"እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም። ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።" ዕብ.2፡14-18
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የመላእክትን ሳይሆን የአብርሃምን ዘር መያዙና በነገር ሁሉ ወንድሞቹን የመምሰሉ ምክንያት፤ በነገር ሁሉ እንደወንድሞቹ ለመፈተን ነው። በነገር ሁሉ እንደወንድሞቹ መፈተኑ ደግሞ፤ የዕብራውያን ጸሐፊ እንደነገረን፡- እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው እንዲችል ነው። የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀክህነት መሠረቱም ይኸው በነገር ሁሉ ወንድሞቹን መምሰሉና፣ በነገር ሁሉ እንደወንድሞቹ መፈተኑ ነው!!
"እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን እምነታችንን እንጠብቅ። ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ (was in all points tempted just as we are, yet without sin.) በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ" ዕብ.4፡14-16
እዚህ ላይ ለብዙዎች አእምሮ የሚከብድ ቢሆንም አንድ ነገር አጥርተን እንይ፤ "ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው" የሚለው የአማርኛው አገባብ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአት እንዳልተፈተነ አስመስሎታል። ነገር ግን ትክክለኛው የቃሉ አገባብ "እርሱ በነገር ሁሉ እንደ እኛ ቢፈተንም ኃጢአትን ግን አላደረገም" የሚል ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስም ከዚሁ ሃሳብ ጋር የሚመሳሰል ነገር ተናግሯል፡-
"የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ" 1ጴጥ.2፡21-23
አንድን ተፈጥሮአዊ ማነንት ወይም ባህሪይን የሚወስነው ዘር ነው። እርሱ በድንግሊቱ ማሕጸን የአብርሐምን ዘር ይዞ የመወለዱ ምሥጢር ለእግዚአብሔር የሚተው ሆኖ፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን የመምሰሉ ምክንያት ግን የተካፈለው በእርግጥ የአብርሃምን ዘር በመሆኑ ነው። በዚህ ዘር ውስጥ ሰውን ሰው ሊያሰኙ የሚችሉ ባህሪያት ሁሉ አሉ። የዕብራውያን ጸሐፊ “የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸው” የማለቱም ምሥጢር ይኸው ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በነገር ሁሉ እንደእኛ የተፈተነው ከተካፈለው የሥጋና ደም ባህሪይ የተነሳ ነው። እርሱ በነገር ሁሉ እንደ እኛ ተፈትኗል ስንል የእኛ ፈተና ምንድነው? አንዳንዶች የክርስቶስን ፈተና ከረሃብና ከጥማት ጋር ብቻ ያያዙታል። ነገር ግን ዋናው ፈተናችን ካለን የሥጋና ደም ባህሪይ የተነሳ የምንፈተንባቸው ልዩ ልዩ የኃጢአት ፈተናዎች ናቸው። እነዚህ ፈተናዎች እያንዳንዳቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትም አልፈዋል። ነገር ግን እርሱ ለአንዱም ስንኳን አልተሸነፈም። ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ሥርየት የሚሆነው የእግዚአብሔር በግ ያለ ነውርና ያለነቀፋ የመሆኑ ምሥጢር፤ በተካፈለው ሥጋና ደም በኩል የመጣበትን የኃጢአት ፈተና ሁሉ በመስቀል ታግሶ ማሸነፉ ነው። "በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ" ያለበትም ምሥጢሩ ይኸው ነው። ዓለምና በዓለም ያለው ደግሞ፤ የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ስለ ገንዘብ መመካት - The pride of life መሆኑን ልብ ይሏል! ሴቲቱ በዔደን ገነት በነበረው እባብ የተፈተነችባቸው በሴቲቱም በኩል ፊተኛው አዳም ተፈትኖ የወደቀባቸው ፈተናዎችም እነዚሁ የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ስለ ገንዘብ መመካት - The pride of life ነበሩ። ዛሬ በዓለም ያለነው እኛም የምንፈተነው በእነዚሁ የጽድቅና የሕይወት ጠላቶች ነው።
"እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።" ዕብ.5፡7-10
ከዘላለም ሞት የመትረፋችንና የመዳናችን መሠረቱ የክርስቶስ ኢየሱስ መታዘዝ መሆኑን የምናውቅ ስንቶቻችን እንሆን? ወገኖቼ! መዳናችን እንዲሁ በተዓምር ወይም በመለኮታዊ ኃይልና ችሎታ፣ ወይም በአምላክ ይሁንታ የተፈጸመ ሳይሆን ***በመታዘዝ*** ነው። በአንዱ አለመታዘዝ ወደ ዓለም የገባው ኃጢአትና ሞት የተሸነፈውና ከዓለም የተወገደው በአንዱ መታዘዝ ነው። የፊተኛው አዳም አለመታዘዝ እውነተኛ አለመታዘዝ ከመሆኑም በላይ የኃጢአትና የሞትን መዘዝ በሰዎች ሁሉ ላይ አስከትላል፤ እንዲሁም የኋለኛው አዳም የኢየሱስ መታዘዝ ፍጹምና እውነተኛ መታዘዝ በመሆኑ የጽድቅና የሕይወት ምንጭ ሆኗል። መዳናችንን ለመፈጸም ክርስቶስ በሥጋው ወራት የተቀበለው መከራ እንዲህ ነው ተብሎ የሚገመት አይደለም። ነውርና ነቀፋ የሌለው የኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ ራሱን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ፤ በተካፈለው ሥጋና ደም በኩል የሚመጣበትን ፈተና ሁሉ ማለፍና ማሸነፍ ነበረበት። የክርስቶስ መከራ በአይሁድ ካህናትና በሮማውያኑ ወታደሮች እጅ ተላልፎ ሲሰጥ በእንጨት ላይ የተቀበለው መከራ ብቻ አልነበረም። ይሄ የመከራው ጫፍና ፍጻሜ እንዲሁም ውጫዊ መገለጫ ነው። ነገር ግን ክርስቶስ በሥጋ ባሳለፋቸው ዓመታት ሁሉ በሥጋና በደም የሚመጡትን ፈተናዎች ለማለፍና መታዘዙን ለመፈጸም መከራን ተቀብሏል። ለዚህም ነው በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን ያቀረበው። ምንም ልጅ ቢሆን ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተምሯል። እስከ መስቀል ሞት የደረሰው መታዘዙ ደግሞ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ የመዳናችንን በር ከፍቷል!!
"ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።"
“ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና"
በዚህ ዓለም በሥጋ ሳለን ክፉውን አሸንፈን የተሰጠንን የዘላለም ሕይወት ተስፋ የመውረሳችን አለኝታ፤ በነገር ሁሉ እኛን መስሎ፣ በሁሉ እንደእኛ ተፈትኖና ድል ነስቶ በሰማያት በግርማው ቀኝ የተቀመጠው ዘላለማዊ ሊቀ ካህን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ” በማለት ተስፋን የሰጠው እርሱ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ ነው። እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች የሆንን ሁላችን የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነውን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስን ተመልክተን ከፊታችን ያለውን ሩጫ በእምነት እንሩጥ፣ እርሱ ነውርን ንቆ፣ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሶ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና!! (ዕብ.12፡1-2)
No comments:
Post a Comment