Saturday, December 7, 2013

እግዚአብሔር በአንድያ ልጁ ወደ ምድር ወረደ -  ብዙ ልጆችንም ይዞ ወደ ሰማይ አረገ!!!


 “የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ሕዝቡ ነው፤ ያዕቆብም የርስቱ ገመድ ነው። በምድረ በዳ በጥማት፣ የነፋስ ጩኸትም በሞላበት ውድማ አገኘው፤ ከበበው ተጠነቀቀለትም፤ እንደ አይን ብሌን ጠበቀው። ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ፣ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ፣ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፣ በክንፎቹም አዘላቸው። እግዚአብሔር ብቻውን መራው፤ ከእርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም።” (ዘዳግም.32፡9-12)  

በቀደመው
ዘመን በግብጽ ምድር የነበረውን የሕዝቡን መከራ በእውነት ያየ፣ ጩኸታቸውንም የሰማና ሥቃያቸውንም ያወቀ  እግዚአብሔር …  የባርነት ቀንበራቸውን ሰብሮ ከግብፃውያን እጅ ያድናቸው ዘንድ፣ ከጠላት እጅ አምልጠውና ከመከራቸው አርፈው በተትረፈረፈ በረከት ወደሚኖሩበት - ወተትና ማር ወደምታፈሰው፣ ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ ምድር የሚወስዳቸውን መንገድ ይመራቸው ዘንድ ወረደ። (ዘፀአት3፡8) …. እስቲ እዚህ ላይ አንዲት ጥያቄ እንጠይቅ፡- የሕዝቡን መከራ በእውነት ያየ፣ ጩኸታቸውንም የሰማ፣ ሥቃያቸውንም ያወቀ እግዚአብሔር እንዴት ወደ ግብጽ ወረደ???

“አሁንም ና፣ ሕዝቤን የእሥራኤል ልጆች ከግብጽ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ። ሙሴም እግዚአብሔርን፡- ወደ ፈርዖን የምሄድ የእሥራኤልንም ልጆች ከግብጽ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? አለው። እርሱም፡- በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም እንደላክሁህ ምልክትህ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብጽ ባወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ ለእግዚአብሔር ትገዛላችሁ አለ።” (ዘፀአት3፡ 10-12)


በግብጽ ምድር ሳለ በወንድሞቹ ላይ የደረሰውን መከራ ተመልክቶ ጥቃታቸውን ለመከላከል የገዛ ጉልበቱንና ብርታቱን በመጠቀም ግብፃዊውን የገደለው ሙሴ፤ ከፈርዖን ፊት ኮብልሎና እጅግ ትሁት ሆኖ የአማቱን የዮቶርን በጎች በሚጠብቅበት በምድያም ምድር ነበር እግዚአብሔር ለዚህ የከበረ ተልዕኮ የጠራው። በግብጽ ሳለ የነበረው ጉልበቱና ብርታቱ አሁን የለም። ስለዚህም፡- ወንድሞቹን ከግብጽ ያወጣ ዘንድ እግዚአብሔር በእርሱ እጅግ የላቀውን ኃይልና ብርታቱን ሊገልጥ ትክክለኛው ጊዜ ደርሶ ወደፈርዖን ሊልከው እንዳሰበ ሲነግረው “የእሥራኤልን ልጆች ከግብጽ የማወጣ እኔ ማን ነኝ??” ብሎ ነበር እግዚአብሔርን የጠየቀው። የአባቶቹ የአብርሐም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክም፡- “በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” አለው። የሕዝቡን መከራ ያየ፣ ጩኸታቸውንም የሰማ፣ ሥቃያቸውንም ያወቀ እግዚአብሔር፣ በጸናችና በበረታች ክንድ የባርነት ቀንበራቸውን ሰብሮ ከፈርዖን አገዛዝ ነጻ ያወጣቸው ዘንድ፣…. ሙሴን ላከው፣ የእሥራኤል ቅዱስ በሙሴ ወረደ!!!!!

“የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፣ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፣ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን እናገር ዘንድ፣ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ፣…. ልኮኛል።” (ኢሳ.61፡1-3)

“ጴጥሮስም አፉን ከፍቶ እንዲህ አለ፡- እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ በእውነት አስተዋልሁ። የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ። ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፣ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስ የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፣ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረና።” (ሥራ፣10፡34-38)

