ነው። ፍጥረት ሁሉ የቆመበት መሠረት፣ የተደገፈበት ምሶሶ፣ የተዋቀረበት መዋቅር፣… ክርስቶስ ነው። የእግዚአብሔር ሥራ ፍጻሜ፣ መጨረሻውና ድምድማቱ - ዖሜጋ….. ክርስቶስ ነው። የሕይወታችንና የእምነታችን መሠረት፣ ሐዋርያና ሊቀ ካህን፣ ጀማሪና ፈጻሚ፣ የቆምንበት ሕያው ዓለት… የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በአዳም በደልና መተላለፍ ወድቀንና ከእርሱ ተለይተን የነበርነውን እኛን፣ አምላካችንና አባታችን የሆነው እግዚአብሔር፣ ከወደቅንበት ያነሳን
በክርስቶስ ነው። በእርሱ ዳግመኛ ወለደን፣ ቀድሞውንም የነበረው ሃሳቡ እኛን በመልኩ እንደምሳሌው መፍጠር ነበርና ወደዚያ መልኩና ምሳሌው - ወደ ክርስቶስ እያሳደገን ነው። “እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ” የተባለለት ልዑል እግዚአብሔር (Sovereign God)፤ ለክብሩ ምሥጋና ይሆን ዘንድ በክርስቶስ የጀመረውን ይህን መልካም ሥራ ይፈጽመው ዘንድ የታመነ ብቻ ሳይሆን፤ በጥበብ፣ በእውቀትና በማስተዋል  የተሞላ ብርቱ አምላክ ነው።     

Friday, July 6, 2012

“ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል!!”

የጽድቅና የሕይወት ጠላት የሆነው ዲያብሎስ በአገልጋዩ በሐይማኖት በኩል በዘመናት መካከል ይፈጽመው ዘንድ የሚተጋበት ዋና ዓላማው፣ እግዚአብሔር ከሙታን ያስነሳውን፣ በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዓለም ከሚጠሩት ስሞች ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጥቶትና ጌታም ክርስቶስም አድርጎት በቀኙ ያስቀመጠውን ኢየሱስን፣ ከቻለ ስሙን ከምድር ገጽ ላይ ለመደምሰስ፣ ካልቻለ ደግሞ ሰዎች ስለ እርሱ ባላቸው መረዳት ላይ ውዥንብርና ግራ መጋባትን መፍጠር ነው። ይኸው “የክርስቶስ ተቃዋሚ” ሰዎች ሁሉ ይድኑበት ዘንድ ከሰማይ በታች የተሰጣቸውን ይህን አንድ ስም በእምነት እንዳይጠሩ፣ ጠርተውም እንዳይድኑ ከልባቸውና ከአንደበታቸው ላይ ለመንጠቅ ግርግር መፍጠር የጀመረው፣ የክርስቶስ ሐዋርያት በጌታቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ቅባት ለማገልገል ‘ሀ’ ብለው በጀመሩበት ማለዳ ነበር።

የበዓለ ሃምሳ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ “ጉሽ” የሰከሩት ሓዋርያት “እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእሥራኤል ወገን ሁሉ ይወቅ” በማለት በእጃቸው የነበረውን የዘላለም ወንጌል መስበክ ሲጀምሩ፣ ሶስት ሺህ የሚያህሉ “ነፍሳት” ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ተጨመሩ። በዚሁ እግሮቻቸው - “በሰላም ወንጌል”፣ ወደ ቤተ መቅደስ ተጉዘው ከእናቱ ማሕጸን ጀምሮ መራመድ ተስኖት የነበረውን አንካሳ “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሳና ተመላለስ” በማለት አዘለሉት። እርሱም ስለሆነለት ድንቅ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደቤተመቅደስ ገባ። በዚህም ተአምር መደነቅና መገረም የያዛቸው አምስት ሺህ ነፍሳት ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሲጨመሩ የካህናት አለቆችና የመቅደስ አዛዥ ሰዱቃውያን ግን ድንጋጤ ወደቀባቸው። በኢየሩሳሌምም ስብሰባ አድርገውና እነዮሐንስን በመካከል አቁመው፡- “በምን ኃይል ወይስ በማን ስም እናንተ ይህን አደረጋችሁ?” ብለው ጠየቋቸው።
“በዚያን ጊዜ ጴጥሮስም መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ እንዲህ አላቸው፡- እናንት የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች፣ እኛ ዛሬ ለድውዩ ሰው ስለተደረገው መልካም ሥራ ይህ በምን እንደዳነ ብንመረምር፣ እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሳው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ሰው ደህና ሆኖ በፊታችሁ እንደቆመ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእሥራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን። እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው። መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” (ሥራ 4፡8-13)

