አንዳንድ
ወገኖች፣ ክርስትና በምድራችን ላይ ከሚቆጠሩት ሐይማኖቶች አንዱ እንደሆነ ያስባሉ። ቡድሃ የሚባለው ሰው ቡዲዝም የሚባለው ሃይማኖት መሪና መስራች እንደነበረ፣ ወይም ደግሞ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የተወለደውና ወላጅ አባቱንና እናቱን ገና በልጅነቱ በሞት የተነጠቀው መሐመድ እስልምና የሚባለውን ሃይማኖት እንደመሰረተ፤ ክርስቶስም ዛሬ በክርስትና ስም ነገር ግን የየራሳቸውን ጎራ ፈጥረው ካቶሊክ፣ ኦርቶዶክስ፣ ፕሮቴስታንት፣…. እያሉ ራሳቸውን የሚጠሩትን የተለያዩ ሃይማኖቶች እንደመሰረተ አድርገው የሚያስቡ ጥቂቶች አይደሉም። አንዳንዶቹ እንደውም “የበቃችውና ትክክለኛዋ ሐይማኖት” እነርሱ የተቀበሏትና የሚከተሏት ሃይማኖት ብቻ እንደሆነች
ደፍረው ይናገራሉ። ነገር
ግን እውነቱ ከዚህ የሰዎች አስተሳሰብ በእጅጉ የራቀ ነው። ክርስትና ሃይማኖት ካለመሆኑም በላይ፤ ክርስቶስም እንዲሁ የሃይማኖት መሪና መሥራች
አይደለም።
ክርስትና ሃይማኖት ካልሆነ ታድያ ምን ሊሆን ይችላል? ክርስትና - ዓለም ሳይፈጠር በአባቱ ዘንድ በክብር የነበረው፣ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ምሕረት አካባቢ በድንግሊቱ ማርያም ማሕፀን ያለወንድ ዘር በመንፈስ ቅዱስ ተጸንሶ በሥጋ የተወለደው ክርስቶስ ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የሚመሰክር፣ እርሱ በፊተኛው አዳም አለመታዘዝ ምክንያት በሰዎች ሁሉ ላይ የሰለጠነውን የኃጢአትና የሞት ሕግ በሞቱና በትንሳዔው እንደሻረ የሚያበስርና፣ ሰዎች ሁሉ ይልቁንም እርሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምነው የሚቀበሉቱ፣ ጻድቅና ቅዱስ ከሆነው እግዚአብሔር ዳግመኛ በመወለድና የልጅነትን ጸጋ በመቀበል ፍጹም የሆነ አዲስ ሕይወት እንደሚጎናጸፉ የሚያስተምር እምነት ነው። በአጭሩ ክርስትና - በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነት የምንኖረው አዲስ ሕይወት ነው።
በዚህ እኛ ባለንበት ዘመን ወደ ሰባት ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በምድራችን ላይ እየኖሩ እንደሆነ ይገመታል። ታድያ እነዚህ ሰባት ቢሊዮን ሰዎች በተለያዩ ሃይማኖታዊ ወጎችና ሥርዓቶች የተለያዩ አማልክቶችን ወይም “አንድ ነው” - “አንድም ሶስትም ነው” …. ብለው የሚያምኑትን አምላክ የሚያመልኩ ከመሆናቸው ቀጥሎ፤ የተለያየ ቀለም ያላቸው፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ፣ የተለያየ ባህልና ልማድ ያላቸው፣ በተለያዩ አካባቢዎችና ሁኔታዎች ተፅዕኖ ሥር የሚኖሩ…. ናቸው። ነገር ግን ተፈጥሮአዊ ማንነታቸውንና ሕይወታቸውን የተመለከትን እንደሆነ በምድር ላይ የሚኖሩት ወደ ሰባት ቢሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ ዐይነት ሰዎች ሳይሆኑ፣ ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው። የመጀመሪያው ሰው አዳምና ሁለተኛው ሰው ክርስቶስ፤ አሮጌውና አዲሱ ሰው፤ ፍጥረታዊውና መንፈሳዊው ሰው፣ መሬታዊውና ሰማያዊው….