በአዳም ከሆነው በደልና መተላለፍ የተነሳ፣ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ከዲያብሎስና ከገዛ ሥጋቸው ቀንበር ሥር ሆነው በኃጢአትና በሞት የሚሰቃዩትን የሰው ልጆች መከራ ያየ እግዚአብሔር፣ ከዚህ ጽኑ እሥራትና መከራ ነጻ ያወጣቸው ዘንድ፣ በእርሱ መልክ ይኖር የነበረውንና እጅግ የሚወደውን አንድያ ልጁን የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት አካባቢ ወደዚህ ምድር ላከው። ሁሉን ወራሽ ያደረገውና ዓለማትን የፈጠረበት ይህ አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ ወደዚህ ምድር የመጣው፣ ቀድሞ በአባቱ ዘንድ በነበረው ክብር ሳይሆን፣ ስለ አባቱ ፈቃድ ሲል እጅግ ትሁት በመሆን ራሱን ባዶ አድርጎና ፍጹም ሰው ሆኖ ነበር። ለዚህም ነው በእግዚአብሔር ለተላከበት - ነፍሱን ስለሰው ልጆች ኃጢአት ቤዛ አድርጎ የመስጠትና ሰዎችን ሁሉ ከዲያብሎስ እሥራት ነጻ አውጥቶ ወደ እግዚአብሔር ክብር የመመለስ ዓላማ ብቁ ይሆን ዘንድ ፤ በሰላሳ ሶስት ዓመቱ በአጥማቂው ዮሃንስ እጅ ሲጠመቅ በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም የተቀባው።

የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ለ33 ½ ዓመታት በምድር ላይ ስለነበረው ቆይታ እጅግ በተለየና ጥልቅ በሆነ መንገድ የጻፈው “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር” ዮሐንስ ነው። ከዚህ በታች የተጠቀሱት የክርስቶስ የራሱ ቃላት ከዚሁ ወንጌል የተወሰዱ ናቸው።

“…..ነፍሴን ደግሞ አነሳት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታልሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሳት ሥልጣን አለኝ፤ ይህችን ትዕዛዝ ከአባቴ ተቀበልኩ።…… እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፣ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።….. እኔ ስለራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው…. የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁምና እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው።….. በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም፣ እኔን የሚያይ የላከኝን ያያል። በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሐን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቼአለሁ።…. እኔ ከራሴ አልተናገርኩምና ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትዕዛዝ ሰጠኝ። ትዕዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።….. እኔን ያየ አብን አይቶአል…. እኔ የምናገረው ቃል ከራሴ አልናገረውም፣ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፣ ባይሆንስ ስለራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ። …… እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”

በግብጽ ምድር የነበረውን ጩኸት ሰምቶ ሕዝቡን ከባርነት ቀንበር ነጻ ለማውጣት በሙሴ ወርዶ የነበረው እግዚአብሔር፤ ከዘላለም ዘመናት በፊት ያቀደውን ሰዎችን ሁሉ የማዳንና ወደክብሩ የመመለስ ዓላማ ይፈጽም ዘንድ፣ መንፈስ የሆነውና “የማይታይ አምላክ” የተባለው እግዚአብሔር በአንድያ ልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ወደዚህ ምድር ወረደ።እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ…. “ በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውም ይህንን እውነት ነው። ሙሴ በቀደመው የእግዚአብሔር ሃሳብ ላይ የሰለጠነውና የታመነው “እንደ ሎሌ” ነበር። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሁሉ ወራሽ፣ የሁሉም ጌታ ነውና እርሱ የእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ላይ እንደ ልጅ የታመነ ነው። ስለዚህም እግዚአብሔር በልጁ ይፈጽመው ዘንድ ያሰበውን ፈቃዱን ለማድረግ ከእርሱ ጋር (WITH Him) ነበረና “የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው” አለ። ደግሞም አብ በእርሱ (IN Him) እርሱም በአባቱ ነበረና፡- “እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ” በማለት መሰከረ። ስለዚህም የዘመናት ሃሳቡን ይፈጽም ዘንድ በልጁ ሆኖ ወደምድር የወረደው እግዚአብሔር፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ያደርግ ዘንድ የወደደውን ፈቃዱን ሁሉ ከፈጸመ በሁዋላ፣ ከሙታን ባስነሳው ከልጁ ጋር በልጁም ሆኖ አረገ - በክብር ከፍ ከፍ አለ።

“አምላክ (Elohim) በእልልታ፣ እግዚአብሔር (Jehovah) በመለከት ድምጽ አረገ።” (መዝ.47፡5)