ከዚህን ዕለት ጀምሮ ነው ያ የወንጌል ጠላት የሆነው “የጨለማው ገዢ” ይህንን ሰዎች ሁሉ ይድኑበት ዘንድ ከሰማይ በታች የተሰጣቸውን አንድና ብቸኛ ስም ለማጥፋት የመጀመሪያ ሙከራውን ያደረገው። አሁንም እነዚያን አገልጋዮቹን በሸንጎአቸው ለምክር እንዲቀመጡ ጠራቸው። እነርሱም ፡- “በነዚህ ሰዎች ምን እንሥራ? የታወቀ ምልክት በእነርሱ እጅ እንደተደረገ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ተገልጦአልና እንሸሽገውም ዘንድ አንችልም፤ ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ አብዝቶ እንዳይስፋፋ ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው ብለው እርስ በእርሳቸው ተማከሩ። ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዟቸው” (ሥራ.4፡16-18) ሐዋርያቱ ግን በዲያበሎስ ዛቻና ማስፈራሪያ ሳይደናገጡ ይህን ሰዎች ሁሉ ይድኑበት ዘንድ ከሰማይ በታች የተሰጠውን አንድና ብቸኛ ስም “እኛ ግን የተሰቀለውን፣ የሞተውን፣ እግዚአብሔርም ከሙታን ያስነሳውንና ጌታም ክርስቶስም አድርጎ በቀኙ ያስቀመጠውን ኢየሱስን እንሰብካለን!!” እያሉ ለምድር ወገኖች ሁሉ በሐይማኖት መርዝ ያልተመረዘውንንና በሰው ትምሕርት ያልተበከለውን ንጹሁን  የመዳን ወንጌል እየሰበኩ ሰዎችን ወደእግዚአብሔር መንግሥት መጨመራቸውን ቀጠሉ።

ከላይ እንዳልነው፣ የጽድቅና የሕይወት ጠላት የሆነው ዲያብሎስ በአገልጋዩ በሐይማኖት በኩል በዘመናት መካከል ይፈጽመው ዘንድ የሚተጋበት ዋና ዓላማው፣ እግዚአብሔር ከሙታን ያስነሳውን፣ በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዓለም ከሚጠሩት ስሞች ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጥቶና ጌታም ክርስቶስም አድርጎ በቀኙ ያስቀመጠውን ኢየሱስን፣ ከቻለ ስሙን ከምድር ገጽ ላይ ለመደምሰስ፣ ካልቻለ ደግሞ ሰዎች ስለ እርሱ ባላቸው መረዳት ላይ ውዥንብርና ግራ መጋባትን በመፍጠር ከጽድቅና ከሕይወት መንገድ ማሳሳት ነው። ውዥንብር በመፍጠር ግራ የማጋባት አጀንዳውን እጅግ በጠለቀና በረቀቀ መልኩ የፈጸመው፣ በተለይም ከ325ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በጠራቸው ሸንጎዎች ላይ ባረቀቃቸውና ባጸደቃቸው “የሐይማኖት መግለጫዎች” ነው። በዚያን ጊዜም፣ በክርስቶስ ሓዋርያት የተሰበከውን ግልጽና የማያሻማ የጽድቅና የሕይወት መንገድ ከመጣመሙም በላይ፣ ሰዎች በክርስቶስ ባላቸው እምነት ከእግዚአብሔር ዳግመኛ ሲወለዱ በሚቀበሉት መንፈሳዊ አእምሮ ብቻ ሊመረምሩና ሊረዱ የሚችሉትን “የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር”፣ በፍጥረታዊው አእምሮአቸው እንዲመረምሩና አቋማቸውንም “በአብላጫ ድምጽ” እንዲወስኑ በማድረግ፣ እስከዛሬ ድረስ በክርስትና ውስጥ እየበዛ ለመጣው ግራ መጋባትና መከፋፈል ምክንያት የሆነውን ጠንካራ መሠረት ጥሏል። 

