Wednesday, March 20, 2013

የጽድቅ ዘር - የጽድቅ ፍሬ!!!



“ጽድቅ” ማለት በእግዚአብሔር ሚዛን የሆነ ትክክለኛ ኑሮ ማለት ነው።ጻድቅ” የሚባለውም እግዚአብሔርትክክል ነው” በሚለው መንገድ ኑሮውንና ሕይወቱን የሚመራ ነው። እግዚአብሔር በቀደመው ዘመን እነ ኢዮብን "ጻድቅ" ያለበትንና ኋላም በክርስቶስ በገለጠው የራሱ ጽድቅ መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ ማወቁ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ከሰጠው ሕግ በፊት ይኖሩ የነበሩት እነኢዮብ፣ ኖህና አብርሃምን የመሳሰሉ አባቶች "ጻድቃን" ተብለው የተጠሩት፣ እነርሱ ይኖሩበት በነበረው ዘመን በኖሩት ኑሮ ልክና መጠን ነው። ማለት ግን ኑሮአቸው በእግዚአብሔር ጽድቅ ልክና መጠን ነበር ማለት አይደለም። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ጽድቅ የተገለጠው በክርስቶስ ስለሆነ ነው።

“አሁን
ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል። እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው…” ሮሜ.3፡21-22

ሕግ የተሰጣቸውን እስራኤላውያንንም ስንመለከት በእነርሱ እንዲገለጥ የተፈለገው ጽድቅ ሕጉ በሚጠይቀው መጠንና ልክ ብቻ ነበር። ይህም ቢሆን ኋላ በክርስቶስ ከተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ ጋር እጅግ ሰፊ የሆነ ልዩነት አለው። ለምሳሌ፡- ሕጉ "አታመንዝር" ሲል፡- ከአንዲቷ ሚስትህ ውጪ ከሌላ ሴት ጋር አትተኛ ማለቱ ነው። ነገር ግን በዚሁ አታመንዝር በሚለው ትዕዛዝ ላይ በክርስቶስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ "ወደሴት ያየ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል" ይላል። በሕጉ የተገለጠው ትክክለኛ ኑሮ የሚወዱንን መውደድ፣ የሚጠሉንን መጥላት ነው። ነገር ግን በክርስቶስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ፣ ጠላቶቻችንን እንድንወድ፣ የሚረግሙንን እንድንመርቅ፣ ለሚጠሉንም መልካም እንድናደርግ፣ ስለሚያሳድዱን እንድንጸልይ... ያስችለናል።
ስለዚህ በኢዲሱ ኪዳን ስለተገለጠውና በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ብቻ ስለሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ወይም ትክክለኛ ኑሮ ስናስብ፣ ሰው በራሱ ዐቅምና ብቃት ፈጽሞ ሊኖረው የማይችል እጅግ የከበረና የላቀ የጽድቅ ሕይወት ነው። ይህ "የእግዚአብሔር ጽድቅ" ማንም "የእኔ" ሊለው አይችልም። የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት በዚህ የጽድቅ ሚዛን ሲለካ ጎደሎ ነው። ከሥጋና ከደም ከተወለዱ የሰው ልጆች መካከል ማንም በዚህ ጽድቅ ልክ የኖረ የለም። ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል፡- "ጻድቅ የለም - አንድ ስንኳ" በማለት አስረግጦ የሚነግረን። በዚህ በክርስቶስ በተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ ሚዛን ላይ ብናስቀምጠው፣ ኢዩብም ጻድቅ አይደለም፣ አብርሃምም ሆነ ኖህ፣ ሙሴም ሆነ ዳዊት.... ተክልዬም ሆኑ አቡዬ ጻድቅ አይደሉም። "ጻድቅ የለም - አንድ ስንኳ!!!!!!!!"
ስለዚህ እግዚአብሔር ይሄንን የራሱን ጽድቅ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ለማኖርና ለመግለጥ ነው አንድያ ልጁን በሥጋ ወደዚህ ዓለም የላከው። በክርስቶስ እምነት የምንካፈለው የእግዚአብሔርን የራሱን ጽድቅ ነው። ይህም ጽድቅ በእኛ ሕይወት የሚገለጥበት ሁለት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ጽድቅ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን በጸጋ ብቻ የሚገኝ ነጻ ስጦታ እንደሆነ አምነን የምንቀበልበትና የራሳችን የምናደርግበት ደረጃ ነው። ይህንን ደረጃ፡- Imputed righteousness ይሉታል። የጽድቅ ሕይወትና ኑሮ ገና በእኛ መገለጥ ሳይጀምር፣ በእግዚአብሔር ዓይንና አቆጣጠር ብቻ "ጻድቃን" ተብለን የምንጠራበትና የምንቆጠርበት ደረጃ ነው። "አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ፣ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት" የሚለው ቃል ለዚህ ሕያው እውነት ምስክር ነው። የእግዚአብሔር ጽድቅ በሥራ ሳይሆን፣ በእምነት ብቻ የሚገኝ ነው።  
"ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ ፤ነገር ግን የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው።" 1ቆሮ.1፡29-31
ክርስቶስ እርሱ ጽድቃችን ነው፤ የመጀመሪያው ነገር ይሄንን አምኖ መቀበልና በክርስቶስ ባለ እምነት ብቻ "ጻድቅ" ወይም "ቅዱስ" ተብሎ መጠራት ነው። እዚህ ላይ "ጻድቅ" ወይም "ቅዱስ" ተብሎ መጠራትና መሆን የተለያዩ ደረጃዎች ናቸው። ከመሆናችን በፊት መጠራታችን ወይም መቆጠራችን ከመቅደሙም በላይ ለመሆናችን መሠረት ነው። ይህም ገበሬው የስንዴውን መከር ከማጨዱና ከመሰብሰቡ በፊት አስቀድሞ ቅንጣቱን እንደመዝራቱ የሚቆጠር ነው። የጽድቅ ዘር የሆነው ክርስቶስ አስቀድሞ በእኛ ሕይወት ካልተዘራ የጽድቅ ፍሬ የሚባል ነገር የለም። የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ፡- ለፊሊጲስዩስ ቅዱሳን በጻፈው መልእክቱ ውስጥ ይህ እውነት ተገልጦአል፡-
"ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ።" ፊሊ.19-11