የመጀመሪያው ሰው አዳም በኃጢአት፣ በሞትና በጨለማ ውስጥ የሚኖረው ወገን የተፈጥሮአዊ ማንነቱ ምንጭ እና የሕይወቱም ራስ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ይገኙ ለነበሩ ክርሰቲያኖች በጻፈው መልዕክቱ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር፡- “ስለዚህም ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” (ሮሜ.5፡12) ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ከሥጋና ከደም እየተወለዱ በዚህ መሬት በተባለው ፕላኔት ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በመጀመሪያው ሰው ምክንያት ወደ ዓለም ከገባው የኃጢአትና የሞት ሕግ በታች ናቸው። ስለዚህም እግዚአብሔርን ባለማወቅ ልቡናቸው ጨልሞ አንዱ ከአንዱ ሳይበላለጥ ወይም ሳያንስ በኃጢአት ይኖራሉ። “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” የሚለውና በወንድማችን ጳወሎስ በኩል የእግዚአብሔር መንፈስ የተናገረው ቃል እውነት ነው። ነገሥታት ቢሆኑ ወይም ‘ተራ’ ሰዎች፣ የሃይማኖት መሪና መሥራችም ሆኑ ሃይማኖት የለሽ ‘አረመኔዎች’…. ያው በአዳም ምክንያት ወደዚህ ዓለም የገባው የኃጢአትና የሞት ሕግ ሰለባዎች ናቸው።
ምንም እንኳን አምላካቸው “የሕያዋን አምላክ” ተብሎ ተጠርቶ በዘመናቸው የእግዚአብሔርን ሃሳብ እያገለገሉ ቢያልፉም፤ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ፣ ሙሴም ሆነ ንጉሱ ዳዊት፣ እንዲሁም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የቀደመው ዘመን ነቢያትና የእምነት ሰዎች፤ ከሰማይ የሆነውና “ሁለተኛው ሰው” የተባለው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ ወደ ሕይወት የሚወስደውን በር እስኪከፍት ድረስ፣ “የዘላለም ሕይወት” የተባለውን ሰማያዊ ተስፋቸውን አላገኙም ነበር። ከእግዚአብሔር መላኩንና የእግዚአብሔር ልጅነቱን ይቃወሙ ለነበሩት አይሁድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር እንዲህ አለ፡- “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሃሴት አደረገ፣ አየም ደስም አለው።” (ዮሃ.8፡56) የዕብራውያን መልዕክት ጸሐፊም ስለቀደሙት የእምነት ሰዎች እንዲህ ጽፎ ነበር፡- “እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፣ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና….” (ዕብ.11፡13)
በመጀመሪያው አዳም መተላለፍ ምክንያት እግዚአብሔር ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ በኪሩቤልና በምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍ ጠብቆት ወይም ዘግቶት ነበር። በብሉይ ኪዳን የነበሩ መስዋዕቶች ሁሉ ይናገሩ የነበረውም ይህ የተዘጋ የሕይወት መንገድ ሊከፈት የሚችለው በመስዋዕት ብቻ እንደሆነ ነበር። “ኋለኛው አዳም” እና “ሁለተኛው ሰው” የተባለው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለኃጢአት ሥርየት የሚሆን ቅዱስና ሕያው መሥዋዕት አድርጎ በመስቀል ላይ ያቀረበውም ይህንን የሕይወት መንገድ ለመክፈት ነበር ። እጅግ በጣም የሚገርመው እውነት ደግሞ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን የሕይወት መንገድ በሞቱ መክፈቱ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ሕይወት የሚወስደው መንገድም ሆነ እየቆረስን የምንበላው ሕይወት ራሱ መሆኑ ነው። “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ…” ማለቱም ለዚህ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሲሞት በኢየሩሳሌም የነበረው የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከታች ለሁለት መቀደዱ፣ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ የመፍረሱ ምልክት ከመሆኑም በላይ፣ ወደ ሕይወት የሚወስደው መንገድ መከፈቱን የሚያመለክት ነው። ለዚህም ነው የዕብራውያን ጸሐፊ፣ ክርስቶስ በደሙ መርቆ በከፈተልን “በአዲስና በሕያው መንገድ” እግዚአብሔር ወዳለበት፣ ዕረፍትና ዘላለማዊ ሕይወት ወደምናገኝበት መንፈሳዊ ሥፍራ ለመግባት ድፍረት እንደሆነልን የጻፈው። (ዕብ.19-22)