ሐዋርያት፣ አሕዛብን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱሰ ስም እያጠመቁና እርሱ ያዘዛቸውን እያስተማሩ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ በክርስቶስ የተሰጣቸው መመሪያ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገር ግን እነርሱ በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ወንጌልን አልሰበኩም፣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ድውዮችን አልፈወሱም፣ አጋንንትን አላወጡም፣ ሙታንን አላስነሱም፣ እጃቸውን ወደግራና ወደቀኝ እያወናጨፉ “አላማተቡም”…. የሰበኩት አንድ ወንጌል፣ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶሰ ስለስዎች ሁሉ ኃጢአት እንደሞተ፣ እንደተቀበረና በሦስተኛውም ቀን እግዚአብሔር ከሙታን አስነስቶ በቀኙ እንዳስቀመጠው የሚናገረውንና፣ ይህን በማመን ስለሚገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት ጸጋ እና ለሰዎች ሁሉ እንዲያው ስለተሰጠው የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሚያበስረውን ወንጌል ነው !! የሰዎችን እምነትና ሕይወት “እንደብልሃተኛ የአናጺ አለቃ” የመሰረቱትም ሆነ ያነጹት፤ በተፈተነው፣ በከበረውና መሠረቱ በጸናው የጽዮኑ አለት በክርስቶስ ላይ ነበር።

ሐዋርያቱ የሰበኩት ክርስትና የተመሠረተው፣ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ!” በሚለው በሰማያት ካለው አባት በመጣው ሰማያዊ መገለጥ ላይ ነበር። ለዚህም ነው፡- “ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፣ ….. ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማነው? ….. በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የሰጠውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል። እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት እንደሰጠን፣ ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፣ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም” (1ኛዮሐ. 5፡1-12) እያሉ ግልጽ በሆነና ውዥንብር በማይፈጥር ትምሕርት የሕይወትን መንገድ የሰበኩት። የእግዚአብሔር መንፈስ እጃቸውን ይዞና አእምሮአቸውን ተቆጣጥሮ የጻፉትም መልእክት ለምን እንደተጻፈ ሲናገሩም እንዲህ አሉ፡-  
“ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።” (ዮሐ.20፡30-31)

Monday, July 2, 2012

የሕይወት መንገድ!!!!


በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት በፊቱ ወዝ - በጉልበቱ ድካም ፣ ካለው በዋጋ ገዝቶ፣ ከሌለው እጁን ዘርግቶ ለሥጋው የሚሆነውን የዕለት እንጀራ እንዲበላ በእግዚአብሔር ተረግሞ የነበረው ሰው፤ “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነው” ወደተባለለት አምላኩ ቀርቦ፣ እንዲያው - በነፃ - ያለምንም ዋጋና ክፍያ፣ ከሕይወት ውሃና እንጀራ በልቶና ጠጥቶ የተራበች ነፍሱን ያጠግብ ዘንድ መንገዱ የትኛው ነው?? አለመታዘዝና ውድቀት ያለበሰውን መንፈሳዊ ጉስቁልና - የኃጢአትና የዓመጽ ድሪቶ አውልቆ የጽድቅና የክብር ሸማ የሚለብሰውስ ምን ቢያደርግ ነው??  ሰው ከሞትና ከሲዖል የሚያመልጥበት መንገዱ ስንት ነው??....

