"አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።" 2. ጢሞ.3፡14-17
መንፈሳዊውን ጥበብና ዕውቀት በተመለከተ "ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ራሱ መንፈሱ የእምነት ምንጭ ነው" የሚለው የአንዳንድ ወንድሞች አባባል "የበሰለ" ቢመስልም ነገር ግን ሚዛኑን የጠበቀ ባለመሆኑ ወደ ስህተት ያዘነበለ ነው። እንዲህ ዓይነቱ መረዳት ከተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ጋር የሚጣረሱ ብዙ የተለያዩ እንግዳ ትምሕርቶች ወደ ቤተክርስቲያን ሾልከው እንዲገቡና ብዙዎች ከጽድቅና ከሕይወት መንገድ ርቀው እንዲጠፉ ምክንያት ይሆናል። ለዚህም ማስረጃው በአገራችን ኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች እጅ ባልነበረባቸው ረጅም ዘመናት ውስጥ የተሰበኩት ልዩ ልዩ የሰው ድርሰቶች የፈጠሩት እንግዳ ሐይማኖት ነው። “እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል!!” ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ የእምነታችን ምንጭ ሊሆን የሚገባው የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ወይም በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እንዲህ ማለቴ “የእግዚአብሔር ቃል” በእጃችን ባለው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰው ፊደላት የተጻፈው ብቻ ነው ለማለት አይደለም። መነሻችንና መሠረታችን ግን የተጻፈውና እግዚአብሔር በዘመናት መካከል የተለየ ጥበቃ እያደረገለት ዛሬ በእጃችን ላይ እንዲገኝ ያደረገው መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
"ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።" ዮሃ.20፡30-31
መጽሐፍ ቅዱሳችን በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ብቻ ሳይሆን ከላይ በ2ጢሞ.3፡14-17 በጠቀስኩት የጳወሎስ መልእክት ላይ እንደምናነበው "የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት" መሆኑን ማንኛችንም አንስትም። ይህ መጽሐፍ እንደየደረስንበት መንፈሳዊ የዕድገት ደረጃ በተለያየ ልክና መጠን የምንረዳውን የእግዚአብሔር ሃሳብ የያዘ ሆኖ ተጀምሮ እስኪጨረስ ድረስ የሚነግረን ዋና መልእክትም በቀደመው አዳም ያጣነውን ክብር የሞላበት ሕይወት በክርስቶስ መልሰን ስለማግኘታችን ነው። በዚህም ምክንያት ወደተፈጠርንበት ዋና የእግዚአብሔር ዓላማ እርሱም እግዚአብሔርን ወደመምስል መድረስ የምንችልበትን ብቸኛ መንገድ ይጠቁመናል። እርሱም ክርስቶስ ነው። (2ጢሞ.3፡12)
በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የተገለጠው የእግዚአብሔር ሃሳብ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ቀድተን የማንጨርሰው ባህር ነው። በዚህ ጥልቅ ባህር ውስጥ ራሳችንን ችለን መዋኘት እስክንጀምር ድረስ፣ ወይም በግልጽ አነጋገር በመንፈስ የተጻፈውን መፅሐፍ በመንፈስ በሆነ መገለጥ በየግላችን መረዳት እስክንችል ድረስ የሚያግዙንን አስተማሪዎች የአካሉ ራስ የሆነው ክርስቶስ በአካሉ ውስጥ አኑሮአል። እነዚህ አስተማሪዎች በተሰጣቸው ጸጋና ቅባት አማካኝነት በመንፈስ የተጻፈውን መጽሐፍ በመንፈስ እየተረጎሙ ያስተምሩናል። እኛም በእነርሱ አማካኝነት ደግሞም በጽሞናና በጸሎት ሆነን በየግላችን ቃሉን በምናነብበት ጊዜ በምናገኘው መረዳት መጠንና ልክ በመታዘዝና በታማኝነት መኖርና መመላለስ ስንጀምር በመንፈሳዊ ሕይወታችን እያደግንና እየጎለመሰን እንሄዳለን። ያኔም በፊደላት በወረቀት ላይ ተጽፎ የነበረውን ቃል የሕልውናችን ሕግ ይሆን ዘንድ በቅዱሱ መንፈስ አማካኝነት በልባችን ጽላት ላይ ተጽፎ እናገኘዋለን። ይሄም በእግዚአብሔር መንፈስ መመራት ወደምንችልበት ከፍታ ያወጣናል።
"ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።.... ስምዖን ጴጥሮስ። ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት። " ዮሃ.6፡63-69
"እኔ የነገርኳችሁ ቃል መንፈስ ነው"
"በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና።" ሮሜ.8፡14
