“ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና the lust of the flesh, የዓይን አምሮት the lust of the eyes, ስለ ገንዘብም መመካት the pride of life, ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።” 1ዮሃ.2፡15-16
በደርግ ዘመን “ሦስቱ ጣምራ ጠላቶቻችን” የሚል አባባል እንደነበር አስታውሳለሁ። ደርግ የነገረን “ሦስቱ ጣምራ ጠላቶቻችን” ኢምፔሪያሊዝም፣ ፊውዳሊዝምና ቢሮክራቲክ ካፒታሊዝም ነበሩ። ነገር ግን የሰው ልጅ በእግዚአብሔር እጅ ተበጅቶ በዔደን ገነት ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የሚፈትኑትና ከእግዚአብሔር ፈቃድና ሃሳብ እንዲጎድል እየጠለፉ የሚጥሉት ሦስት ጣምራ ጠላቶች አሉት። እነርሱም ከላይ በምናነበው መልእክት ውስጥ የተገለጡት፤ የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አእምሮትና እኔነት ናቸው። “እኔነት” ወይም በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱሳችን “ስለገንዘብ መመካት” ተብሎ የተተረጎመውን ሃሳብ ስናብራራው፤ በዚህ ሕይወት ባለን ነገር ወይም በራስ የመተማመን፣ የመኮፈስና ከፍ-ከፍ የማለት፣ ገደብ የለሽ ሃብትና ክብር፣ ከዚህ ዓለም የሆነውን ጥበብና እውቀት የማግኘትና ሁልጊዜም ለማግኘት የመጓጓት ፍላጎት እንደሆነ እንረዳለን።
“ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።” ሮሜ.8፡6
እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ሰው በራሱ መልክና ምሳሌ ፈጥሮና አበጃጅቶ በዔደን ገነት ሲያስቀምጠው ሁለት መንገዶችን በፊቱ አኑሮ ነው። (((በምድር ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ መካከል ለይቶ ርስት የሰጣቸውን እሥራኤላውያንን ወደርስታቸው ለማስገባት በምድረ በዳ በመራቸውም ጊዜ የእሥራኤል አምላክ እነዚህን ሁለት መንገዶች በፊታቸው አኑሮ እንደነበር በዘዳ.30፡19-20 ላይ ተጽፎ እናገኛለን))) በዔደን ገነት መካከል በነበረው የሕይወት ዛፍ ተምሳሌትነት የተገለጠውና እግዚአብሔርን የሕይወትና የህልውና ማዕከል በማድረግ፣ ለቃሉም በመኖርና በመታዘዝ፣ ወይም በመንፈስ በመመላለስ ወደሚገኘው የማይጠፋ ሕይወት የሚወስደውና፤ መልካሙንና ክፉውን በሚያስታውቀው ዛፍ ተምሳሌትነት የተገለጠውና ራስን የህልውና ማዕከል በማድረግ፣ በራስ ፈቃድና ሃሳብ ወይም እንደ ሥጋ ፈቃድና ሃሳብ እንደወደዱ በመመላለስ ከእግዚአብሔር ወደመለየትና ወደሞት የሚወስደው መንገዶች ናቸው። በሴቲቱና በእባቡ መካከል በተደረገው ‘ውይይት’ የተቀሰቀሰውና ኋላም አሸንፎ የወጣው ሁለተኛው መንገድ ነው። “ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ (የሥጋ ምኞት)፣_ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ (የዓይን አምሮት)፣ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ (እኔነት) አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።” (ዘፍ.3፡6)
የሰው ልጅ በፊተኛው ሰው ኣዳም አለመታዘዝ ወይም በእነዚህ ሦስቱ ጣምራ ጠላቶቹ አማካኝነት ከእግዚአብሔር ሕይወት ተለይቶ ወድቆበት ከነበረው የሞትና የጨለማ ጉድጓድ የወጣው፤ በኋለኛው (በመጨረሻው) ኣዳም መታዘዝ ነው። የኋለኛው አዳም መታዘዝ በይፋ መታየትና መገለጥ የጀመረው ደግሞ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው” የተባለው የቀደመው እባብ በዔደን ገነት የፊተኛውን ሰው ፈትኖ ከሕይወት መንገድ እንዳሳተው፣ ለአርባ ቀንና ሌሊት በጾምና በጸሎት በደከመበት ምድረ በዳ ኢየሱስ ክርስቶስንም ፈትኖ ለመጣል ያደረገው ሙከራ በከሸፈበት ወቅት ነው። በዚህ የምድረበዳ ፈተናም ወቅት በፈታኙ በኩል ለኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦለት የነበረው ፈተና፤ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር እጅ ተበጅቶ በዔደን ገነት ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የሚፈትኑትና ከእግዚአብሔር ፈቃድና ሃሳብ እንዲጎድል እየጠለፉ የሚጥሉት ሦስቱ ጣምራ ጠላቶቹ ማለትም የስጋ ምኞት፣ የዓይን ዓምሮትና እኔነት ነበሩ። (ማቴ.4፡1-11 ይነበብ)
“በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” (ዮሃ.16፡33)
እውነተኛው ክርስትና ሲገባን በእነዚህ ሦስቱ ጣምራ ጠላቶቻችን የሚደርስብንን ፈተና የሚያህል ሌላ ታላቅ መከራ በዚህ ዓለም ላይ እንደሌለ እንረዳለን። በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው” የተባሉት፣ ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ያነጹት ናቸው። በበጉ ደም ታጥቦ የሚነጻው ልብሳችን ደግሞ በዚህ ዓለም በሚገኝ ነውርና እድፍ፣ ማለትም በሥጋ ምኞት፣ በዓይን አምሮትና በእኔነት ያደፈው ማንነታችን ነው። በበጉ ደም ታጥቦ መንጻት ማለትም፣ በድካማችንና በኃጢአታችን ከምንወነጀልበት የዲያብሎስ ክስ ነጻ ከመውጣት ጀምሮ፣ የሥጋችንን ድካም ምክንያት አድርጎ በእኛ የሚሰራውን የኃጢአት ኃይልና ሕግ ፈጽመን ድል እስከምናደርግበትና እስከምናሸንፍበት፣ በዚህም የሥጋ ሥራ ከተባሉት የሞት አገልጋዮች አርነት ወጥተን በመንፈስ ፍሬ ወይም በክርስቶስ ሕይወት ሙላት እስከምንሞላበት የሕይወት ከፍታ የሚደርስ ነው። ዓለምን ማሸነፍና “ድል ነሺ” የመባል ትርጉሙም ይኸው ነው።
“ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።” (ገላ.6፡14)
እኛ ለዓለም - ዓለምም ለእኛ የተሰቀለበት የክርስቶስ መስቀል፣ ዓለምንና በዓለም ያሉትን ማለትም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን ዓምሮትንና እኔነትን ከእኛ ፈጽሞ ያስወገደና የሚያስወግድ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። አንድ ክርስቲያን የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ከእርሱ ሕይወት ጋር የተያያዘበትን ሙሉውን እውነት ካላየ፣ እግዚአብሔር በሕይወቱ ሊፈጽመው ያሰበውን የከበረ ዓላማ መገንዘብ ካለመቻሉም በላይ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የሰጠውን የከበረ ሕይወት በሙላት ለሊያጣጥም አይችልም። ክርስቶስ በመስቀል ላይ የከፈለው ቤዛነታችን እርሱም የበደላችን ስርየት ከእግዚአብሔር ጋር የታረቅንበት ብቸኛው መንገድ እንደመሆኑ፣ እኛም ከክርስቶስ ሞት ጋር መተባበራችን ወይም አሮጌው ሰዋችን ከክርስቶስ ጋር መሰቀሉን መረዳታችን ዓለምንና በዓለም ያለውን ሁሉ የምናሸንፍበት የድላችን ዋስትና ነው። የክርስቶስ ሕይወት ሕይወታችን የሚሆነው ሞቱም ሞታችን ከሆነ ብቻ ነው። ለዚህም ነው የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ፡- “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው” ያለው። (ገላ.2፡20)
ክርስትና የምንለው የከበረ ኑሮና ሕይወት በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምንኖረው ኑሮ ነው። ወይም በሌላ አገላለጥ ክርስትና እኛ የምንኖረው ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጅ በእኛ የሚኖረው ኑሮ ነው!! ይህም እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ሰውሮት የነበረው፣ ልጁ በሥጋ በመምጣቱ ለቅዱሳኑ ሁሉ የገለጠው የከበረ ምሥጢር ነው። ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእኛ ዘንድ (Christ IN us) መሆኑ ነው። ዓለምንም የሚያሸንፈው፤ ማለትም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና እኔነት ከተባሉት ክፉ ጠላቶቻችን አርነት የሚያወጣን በእኛ ያለው ክርስቶስ እርሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የሚመሰክረው እምነታችን ነው።
“ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?” 1ዮሃ.5፡4-5
No comments:
Post a Comment