በዚህ የቆሬ ልጆች መዝሙር የተገለጠው ጥልቅ የመለኮት ሃሳብ ይህን መልእክት ለሚያነቡ ሁሉ የተገለጠ እንዲሆን ጸሎቴ ነው። በዚህ መዝሙር ላይ የምናገኛቸው ሁለት ስሞች እንዲሁ ተለያይተው የተቀመጡ አይደሉም። በአማርኛችን “አምላክ” ተብሎ የተጠቀሰው ቃል የሒብሪው አቻው “ኤሎሂም” ተብሎ የሚታወቀውና በትክክል ወደ አማርኛችን ብንመልሰው “አምላክ” ከሚለው የነጠላ መጠሪያ ስም ይልቅ “አማልክት” የሚለውን ከአንድ በላይ ለሆኑ አካላት የምንጠቀምበትን ቃል ይሰጠናል። ይህን ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንውሰድ፡- ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” በማለቱ ከአይሁድ ለደረሰበት ተቃውሞ፡- “መጽሐፉ ሊሻር አይችልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት (ኤሎሂም) ካላቸው፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፡- ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?” በማለት የሰጠው መልስ ቀድሞ በመጽሐፋቸው እንዲህ ተብሎ የተጻፈውን በመጥቀስ ነበር፡-
 
“እግዚአብሔር በአማልክት (ሒብሪው ‘ኤል’ - ኃያላን) መካከል ቆመ፣ በአማልክትም (ኤሎሂም) መካከል ይፈርዳል።……. አኔ ግን፡- አማልክት (ኤሎሂም) ናችሁ፣ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤ ነገር ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ፣ ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ አልሁ። God standeth in the congregation of the mighty; he judgeth among the gods…. I have said, Ye are gods; and all of you are children of the most High. KJV (መዝ.82፡1 -6)

እንግዲህ በመለከት ድምጽ ከእግዚአብሔር(Jehovah) ጋር ያረጉት አማልክት(Elohim) የልዑል ልጆች ሁሉ ሲሆኑ፣ በእነዚህ ልጆች መካከል ቀዳሚና ራስ የሆነው ግን “ከሙታንም በኩር” የተባለው የሕያው እግዚአብሔር አንድያ ልጅ ጌታ ኢያሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ “የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ” ነው። ጌቶችና ነገሥታት የተባሉት፣ መከራውን የተካፈሉና ከእርሱ ጋር አብረው የሚንግሡት “የልዑል ልጆች” እንደሆኑ ያስተዋልን ስንቶች እንሆን??? እርሱ በነዚህ ብዙ ወንድሞቹ መካከል በኩር ሆኖ የቤተ ክርስቲያን ማለትም የአካሉ ራስ ሲሆን፣ እግዚአብሔርም “የክርስቶስ ራስ” እንደሆነ በመጽሐፋችን በግልጽ የተጻፈ ነው። (1ቆሮ.11፡3)  እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሳውና በቀኙ ሲያስቀምጠው፣ ከእርሱ ጋር አብሮ ያስነሳቸውና በሰማያዊም ስፍራ ከክርስቶስ ጋር ያስቀመጣቸው ብዙ ልጆች እንዳሉ ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ቅዱሳን በጻፈው መልእክቱ ውስጥ እንዲህ ገልጦታል፡-
“ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ፣ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፤ በጸጋ ድናችሗልና፣ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ፣ ከእርሱ ጋር አስነሳን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን” (ኤ.ፌ.2፡4-7)

የክብር አባት፣ የጌታችንም የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ፣ በልጁም በኩል የገለጠውን ዘላለማዊ ሃሳቡንም ለመረዳት እንድትችሉ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲስጣችሁ እለምናለሁ። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን!!!! 

 

Tuesday, October 29, 2013

በነገር ሁሉ ወንድሞቹን መሰለ!!!

"እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም። ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።" ዕብ.214-18

ጌታ
ኢየሱስ ክርስቶስ የመላእክትን ሳይሆን የአብርሃምን ዘር መያዙና በነገር ሁሉ ወንድሞቹን መምሰሉ ምክንያት፤ በነገር ሁሉ እንደወንድሞቹ ለመፈተን ነው። በነገር ሁሉ እንደወንድሞቹ መፈተኑ ደግሞ፤ የዕብራውያን ጸሐፊ እንደነገረን፡- እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው እንዲችል ነው። የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀክህነት መሠረቱም ይኸው በነገር ሁሉ ወንድሞቹን መምሰሉና፣ በነገር ሁሉ እንደወንድሞቹ መፈተኑ ነው!!

"እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን እምነታችንን እንጠብቅ። ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ (was in all points tempted just as we are, yet without sin.) በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ" ዕብ.414-16

እዚህ
ላይ ለብዙዎች አእምሮ የሚከብድ ቢሆንም አንድ ነገር አጥርተን እንይ፤ "ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው" የሚለው የአማርኛው አገባብ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአት እንዳልተፈተነ አስመስሎታል። ነገር ግን ትክክለኛው የቃሉ አገባብ "እርሱ በነገር ሁሉ እንደ እኛ ቢፈተንም ኃጢአትን ግን አላደረገም" የሚል ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስም ከዚሁ ሃሳብ ጋር የሚመሳሰል ነገር ተናግሯል፡-
"የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ" 1ጴጥ.221-23

አንድን
ተፈጥሮአዊ ማነንት ወይም ባህሪይን የሚወስነው ዘር ነው። እርሱ በድንግሊቱ ማሕጸን የአብርሐምን ዘር ይዞ የመወለዱ ምሥጢር ለእግዚአብሔር የሚተው ሆኖ፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን የመምሰሉ ምክንያት ግን የተካፈለው በእርግጥ የአብርሃምን ዘር በመሆኑ ነው። በዚህ ዘር ውስጥ ሰውን ሰው ሊያሰኙ የሚችሉ ባህሪያት ሁሉ አሉ። የዕብራውያን ጸሐፊ “የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸው” የማለቱም ምሥጢር ይኸው ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በነገር ሁሉ እንደእኛ የተፈተነው ከተካፈለው የሥጋና ደም ባህሪይ የተነሳ ነው። እርሱ በነገር ሁሉ እንደ እኛ ተፈትኗል ስንል የእኛ ፈተና ምንድነው? አንዳንዶች የክርስቶስን ፈተና ከረሃብና ከጥማት ጋር ብቻ ያያዙታል። ነገር ግን ዋናው ፈተናችን ካለን የሥጋና ደም ባህሪይ የተነሳ የምንፈተንባቸው ልዩ ልዩ የኃጢአት ፈተናዎች ናቸው። እነዚህ ፈተናዎች እያንዳንዳቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትም አልፈዋል። ነገር ግን እርሱ ለአንዱም ስንኳን አልተሸነፈም። ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ሥርየት የሚሆነው የእግዚአብሔር በግ ያለ ነውርና ያለነቀፋ የመሆኑ ምሥጢር፤ በተካፈለው ሥጋና ደም በኩል የመጣበትን የኃጢአት ፈተና ሁሉ በመስቀል ታግሶ ማሸነፉ ነው። "በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ" ያለበትም ምሥጢሩ ይኸው ነውዓለምና በዓለም ያለው ደግሞ፤ የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ስለ ገንዘብ መመካት - The pride of life መሆኑን ልብ ይሏል! ሴቲቱ በዔደን ገነት በነበረው እባብ የተፈተነችባቸው በሴቲቱም በኩል ፊተኛው አዳም ተፈትኖ የወደቀባቸው ፈተናዎችም እነዚሁ የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ስለ ገንዘብ መመካት - The pride of life ነበሩ። ዛሬ ለም ያለነው እኛም የምንፈተነው በእነዚሁ የጽድቅና የሕይወት ጠላቶች ነው።

"እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።" ዕብ.57-10

ከዘላለም
ሞት የመትረፋችንና የመዳናችን መሠረቱ የክርስቶስ ኢየሱስ መታዘዝ መሆኑን የምናውቅ ስንቶቻችን እንሆን? ወገኖቼ! መዳናችን እንዲሁ በተዓምር ወይም በመለኮታዊ ኃይልና ችሎታ፣ ወይም በአምላክ ይሁንታ የተፈጸመ ሳይሆን ***በመታዘዝ*** ነው። በአንዱ አለመታዘዝ ወደ ዓለም የገባው ኃጢአትና ሞት የተሸነፈውና ከዓለም የተወገደው በአንዱ መታዘዝ ነው። የፊተኛው አዳም አለመታዘዝ እውነተኛ አለመታዘዝ ከመሆኑም በላይ የኃጢአትና የሞትን መዘዝ በሰዎች ሁሉ ላይ አስከትላል፤ እንዲሁም የኋለኛው አዳም የኢየሱስ መታዘዝ ፍጹምና እውነተኛ መታዘዝ በመሆኑ የጽድቅና የሕይወት ምንጭ ሆኗል። መዳናችንን ለመፈጸም ክርስቶስ በሥጋው ወራት የተቀበለው መከራ እንዲህ ነው ተብሎ የሚገመት አይደለም። ነውርና ነቀፋ የሌለው የኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ ራሱን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ፤ በተካፈለው ሥጋና ደም በኩል የሚመጣበትን ፈተና ሁሉ ማለፍና ማሸነፍ ነበረበት። የክርስቶስ መከራ በአይሁድ ካህናትና በሮማውያኑ ወታደሮች እጅ ተላልፎ ሲሰጥ በእንጨት ላይ የተቀበለው መከራ ብቻ አልነበረም። ይሄ የመከራው ጫፍና ፍጻሜ እንዲሁም ውጫዊ መገለጫ ነው። ነገር ግን ክርስቶስ በሥጋ ባሳለፋቸው ዓመታት ሁሉ በሥጋና በደም የሚመጡትን ፈተናዎች ለማለፍና መታዘዙን ለመፈጸም መከራን ተቀብሏል። ለዚህም ነው በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን ያቀረበው። ምንም ልጅ ቢሆን ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተምሯል። እስከ መስቀል ሞት የደረሰው መታዘዙ ደግሞ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ የመዳናችንን በር ከፍቷል!!


"ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።"

“ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና"

በዚህ ዓለም በሥጋ ሳለን ክፉውን አሸንፈን የተሰጠንን የዘላለም ሕይወት ተስፋ የመውረሳችን አለኝታ፤ በነገር ሁሉ እኛን መስሎ፣ በሁሉ እንደእኛ ተፈትኖና ድል ነስቶ በሰማያት በግርማው ቀኝ የተቀመጠው ዘላለማዊ ሊቀ ካህን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ” በማለት ተስፋን የሰጠው እርሱ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ ነው። እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች የሆንን ሁላችን የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነውን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስን ተመልክተን ከፊታችን ያለውን ሩጫ በእምነት እንሩጥ፣ እርሱ ነውርን ንቆ፣ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሶ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና!! (ዕብ.12፡1-2)  

Thursday, July 11, 2013

መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ!!


“እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና። በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ” ኢሳ.56፡4

የአዲስ ኪዳኑ የእግዚአብሔር ቤትና መቅደስ፤ ወይም የእግዚአብሔር ከተማና ቅጥር እንደቀደመው ኪዳን በሰው እጅ የተሰሩ ወይም የታነጹና የተገነቡ የሰው እጅ ሥራዎች አይደሉም። ዛሬ እግዚአብሔር ያለው መቅደስ ወይም ቤት ወይም ከተማና ቅጥር አንድ ነው። እርሱም በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተቀደሰው፣ በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ማለትም፤ "አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ" በሚለው አንድ እምነት ላይ የቆመውና፣ በክርስቶስ ባለው ሕይወት እግዚአብሔርን ለመምሰል በቅዱስ ቃሉና በቅዱስ መንፈሱ እየታነጸና እየተሰራ ያለው የእግዚአብሔር ሕዝብ ነው። ይህም በሐዋርያቱ ትምሕርት ላይ በግልጽ ተጽፎ ይገኛል።

"በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ" ኤፌ.2፡20-22

"በሰውም ወደ ተጣለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደ ሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ፥እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ" 1ጴጥ.2፡4-5

የዚሁ የእግዚአብሔር ቤት፣ መቅደስ፣ ከተማና ቅጥር ማንነት በተለይ በራዕይ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፎች ላይ እጅግ ጥልቅና ድንቅ በሆነ መንገድ ተገልጧል። በቀደመው ኪዳን በነበረችው የኢየሩሳሌም ከተማና ቅጥርዋ ምሳሌነትና አስረጂነት ለዮሃንስ በተገለጠለት በዚህ ድንቅ ራዕይ፤ ሰማያዊቱ፣ አዲሲቱና ቅደስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌምና ቅጥርዋ በተለያዩ የከበሩ ድንጋዮች ታንጸውና ተገንብተው ይታያሉ። የዚችን ሰማያዊ ከተማ ማንነት ለዮሃንስ ይገልጥለት ዘንድ የተላከው መልአክ የተናገረው ቃል፤ ዛሬ በአብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች አእምሮ ውስጥ ያለውን አስተሳሰብና እውቀት ፈጽሞ ከሥሩ የሚንድ ነው። ለብዙዎች አዲሲቱና ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም በአንድ ባልታወቀ ሩቅ ሰማይ ላይ እግዚአብሔር ለእነርሱ እየሰራት ያለችና፣ ከሞቱ ወይም “ከተነጠቁ” በኋላ ዘላለማዊ ኑሮቸውን የሚጀምሩባት ከተማ ናት። በመልአኩ የተገለጠው ቃል ግን "ከተማይቱ እናንተ ናችሁ" ይላቸዋል።

"ሰባቱም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ። ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤ ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፥ አሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ፥ የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር። በምሥራቅ ሦስት ደጆች፥ በሰሜንም ሦስት ደጆች፥ በደቡብም ሦስት ደጆች፥ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ። ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር" ራዕ.21፡9-14