ለእነዚህ ጥያቄዎች የማያዳግም መልስ የሰጠው እግዚአብሔር፣ በአንድያ ልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የገለጠውን ብቸኛ የጽድቅና ሕይወት መንገድ የሚቃወመውና የሚያጣምመው ዲያብሎስ፣ በአገልጋዩ በሐይማኖት በኩል ለሰዎች ብዙ ሐሰተኛ ምርጫዎችን አቅርቦላቸዋል። መልካም ሥራ ቢሰሩ - ቢጾሙ ቢጸልዩ፣ ለድሆች ቢሰጡ፣ በቀን አምስት ወይም ሰባት ጊዜ ቢጸልዩና ቢሰግዱ፣ ልዩ ልዩ "መንፈሳዊ ስፍራዎችን" ቢጎበኙ፣ ከሰዎች ርቀው ከአውሬ ጋር በጫካ ቢኖሩ - ገዳም ገብተው ቅጠል ከበሉና ጥሬ ከቆረጠሙ፣…. ወደ ጽድቅ በሚወስደው መንገድ ላይ ስለመሆናቸው አንዳች እንዳይጠራጠሩ ነግሮአቸዋል። ደግሞም ሰው ሁሉ ደካማ አይደለምና ከእርሱ ይልቅ የበረቱትን “ጻድቃን - ሰማዕታት”፣ ለእግዚአብሔር ቅርብ የሆነችውን “ወላዲተ አምላክ”፣ ወይም ቅዱሳን መላዕክቱን… እነርሱን በግንባር ማግኘት ስለማይቻል “ይህን ሊመስሉ ይችላሉ” ብሎ ለቀባው ሰዕላቸው “የአክብሮት ስግደት” እየሰገደ ቢለማመን… “በዕለተ ቀናቸው” ወይም “በበዐለ ንግሣቸው”፤ ጧፍ ዣንጥላውን፣ ዕጣን ዘቢቡን… ስዕለት መሥዋዕት አድርጎ ቢያቀርብ፣ ድግስ ደግሶ ቢያበላ ቢያጠጣ፤ …. ችግሩን ለእግዚአብሔር ነግረው፣ ወደ ሕይወት የሚያስገባውን በር እንደሚያስከፍቱለት አስተምሮአቸዋል። ….. እነዚህ ሁሉ ግን ሐይማኖት የጠረጋቸው የሲዖል መንገዶች ናቸው።

“በታች ካለው ከሲዖል ያመልጥ ዘንድ፣ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደላይ ይወስደዋል።” (ምሳሌ 15፡24)

አዳም ባለመታዘዝ ሲወድቅ፣ ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላና በኃጢአት በተበላሸው በዚያ ማንነቱ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር እግዚአብሔር ወደሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ በኪሩቤልና በምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍ ዘግቶት ነበር። ከዚህም የተነሳ ሰው ከአምላኩ ተለይቶ በመንፈሱ ሞተ፤ ነፍሱም እረፍትና ሰላም ያጣች ተቅበዝባዥ ሆነች፣ ሰውነቱም በተለያዩ ጥቃቅን ተሐዋስያን የሚጠቃና በደዌ የሚማቅቅ አቅመ ቢስ እየሆነ፣ በእርጅና እየደከመና እየጎበጠ ወደተገኘበት አፈር መመለስ ጀመረ። ከእግዚአብሔር በተወሰነለት የጽድቅና የሕይወት መንገድ ላይ ሳይሆን፣ ዓመጽና ኃጢአት በሞላበት የሞትና የሲዖል መንገድ ላይ ራሱን አገኘ። ነቢዩ ኢሳይያስ ይህን ሁኔታ “እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፣ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ….” በማለት ገልጦታል።