ስለዚህ በእምነት ከተቀበልነው የጽድቅ ዘር ክርስቶስ የተነሳ "ጻድቃንና ቅዱሳን" ተብለን መጠራታችን የመጀመሪያው ደረጃ ሲሆን፣ ይህ በእምነት የተቀበልነው የጽድቅ ዘር፣ የጽድቅ ፍሬ የሚሆንበት፣ ወይም በሕይወት አካሄዳችን የሚገለጥበት ደረጃ ደግሞ ሁለተኛው ነው። ይህንንም Imparted Righteousness ይሉታል። በእኛ ያለውን ክርስቶስና ሕይወቱን የምንካፈልበትና የምንኖርበት ደረጃ ነው። በእምነት "ጻድቃን እና ቅዱሳን" ተብለው የተጠሩት ያመኑ ክርስቲያኖች፣ ጽድቃቸውና ቅድስናቸው የሆነው ክርስቶስ በሕይወት አካሄዳቸው እንዲገለጥ፣ በነፍሳቸው ጥልቀት ውስጥ የተዘራው የጽድቅና የቅድስና ዘር - ክርስቶስ የኑአሮቸው ፍሬ እንዲሆን....  "ቅዱሳን ሁኑ፣ ትቀደሱ ዘንድ ፈልጉ፣ ሰውነታችሁን ቅዱስና ሕያው መስዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ...." እየተባሉ ዕለት - ዕለት ይማራሉ፣ ይመከራሉ፣ ይገሰጻሉ፣ ይበረታታሉ!! ይህም በሚገባ አርሶና ጎልጉሎ መልካሙን ዘር የዘራበትን መሬት እንደሚንከባከበው ገበሬ፣ የቃሉ አገልጋዮች የዕለት ተዕለት ሥራ ነው።

እግዚአብሔር በተለይ በወንድማችን ጳውሎስ በኩል በተሰበከው ወንጌል የገለጠው ምሥጢር አንድ ነው። እርሱም የጽድቅ ዘር የሆነው ክርስቶስ በእኛ ውስጥ መሆኑንና በሕይወት አካሄዳችንም የኑሮአችን ፍሬ ሆኖ የሚገለጠው ክርስቶስ ራሱ መሆኑን ነው። የተወደደው ሐዋርያ ይህንን የጽድቅ ዘር በወንጌሉ የዘራባቸውን ቅዱሳን “እናንተ የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ” እያለ፤ ክርስቶስ በእነሱ እስኪሳል ወይም ሕያው ሆኖ እስኪገለጥና የሕይወት አካሄዳቸው ደግሞም የኑሮቸው ፍሬ እስኪሆን ድረስ ዕለት ዕለትእንደ ትጉ ገበሬ አገልግሎቱን ይፈጽም ነበር። የተጋድሎውንም ዓላማ "በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰው ማቅረብ" ብሎታል። ይህም የመንፈሳዊው ገበሬ የድካሙ የመጨረሻ ውጤት ወይም ፍሬው ነው።

“ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ። ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል። ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። እኛም
በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው። ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ።” (ቆላ.1፡25-29)

Friday, March 8, 2013

ዓለምን የሚያሸንፈው እምነታችን ነው!!


“ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና the lust of the flesh, የዓይን አምሮት the lust of the eyes, ስለ ገንዘብም መመካት the pride of life, ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።” 1ዮሃ.2፡15-16

በደርግ ዘመን “ሦስቱ ጣምራ ጠላቶቻችን” የሚል አባባል እንደነበር አስታውሳለሁ። ደርግ የነገረን “ሦስቱ ጣምራ ጠላቶቻችን” ኢምፔሪያሊዝም፣ ፊውዳሊዝምና ቢሮክራቲክ ካፒታሊዝም ነበሩ። ነገር ግን የሰው ልጅ በእግዚአብሔር እጅ ተበጅቶ በዔደን ገነት ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የሚፈትኑትና ከእግዚአብሔር ፈቃድና ሃሳብ እንዲጎድል እየጠለፉ የሚጥሉት ሦስት ጣምራ ጠላቶች አሉት። እነርሱም ከላይ በምናነበው መልእክት ውስጥ የተገለጡት፤ የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አእምሮትና እኔነት ናቸው። “እኔነት” ወይም በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱሳችን “ስለገንዘብ መመካት” ተብሎ የተተረጎመውን ሃሳብ ስናብራራው፤ በዚህ ሕይወት ባለን ነገር  ወይም በራስ የመተማመን፣ የመኮፈስና ከፍ-ከፍ የማለት፣ ገደብ የለሽ ሃብትና ክብር፣ ከዚህ ዓለም የሆነውን ጥበብና እውቀት የማግኘትና ሁልጊዜም ለማግኘት የመጓጓት ፍላጎት እንደሆነ እንረዳለን።

“ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።” ሮሜ.8፡6  

እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ሰው በራሱ መልክና ምሳሌ ፈጥሮና አበጃጅቶ በዔደን ገነት ሲያስቀምጠው ሁለት መንገዶችን በፊቱ አኑሮ ነው። (((በምድር ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ መካከል ለይቶ ርስት የሰጣቸውን እሥራኤላውያንን ወደርስታቸው ለማስገባት በምድረ በዳ በመራቸውም ጊዜ
የእሥራኤል አምላክ እነዚህን ሁለት መንገዶች በፊታቸው አኑሮ እንደነበር በዘዳ.30፡19-20 ላይ ተጽፎ እናገኛለን))) በዔደን ገነት መካከል በነበረው የሕይወት ዛፍ ተምሳሌትነት የተገለጠውና እግዚአብሔርን የሕይወትና የህልውና ማዕከል በማድረግ፣ ለቃሉም በመኖርና በመታዘዝ፣ ወይም በመንፈስ በመመላለስ ወደሚገኘው የማይጠፋ ሕይወት የሚወስደውና፤ መልካሙንና ክፉውን በሚያስታውቀው ዛፍ ተምሳሌትነት የተገለጠውና ራስን የህልውና ማዕከል በማድረግ፣ በራስ ፈቃድና ሃሳብ ወይም እንደ ሥጋ ፈቃድና ሃሳብ እንደወደዱ በመመላለስ ከእግዚአብሔር ወደመለየትና ወደሞት የሚወስደው መንገዶች ናቸው። በሴቲቱና በእባቡ መካከል በተደረገው ‘ውይይት’ የተቀሰቀሰውና ኋላም አሸንፎ የወጣው ሁለተኛው መንገድ ነው። “ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ (የሥጋ ምኞት)፣_ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ (የዓይን አምሮት)፣ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ (እኔነት) አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።” (ዘፍ.3፡6)

የሰው ልጅ በፊተኛው ሰው ኣዳም አለመታዘዝ ወይም በእነዚህ ሦስቱ ጣምራ ጠላቶቹ አማካኝነት ከእግዚአብሔር ሕይወት ተለይቶ ወድቆበት ከነበረው የሞትና የጨለማ ጉድጓድ የወጣው፤ በኋለኛው (በመጨረሻው) ኣዳም መታዘዝ ነው። የኋለኛው አዳም መታዘዝ በይፋ መታየትና መገለጥ የጀመረው ደግሞ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው” የተባለው የቀደመው እባብ በዔደን ገነት የፊተኛውን ሰው ፈትኖ ከሕይወት መንገድ እንዳሳተው፣ ለአርባ ቀንና ሌሊት በጾምና በጸሎት በደከመበት ምድረ በዳ ኢየሱስ ክርስቶስንም ፈትኖ ለመጣል ያደረገው ሙከራ በከሸፈበት ወቅት ነው። በዚህ የምድረበዳ ፈተናም ወቅት በፈታኙ በኩል ለኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦለት የነበረው ፈተና፤ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር እጅ ተበጅቶ በዔደን ገነት ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የሚፈትኑትና ከእግዚአብሔር ፈቃድና ሃሳብ እንዲጎድል እየጠለፉ የሚጥሉት ሦስቱ ጣምራ ጠላቶቹ ማለትም የስጋ ምኞት፣ የዓይን ዓምሮትና እኔነት ነበሩ። (ማቴ.4፡1-11 ይነበብ)

“በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” (ዮሃ.16፡33)

እውነተኛው ክርስትና ሲገባን በእነዚህ ሦስቱ ጣምራ ጠላቶቻችን የሚደርስብንን ፈተና የሚያህል ሌላ ታላቅ መከራ በዚህ ዓለም ላይ እንደሌለ እንረዳለን። በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው” የተባሉት፣ ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ያነጹት ናቸው። በበጉ ደም ታጥቦ የሚነጻው ልብሳችን ደግሞ በዚህ ዓለም በሚገኝ ነውርና እድፍ፣ ማለትም በሥጋ ምኞት፣ በዓይን አምሮትና በእኔነት ያደፈው ማንነታችን ነው። በበጉ ደም ታጥቦ መንጻት ማለትም፣ በድካማችንና በኃጢአታችን ከምንወነጀልበት የዲያብሎስ ክስ ነጻ ከመውጣት ጀምሮ፣ የሥጋችንን ድካም ምክንያት አድርጎ በእኛ የሚሰራውን የኃጢአት ኃይልና ሕግ ፈጽመን ድል እስከምናደርግበትና እስከምናሸንፍበት፣ በዚህም የሥጋ ሥራ ከተባሉት የሞት አገልጋዮች አርነት ወጥተን በመንፈስ ፍሬ ወይም በክርስቶስ ሕይወት ሙላት እስከምንሞላበት የሕይወት ከፍታ የሚደርስ ነው። ዓለምን ማሸነፍና “ድል ነሺ” የመባል ትርጉሙም ይኸው ነው።

“ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።” (ገላ.6፡14)

እኛ ለዓለም - ዓለምም ለእኛ የተሰቀለበት የክርስቶስ መስቀል፣ ዓለምንና በዓለም ያሉትን ማለትም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን ዓምሮትንና እኔነትን ከእኛ ፈጽሞ ያስወገደና የሚያስወግድ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። አንድ ክርስቲያን የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ከእርሱ ሕይወት ጋር የተያያዘበትን ሙሉውን እውነት ካላየ፣ እግዚአብሔር በሕይወቱ ሊፈጽመው ያሰበውን የከበረ ዓላማ መገንዘብ ካለመቻሉም በላይ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የሰጠውን የከበረ ሕይወት በሙላት ለሊያጣጥም አይችልም። ክርስቶስ በመስቀል ላይ የከፈለው ቤዛነታችን እርሱም የበደላችን ስርየት ከእግዚአብሔር ጋር የታረቅንበት ብቸኛው መንገድ እንደመሆኑ፣ እኛም ከክርስቶስ ሞት ጋር መተባበራችን ወይም አሮጌው ሰዋችን ከክርስቶስ ጋር መሰቀሉን መረዳታችን ዓለምንና በዓለም ያለውን ሁሉ የምናሸንፍበት የድላችን ዋስትና ነው። የክርስቶስ ሕይወት ሕይወታችን የሚሆነው ሞቱም ሞታችን ከሆነ ብቻ ነው። ለዚህም ነው የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ፡- “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው” ያለው። (ገላ.2፡20)

ክርስትና የምንለው የከበረ ኑሮና ሕይወት በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምንኖረው ኑሮ ነው። ወይም በሌላ አገላለጥ ክርስትና እኛ የምንኖረው ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጅ በእኛ የሚኖረው ኑሮ ነው!! ይህም እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ሰውሮት የነበረው፣ ልጁ በሥጋ በመምጣቱ ለቅዱሳኑ ሁሉ የገለጠው የከበረ ምሥጢር ነው። ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእኛ ዘንድ (Christ IN us) መሆኑ ነው። ዓለምንም የሚያሸንፈው፤ ማለትም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና እኔነት ከተባሉት ክፉ ጠላቶቻችን አርነት የሚያወጣን በእኛ ያለው ክርስቶስ እርሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የሚመሰክረው እምነታችን ነው።   

ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?” 1ዮሃ.5፡4-5