የበጉ ሚስትና ሙሽራይቱ የተባለችው፤ ቤተክርስቲያን እንደሆነችና የክርሰቶስ ቤተክርስቲያንም በሰው እጅ የተሰሩ ሕንጻዎች ሳይሆኑ ራሳቸው መሆናቸውን ብዙዎች ይረዳሉ። ይቺ የበጉ ሚስትና ሙሽራይቱ የተባለችው ቤተክርስቲያን አዲሲቱ ኢየሩሳሌምና ቅደስቲቱ ከተማ እንደሆነች የሚያስተውሉት ግን ጥቂቶች ናቸው። ዛሬ የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች እነርሱ እንደሆኑ፣ የእግዚአብሔር ቤት ለመሆን እየታነጹ ያሉትም ሕያዋን ድንጋዮች ራሳቸው እንደሆኑ የሚረዱት ክርስቲያኖች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፤ ነገር ግን አዲሲቱ ኢየሩሳሌም - ቅደስቲቱ ከተማ የታነጸችባቸው የከበሩ ድንጋዮች እነርሱ ራሳቸው መሆናቸውን የሚረዱ በጣም ጥቂቶች ናቸው። (ከተማይቱና ቅጥሯ የታነጹባቸው ልዩ ልዩ የከበሩ ድንጋዮች፣ በቅዱሳኑ የእግዚአብሔር ልጆች የሚገለጠው የመለኮት ባህሪይ ምሳሌዎች ናቸው)

***ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ

***የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ

ነገር ግን እጅግ ልንረዳው የሚያስፈልገን አንድ ዋና ነጥብ አለ፤ ይኸውም በዚሁ የራዕይ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጠው ርኩሰትና ውሸት የሚያደርግ ሁሉ ወደዚች ከተማ አይገባም፣ ወይም የዚች ከተማ ክፍል ሊሆን አይችልም። የዛሬ መዘጋጀታችንና በክርስቶስ ባለ ሕይወት ፍጹማን ለመሆን መሰራታችንም ጥቅሙ እዚህ ላይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስያስ ወንድሞቹ እንደጻፈው፣ በማስተማር፣ በመገሰጽ፣ በመምክር ይተጋና ይጋደል የነበረው በክርስቶስ ፍጹም የሚሆንን ሰው ለማቅረብ ነበር። "ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው፣ በደጆችዋም ወደከተማይቱ ለመግባት ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁአን ናቸው" ተብሎ እንደተጻፈውም፤ ዓለምንና በዓለም የሚገኘውን ትርፍ ሁሉ እየተውን፣ በኑሮአችንና በአካሄዳችን ከሚገለጥ የዚህ ዓለም ዕድፍና ርኩሰት ራሳችንን እያነጻንና፣ ጌታችንና አምላካችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በእምነትና በመታዘዝ እስከፍጻሜው ድረስ የመከተላችን ውጤት ነው በእርግጥ የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች፣ ሕያዋንና የከበሩ ድንጋዮች፣ የቅድስቲቱም ከተማ አባላት ወይም ክፍሎች የሚያደርገን። "ድል መንሳት" የሚባለውም ይኸው ነው። በራዕይ መጽሐፍ ሁለተኛውና ሦስተኛው ምዕራፎችም ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት በላካቸው መልእክቶች መጨረሻ ላይ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ወይም ከቤተክርስቲያን መካከል የእምነት ሩጫቸውንና ተጋድሎአቸውን ድል በመንሳት ለሚፈጽሙ የእግዚአብሔር ልጆች የተሰጠው ተስፋ ተጽፎ እናገኛለን። የዚህ መልእክት ዋና ዓላማም ዛሬ ይህንን መልእክት የሚያነቡ ቅዱሳን ሁሉ መንፈስ ለእነርሱ የሚለውን ለመስማት ጆሮአቸውን እንዲሰጡ ለማበረታት ነው።

=> መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ።

=> እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጐዳም።

=> መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፥ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፥ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎአል።

=> ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፥ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፥ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፤ የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

=> ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

=> ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፥ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

=> እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

***እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና። በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ***

እግዚአብሔር አምላኬና አባቴ ሆይ!! በከበረውና አንድያ በሆነው ልጅህ በክርስቶስ ኢየሱስ እኛን የፈጠርክበት፣ ከወደቅንበት ያነሳህበት፣ ከዚህ በርኩሰትና በጥፋት ከተሞላ ዓለም መካከል እኛን ለይተህ የጠራህበትና የዋጀህበት፣ ያነጻህበትና የቀደስክበት ዓላማህ እንዴት ግሩም ነው። እባክህን!! በዚህ ክፋትና ርኩሰት በሞላበት ዓለምና በተለይም በዚህ አስጨናቂ ዘመን ውስጥ የምንኖረውን እኛን ልጆችህን አስበን!! በክርስቶስ ኢየሱስ አንተን እየመሰልን የምንኖርበትንም ጸጋ ጨምርልን!! እንደተሰጠንም ተስፋ ድል ነስተን የመንግሥትህ ወራሾች፣ የቅድሰቲቱ ከተማ ክፍሎች፣ የመለኮታዊ ባህሪህም ተካፋዮች እንድንሆን እርዳን!! በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን!!!!