በእግዚአብሔር ቃል ወይም ከላይ እንዳልኩት በክርስቶስ ትምሕርት መኖርና በመንፈስ መመላስ ሁለት የተለያዩ ነገሮች አይደሉም። በእግዚአብሔር መንፈስ መመራት ማለት በልባችን ውስጥ እየተጻፈ ካለው የእግዚአብሔር ቃል ውጪ በአንድ የሆነ ኃይል መነዳት ማለት አይደለም። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ በሰጠን ጸጋና ጉልበት ክርስቶስ በነገረን ቃል መሠረት መመላለስ ስንጀምር በመንፈስ መመላለስ ጀምረናል ማለት ነው። እሱ የነገረን ቃል የሚመራን መንፈስም ጭምር ነው። ይሄ የከበረ እውነት በእግዚአብሔር መንፈስ ለተቀባው ዳዊትም ተገልጦለት ነበር። "ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው" መዝ.119፡105
በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያላደጉ ክርስቲያኖች "በእግዚአብሔር መንፈስ መመራት" ወይም በሰሙት ቃል መጠንና ልክ ለመኖር ወደሚችሉበት መንፈሳዊ ዓቅምና ችሎታ እስኪደርሱ ድረስ በእምነት የሚያበረታቷቸው፣ የሚመክሩዋቸውና የሚያጽናኗቸው፣ ደግሞም እንደየደረሱበት የዕድገት ደረጃ የሚመጥናቸውን መንፈሳዊ ምግብ የሚመግቡዋቸው፣ የሚጠብቋቸውና ከፊት ሆነው የሚመሯቸው እረኞችና አስተማሪዎች ያስፈልጓቸዋል። ከላይ በአጭሩ ለመግለጥ እንደሞከርኩትም በኤፌሶን መልእክት ምዕራፍ 4 ላይ የምናገኛቸው አገልግሎቶችም ዓላማቸው ይህ ነው።
"እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።" ኤፌ.4፡11-13
እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የመሠረተው አዲስ ኪዳን፤ ከአሮጌው ኪዳን የሚለይበት ዋነኛ ምክንያት አዲሱ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕግ በእግዚአብሔር መንፈስ አማካኝነት በልባችንና በአእምሮአችን ላይ የሚጻፍበት የሕይወት ዘመን ሂደት በመሆኑ ነው። ይሄ ሂደት ወደ ሙላትና ፍጽምና የሚደርሰው ግን በመጽሐፍ ተጽፎ የተሰጠን የክርስቶስ ትምሕርት በቃልም ቢሆን በስብከት አማካኝነት በልባችን ውስጥ ተዘርቶ ሲያድግ፣ አድጎም ፍሬ ሲያፈራ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አሥራ ሶስት ላይ ስለዘሪው ምሳሌ ያስተማረውም ትምሕርት ለዚህ እውነት ዓይነተኛ ምሳሌ ነው።
"በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል።" ዮሃ.15፡7-8
ዛሬ የክርስቶስን ቃል ከየት ነው የምናመጣው?? ከተጻፈልንና በእጃችን ካለው መጽሐፍ ውስጥ አይደለምን?? እያንዳንዳችን የደረስንበትንና ዛሬ ያለንበትን ሕይወት መጠንና ልኩን ለማወቅ፤ በቀላሉ "የተራራው ስብከት" በመባል የሚታወቀውንና ከማቴዎስ ምዕራፍ አምስት እሰከ ሰባትድረስ ባሉ ሦስት ምዕራፎች ብቻ የተጻፈውን የክርስቶስ ትምሕርት ማጥናት በቂ ነው። ያኔ - በሦስት ምዕራፎች ላይ ብቻ በተጻፈው በዚህ የክርስቶስ ትምሕርት መጠንና ልክ ራሳችንን ለማግኘት የሕይወት ዘመን ተጋድሎን እንደሚጠይቅ እናስተውላለን።
"ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ። ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።" ማቴ.7፡24-29
ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው፡-
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ቃል የተናገረው ከላይ ያነሳሁትንና "የተራራው ስብከት" በመባል የሚታወቀውን የከበረ ትምሕርት አስተምሮ ሲጨርስ ነው። ይህን ትምሕርት በዚህ ዘመን ያለነውን እኛን ያስተምረን ዘንድ ክርስቶስ እንደገና በሥጋ መገኘት አያስፈልገውም። እንሰማው ዘንድ ቃሉ በእጃችን ባለው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ እናገኘዋለን። ልናደርገው ወይም በሕይወት አካሄዳችን ልንመላለስበት የምንችለው ግን በስብከትም ይሁን በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት በጆሮአችን የምንሰማው ይህ ቃል በእግዚአብሔር መንፈስ አማካኝነት በልባችን ጽላት ውስጥ የተጻፈ እንደሆን ብቻ ነው። ቃሉ በልባችን ውስጥ የመጻፉ ነገር እውን የሚሆነው ደግሞ በእግዚአብሔር መንፈስ አሰራር ብቻ ሳይሆን በእኛም የልብ መዘጋጀት ጭምር ነው። ለዚህ መንፈስና ሕይወት ለሆነው ሕያው ቃል ልባችንን እንደመልካም መሬት ማዘጋጀት እንድንችል እግዚአብሔር ይርዳን!!!!
"በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።" ሉቃ.8፡15