ሰው ዬትኛውንም ዓይነት ብልሐትና ጥበብ፣ ጉልበትና ኃይል.... ቢጠቀም፣ በምድር ላይ ያሉትን እንሰሳት ሁሉ መሥዋዕት አድርጎ ቢያቀርብ፣ በቀን ውስጥ የቻለውን ያህል ሲሰግድና ሲለማመን ቢውል፣.... የማንም ልመናና ጸሎት፣ ምልጃና ዕንባ… እግዚአብሔር የዘጋውን ይህን የሕይወት መንገድ ሊያስከፍት አይችልም። እግዚአብሔር የዘጋውን ማን ሊከፍተው ይችላል?? ታድያ እርሱ ይህን ወደሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ የዘጋው እስከወዲያኛው ላይከፍተው ነበር?? ሰውስ ወደቀደመው ክብሩ የሚመለስበት ተስፋ የለውም?? የሰው ልጅ አሁን በሚኖርበት የሐዘንና ሰቆቃ፣ የጉስቁልናና የስቃይ ኑሮ፤ በጨለማው ገዢ የባርነት ቀንበር ስር እየማቀቀ ዘመኑን አንዲገፋ ለዘላለም ተፈርዶበታል?? ..... በጭራሽ!! እንዲህ ዓይነቱ ጭካኔ ከእግዚአብሔር ይራቅ!!    

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዐለሙን  እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሃ.3፡16)
“እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደሰጠን፣ ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፣ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።” (1ዮሃ.5፡11-12)   

የዛሬ 2000 ዓመት አካባቢ፣ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሲሰጥ፣ በአዳም አለመታዘዝ ሰበብ በኪሩቤልና በምትገለባበጥ ሰይፍ ተጠብቆ ወይም ተዘግቶ የነበረውና ወደሕይወት ዛፍ የሚወስደው መንገድ ለሰው፣ ይልቁንም ለሚያምኑ ሁሉ እንደተከፈተ የተረዳን ስንቶች ነን?? ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ላይ የመጨረሻ ትንፋሹን ተንፍሶ እና በታላቅ ድምጽ “ተፈጸመ” በማለት ጮሆ ነፍሱን ሲሰጥ፣ በኢየሩሳሌም ምድር እጅግ አስገራሚ ነገር ሆነ፤ ….. ፀሐይ ጨለመች፣ የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። የዚህ መጋረጃ መቀደድ ተምሳሌትነቱ፣ በአዳም በደል ምክንያት በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ መፍረሱና፣ ሰዎች ሁሉ በክርስቶሰ ኢየሱስ ባለ እምነት በኩል ወደ እግዚአብሔር እየቀረቡ ከሕይወት ምንጭ እንዲያው - በነፃ የሚጠጡበት፣ ከሕይወት እንጀራም የተራበች ነፍሳቸውን የሚያጠግቡበት መንገድ መከፈቱ ነው።

“እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሃ.14፡6)

እግዚአብሔር የዛሬ 2000 ዓመት አካባቢ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን ይህን አንድና ብቸኛ መንገድ ከገለጠበት ጊዜ ጀምሮ፣ የጽድቅና የሕይወት ጠላት የሆነው ዲያብሎስ፣ ሲችል ይህን ብቸኛ የሕይወት መንገድ በግልጽ እየዘጋና እየተቃወመ፣ ሳይችል ደግሞ ሌላ አማራጭና ሐሰተኛ መንገዶችን እያቀረበ፣ እግዚአብሔር በልጁ በኩል እንዲሁ - በእምነት ብቻ ከሰጣቸው ሕይወት ሰዎችን ለማሳትና ለማጉደል የተጠቀመው ፖለቲካን ወይም ኢኮኖሚን ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም ሐይማኖትን ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የቀደደውን መጋረጃ በትምሕርቶቻቸው መልሰው የሰፉ፣ እርሱ በሥጋው ያፈረሰውን የጥል ግድግዳ በተረቶቻቸው መልሰው የገነቡ የፖለቲካ ካድሬዎች ሳይሆኑ የሐይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች ናቸው። ዛሬ ግን ዘመን መጣ!! ሓይማኖት በሰዎች አዕምሮ ላይ የጣለውን መጋረጃ እግዚአብሔር በመንፈሱ ኃይልና በቃሉ ሥልጣን እየገፈፈ ነው!! ለሰው ልጆች የሰጠውም ብቸኛው ሕይወትና የሕይወት መንገድ፣ እርሱም ክርስቶስና ጌታ የሆነው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ፣ ስሙ በኢትዮጵያ ሰማያት ላይ እያስተጋባ ነው!! ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን!!!!!!