Wednesday, March 20, 2013

የጽድቅ ዘር - የጽድቅ ፍሬ!!!



“ጽድቅ” ማለት በእግዚአብሔር ሚዛን የሆነ ትክክለኛ ኑሮ ማለት ነው።ጻድቅ” የሚባለውም እግዚአብሔርትክክል ነው” በሚለው መንገድ ኑሮውንና ሕይወቱን የሚመራ ነው። እግዚአብሔር በቀደመው ዘመን እነ ኢዮብን "ጻድቅ" ያለበትንና ኋላም በክርስቶስ በገለጠው የራሱ ጽድቅ መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ ማወቁ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ከሰጠው ሕግ በፊት ይኖሩ የነበሩት እነኢዮብ፣ ኖህና አብርሃምን የመሳሰሉ አባቶች "ጻድቃን" ተብለው የተጠሩት፣ እነርሱ ይኖሩበት በነበረው ዘመን በኖሩት ኑሮ ልክና መጠን ነው። ማለት ግን ኑሮአቸው በእግዚአብሔር ጽድቅ ልክና መጠን ነበር ማለት አይደለም። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ጽድቅ የተገለጠው በክርስቶስ ስለሆነ ነው።

“አሁን
ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል። እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው…” ሮሜ.3፡21-22

ሕግ የተሰጣቸውን እስራኤላውያንንም ስንመለከት በእነርሱ እንዲገለጥ የተፈለገው ጽድቅ ሕጉ በሚጠይቀው መጠንና ልክ ብቻ ነበር። ይህም ቢሆን ኋላ በክርስቶስ ከተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ ጋር እጅግ ሰፊ የሆነ ልዩነት አለው። ለምሳሌ፡- ሕጉ "አታመንዝር" ሲል፡- ከአንዲቷ ሚስትህ ውጪ ከሌላ ሴት ጋር አትተኛ ማለቱ ነው። ነገር ግን በዚሁ አታመንዝር በሚለው ትዕዛዝ ላይ በክርስቶስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ "ወደሴት ያየ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል" ይላል። በሕጉ የተገለጠው ትክክለኛ ኑሮ የሚወዱንን መውደድ፣ የሚጠሉንን መጥላት ነው። ነገር ግን በክርስቶስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ፣ ጠላቶቻችንን እንድንወድ፣ የሚረግሙንን እንድንመርቅ፣ ለሚጠሉንም መልካም እንድናደርግ፣ ስለሚያሳድዱን እንድንጸልይ... ያስችለናል።
ስለዚህ በኢዲሱ ኪዳን ስለተገለጠውና በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ብቻ ስለሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ወይም ትክክለኛ ኑሮ ስናስብ፣ ሰው በራሱ ዐቅምና ብቃት ፈጽሞ ሊኖረው የማይችል እጅግ የከበረና የላቀ የጽድቅ ሕይወት ነው። ይህ "የእግዚአብሔር ጽድቅ" ማንም "የእኔ" ሊለው አይችልም። የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት በዚህ የጽድቅ ሚዛን ሲለካ ጎደሎ ነው። ከሥጋና ከደም ከተወለዱ የሰው ልጆች መካከል ማንም በዚህ ጽድቅ ልክ የኖረ የለም። ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል፡- "ጻድቅ የለም - አንድ ስንኳ" በማለት አስረግጦ የሚነግረን። በዚህ በክርስቶስ በተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ ሚዛን ላይ ብናስቀምጠው፣ ኢዩብም ጻድቅ አይደለም፣ አብርሃምም ሆነ ኖህ፣ ሙሴም ሆነ ዳዊት.... ተክልዬም ሆኑ አቡዬ ጻድቅ አይደሉም። "ጻድቅ የለም - አንድ ስንኳ!!!!!!!!"
ስለዚህ እግዚአብሔር ይሄንን የራሱን ጽድቅ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ለማኖርና ለመግለጥ ነው አንድያ ልጁን በሥጋ ወደዚህ ዓለም የላከው። በክርስቶስ እምነት የምንካፈለው የእግዚአብሔርን የራሱን ጽድቅ ነው። ይህም ጽድቅ በእኛ ሕይወት የሚገለጥበት ሁለት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ጽድቅ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን በጸጋ ብቻ የሚገኝ ነጻ ስጦታ እንደሆነ አምነን የምንቀበልበትና የራሳችን የምናደርግበት ደረጃ ነው። ይህንን ደረጃ፡- Imputed righteousness ይሉታል። የጽድቅ ሕይወትና ኑሮ ገና በእኛ መገለጥ ሳይጀምር፣ በእግዚአብሔር ዓይንና አቆጣጠር ብቻ "ጻድቃን" ተብለን የምንጠራበትና የምንቆጠርበት ደረጃ ነው። "አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ፣ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት" የሚለው ቃል ለዚህ ሕያው እውነት ምስክር ነው። የእግዚአብሔር ጽድቅ በሥራ ሳይሆን፣ በእምነት ብቻ የሚገኝ ነው።  
"ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ ፤ነገር ግን የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው።" 1ቆሮ.1፡29-31
ክርስቶስ እርሱ ጽድቃችን ነው፤ የመጀመሪያው ነገር ይሄንን አምኖ መቀበልና በክርስቶስ ባለ እምነት ብቻ "ጻድቅ" ወይም "ቅዱስ" ተብሎ መጠራት ነው። እዚህ ላይ "ጻድቅ" ወይም "ቅዱስ" ተብሎ መጠራትና መሆን የተለያዩ ደረጃዎች ናቸው። ከመሆናችን በፊት መጠራታችን ወይም መቆጠራችን ከመቅደሙም በላይ ለመሆናችን መሠረት ነው። ይህም ገበሬው የስንዴውን መከር ከማጨዱና ከመሰብሰቡ በፊት አስቀድሞ ቅንጣቱን እንደመዝራቱ የሚቆጠር ነው። የጽድቅ ዘር የሆነው ክርስቶስ አስቀድሞ በእኛ ሕይወት ካልተዘራ የጽድቅ ፍሬ የሚባል ነገር የለም። የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ፡- ለፊሊጲስዩስ ቅዱሳን በጻፈው መልእክቱ ውስጥ ይህ እውነት ተገልጦአል፡-
"ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ።" ፊሊ.19-11

