by Tibebe Belay
|
"በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግስት ርቃችሁ, ለተስፋውም ቃልኪዳን እንግዶች ሆናችሁ, በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ, ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያ-ለ-ክ-ር-ስ-ቶ-ስ ነበራችሁ" ኤፌ.2:12በክፍል 1 መልእክታችን በጥቂቱ ለማየት እንደሞከርነው, እግዚአብሔር ለእኛ ለሰው ልጆች የሰጠንና የወሰነልን የከበረ ሕይወት ክርስቶስ ነው:: ሓዋርያው ዮሃንስም በ1ኛ መልእክቱ ምዕራፍ አንድ ከቁጥር አንድ እስከ አራት ላይ እንዳመለከተን የዛሬ 2000 ዓመት አካባቢ የተገለጠው ከዘላለም ዘመናት በፊት በርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረውና እግዚአብሔር ለእኛ ያዘጋጀው ሕይወት ነው:: ይህ ሕይወት የሚገኘው ደግሞ ከአብና ከልጁ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሚኖረን ሕብረት እንደሆነ በግልጽ ተጽፎ እናገኛለን:: እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት እንዲሁ ሰቶናል:: ይህም ሕይወት ያለው ደግሞ በልጁ ነው:: ለዚህም ነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ "በእግዚአብሔር እመኑ - በእኔም ደግሞ እመኑ... አባት ልጁን ይወዳል, ሁሉንም በእጁ ሰቶታል:: በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው:: በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም... እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ, አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይቺ የዘላለም ሕይወት ናት.." እያለ ሲናገር የምናገኘው::
ከላይ ሓዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ የምናነበው ቃል, የዛሬ 2000 ዓመት አካባቢ ክርስቶስ በስጋ ከመምጣቱ በፊት ወይም እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት የወሰነልን የከበረ ሕይወት ከመገለጡ በፊት እንኖር የነበረበትንና "የእግዚአብሔር ሕዝብ" በተባሉት እስራኤላውያን ዘንድ "አሕዛብ" እየተባልን እንጠራበት የነበረበትን ሁኔታ የሚያመለክት ነው:: በዚህ ዓለም ተስፋ አጥተን እንኖር የነበረው ከእግዚአብሔር ተለይተን ያ-ለ-ክ-ር-ስ-ቶ-ስ ያለ ሕይወት - ሙታን ከመሆናችን የተነሳ ነው:: በእርግጥ ዛሬ ደግሞ በተራችን የዘላለምን ሕይወት ተስፋ በክርስቶስ ኢየሱስ አግኝተን ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት በሆነልን በእኛ ዘንድ "አሕዛብ" ተብለው የሚጠሩት "ከእግዚአብሔር ተለይተው ያ-ለ-ክ-ር-ስ-ቶ-ስ" የሆኑት ሁሉ ናቸው:: እነዚህ ያለክርስቶስ "ያለ እግዚአብሔር ሕይወት" የሚኖሩት አሕዛብ ዛሬ ያሉበትን ሁኔታ ሓዋርያው እንዲህ በማለት ገልጾታል:: "እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከ እንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ: በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ:: እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳናነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ: ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ: ደንዝዘውም በመመኘት ርኩሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ:: እ-ና-ን-ተ ግ-ን ክ-ር-ስ-ቶ-ስ-ን እንዲህ አልተማራችሁም..." ኤፌ.4:17-24
ክርስቶስ ሕይወታችን ነው ማለታችን; በመንፈሳችን ከፍታ ላይ የሚኖርና በነፍሳችን ማሕጸን የተጸነሰ የዘላለም ሕይወት - የጽድቅ, የቅድስና, የጥበብ, የእውቀት...ሁሉ ምንጭ ነው ማለታችን ነው:: ክርስቶስ ሕይወታችን ነው ስንል; በመጽሓፍ ቅዱሳችን ውስጥ "የመንፈስ ፍሬ" ተብሎ የተዘረዘረው የጽድቅ ሕይወት የሚገኝበት ዘር ነው ማለታችን ነው:: (ፊሊ.1:9-11) በሰውነታችን ሁሉ የሚዘዋወረው ደም በምድር ላይ በምንኖርበት ዘመን ሁሉ ለስጋችን የሕይወት - የኃይልና ጉልበት ምንጭ እንደሆነ ሁሉ; ክርስቶስም ለመንፈሳዊ ኑሮአችን የሕይወትን የቅድስና ምንጭ, የመንፈስ ኃይልና የጽድቅ ጉልበት ነው:: እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ሰውሮት የነበረው, በነቢያት የተነገረውና, በወንጌል የተሰበከው ደግሞም የዛሬ 2000 ዓመት በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት የገለጠው የከበረ ምሥጢር ይህ ነው:: "ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእኛ ዘንድ (in us) መሆኑ ነው" (ቆላ.1:27)
No comments:
Post a Comment