ስለዚህ በእምነት ከተቀበልነው የጽድቅ ዘር ክርስቶስ የተነሳ "ጻድቃንና ቅዱሳን" ተብለን መጠራታችን የመጀመሪያው ደረጃ ሲሆን፣ ይህ በእምነት የተቀበልነው የጽድቅ ዘር፣ የጽድቅ ፍሬ የሚሆንበት፣ ወይም በሕይወት አካሄዳችን የሚገለጥበት ደረጃ ደግሞ ሁለተኛው ነው። ይህንንም Imparted Righteousness ይሉታል። በእኛ ያለውን ክርስቶስና ሕይወቱን የምንካፈልበትና የምንኖርበት ደረጃ ነው። በእምነት "ጻድቃን እና ቅዱሳን" ተብለው የተጠሩት ያመኑ ክርስቲያኖች፣ ጽድቃቸውና ቅድስናቸው የሆነው ክርስቶስ በሕይወት አካሄዳቸው እንዲገለጥ፣ በነፍሳቸው ጥልቀት ውስጥ የተዘራው የጽድቅና የቅድስና ዘር - ክርስቶስ የኑአሮቸው ፍሬ እንዲሆን....  "ቅዱሳን ሁኑ፣ ትቀደሱ ዘንድ ፈልጉ፣ ሰውነታችሁን ቅዱስና ሕያው መስዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ...." እየተባሉ ዕለት - ዕለት ይማራሉ፣ ይመከራሉ፣ ይገሰጻሉ፣ ይበረታታሉ!! ይህም በሚገባ አርሶና ጎልጉሎ መልካሙን ዘር የዘራበትን መሬት እንደሚንከባከበው ገበሬ፣ የቃሉ አገልጋዮች የዕለት ተዕለት ሥራ ነው።

እግዚአብሔር በተለይ በወንድማችን ጳውሎስ በኩል በተሰበከው ወንጌል የገለጠው ምሥጢር አንድ ነው። እርሱም የጽድቅ ዘር የሆነው ክርስቶስ በእኛ ውስጥ መሆኑንና በሕይወት አካሄዳችንም የኑሮአችን ፍሬ ሆኖ የሚገለጠው ክርስቶስ ራሱ መሆኑን ነው። የተወደደው ሐዋርያ ይህንን የጽድቅ ዘር በወንጌሉ የዘራባቸውን ቅዱሳን “እናንተ የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ” እያለ፤ ክርስቶስ በእነሱ እስኪሳል ወይም ሕያው ሆኖ እስኪገለጥና የሕይወት አካሄዳቸው ደግሞም የኑሮቸው ፍሬ እስኪሆን ድረስ ዕለት ዕለትእንደ ትጉ ገበሬ አገልግሎቱን ይፈጽም ነበር። የተጋድሎውንም ዓላማ "በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰው ማቅረብ" ብሎታል። ይህም የመንፈሳዊው ገበሬ የድካሙ የመጨረሻ ውጤት ወይም ፍሬው ነው።

“ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ። ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል። ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። እኛም
በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው። ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ።” (ቆላ.1፡25-29)