እንግዲህ ክርስትና ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደው የዚህ አዲስና ሕያው መንገድ መገለጫ ነው። ጅማሬውም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምኖ የሞቱንና የትንሣዔውን ፋይዳ በመገንዘብ፤ ማለትም በሞቱ የኃጢአት ሥርየትና ይቅርታ፣ በትንሣዔው ደግሞ ፍጹም የሆነ አዲስ ሕይወት እንደሚገኝ በማመንና ይህንንም በውኃ ጥምቀት መስክሮ ከእግዚአብሔር ዳግመኛ በመወለድ ነው። በዚህም ሂደት ውስጥ ያለፈ አንድ ሰው በአዳም ከሆነው ኃጢአት፣ ሞትና ጨለማ፤ በክርስቶስ ወደሆነው ጽድቅ የተትረፈረፈበት ሕይወትና ወደሚደነቅ ብርሃን ይሻገራል። በኃጢአትና ባለመታዘዝ የወደቀውን ሰው በባርነት ጠፍንጎ ከያዘው የሰይጣን ሥልጣንና አገዛዝ ተላቆ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ወደሚገዛበትና፤ ፍቅርና ሰላም፣ መንፈሳዊ ደስታና ሰማያዊ ዕረፍት ወደሞላበት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መፍለስ ይሆንለታል። “የሞት መውጊያ” ከተባለው ኃጢአትና ከሥጋ ሥራ ነጻ እየወጣ፣ ወደ እግዚአብሔር መንግስት በሙላት ለመግባት የሚያስችለውን የመንፈስ ፍሬ በሕይወቱ ማፍራት ይጀምራል። በኃጢአት የተበላሸው ሕይወቱ ከላዩ እየተገፈፈ፣ ፍጹምና አዲስ የሆነ ሰማያዊ ሕይወት መልበሰ ይጀምራል። ወንድማችን ጳወሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ሁለተኛ መልዕክቱም የገለጠልን ይህንን እውነት ነው። “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፣ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።” (2ቆሮ.5፡17)
የወንጌልን እውነት እየተቀበሉና በክርስቶስ ባለ እምነት ከእግዚአብሔር በመወለድ አዲስ ፍጥረት የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች የሚጋጠሙትና የሚጨመሩት ደግሞ በተለያዩ ሰዋዊ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ሊከፋፈል ወደማይችል ወደ አንድ መንፈሳዊ አካል ነው። ይህም መንፈሳዊ አካል “የሐዋርያትና የነቢያት መሠረት” በተባለው አንድ ጠንካራ መሠረት - በክርስቶስ ላይ የቆመ፤ መሠረቱ፣ ግድግዳውና ማገሩ፣ ድምድማቱም ጭምር ክርስቶስ የሆነለት አንድ አዲስ ሰው ነው።
“አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤” 1ቆሮ.12፡12
ጥሩ ብለሃል ወንድሜ፡፡ ክርስቶስ በመስቀሉ ፍቅርን፣ ፍጹም የሆነ አንድነትን በእርሱ አምኖ ለተጠመቀ ሁሉ ሰጥቶአል፡፡ ጥምቀትም ቅዱስ ጳውሎስ አንዲት እንደሆነች ጽፎልናል፡፡ በእርሱ አንድ አካል ሆነን የምንጠቀልበት ጌታ አንድ እንደሆነ ገልጾ ጽፎልናል፡፡ በእርሱ ስንታይ ብዙ ብንባልም አንድ የእርሱ ቤተመቅደስ ሆነናል፡፡ በሰውነታችን ቤተመቅደስም የሚያድረው ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ቃሉን ፈጽመን የተገኘን እንደሆነ እርሱና አብ በእኛ ይገለጣሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም እናንተ የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ናችሁ ብሎ አስፍሮልናል፡፡ ስለዚህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በሰውነታችን ቤተመቅደስ ውስጥ ያድራሉ፡፡ ይህ በእርሱ አምነው ለተጠመቁና በጥምቀት ክርስቶስን ለለበሱት የሚፈጸምና በእርሱ አንድ አካል ሆነው ስለመጠቅለላቸው ምስክር ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለያየትና አንዱ ለአንዱ ጠላት ሆኖ መንቀሳቀስንአላስተማረንም፡፡ የሚታየው ገሃድ የሆነ እውነታ ግን መለያየትን በመምረጥ ብዙዎች የክርስቶስ ጠላቶች ሆነው መንቀሳቀሳቸውን ነው፡፡ ይህ የሚመነጨው ከፍቅር መጥፋት ነው፡፡ በአሁኑም ጊዜ ለገዛ ዝናቸውና ጥቅማቸው ሲሉ ብዙዎች እጅግ ብዙዎች ልዩነትን በመስበክ የክርስቶስን አካል ለመለያየት ለመበታተን ይደክማሉ፡፡ አምላክ እርሱ ማስተዋሉን ይስጣቸው ነው የኔ መልእክቴ፡፡
ReplyDeleteአንድ ነገር ደግሞ አንተ ባልከው የማልስማማው ነገር አለን፡፡ ተመልከት ወንድሜ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሠ”(ሮሜ.5፡14)ይላል እንግዲህ ሞት እንጂ ኃጢአት ከሰው ባሕርይ ጋር አልተዋሐደም፡፡ ወገኔ ሆይ ይህ ስለፍቅር እላለሁ፡ ተመልከት ወንድሜ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ የተባለው ሄኖክ ስለመበደሉ ተጽፎልናልን? ካህኑና ነቢዩ ሳሙኤልስ ስለመበደሉ ተጽፎልናልን? ስለዘካርያስና ስለኤልሳቤጥስ መበደል ተነግሮናልን ዘካርያስ ባለማመኑ በድሎ ይሆናል ነበር ግን ኤልሳቤጥ በድላለችን? በቤተመቅደስ እግዚአብሔርን ስታገለግለው የነበረችው ሃናስ ኃጢአትን ስለመፈጸሟ ተጽፎልን እናገኛለንን? ሌላውን ልተወው ወንድሜ፡፡ ስለዚህም ኃጢአትን ያልፈጸሙ ነበሩ ነገር ግን ከሞት ፍርድ አላመለጡም፡፡ “አዳም አፈር ነህና ወደ አፈርነትህ ትመለሳለህ” ከሚለው ፍርድ የሰው ልጅ ሁሉ አላመለጡም ነገር ግን በዚህ ምድር ሲኖሩ ኃጢአትን ደምን እስከማፍሰስ ደርሰው የተመላለሱ ጻድቃንም አሉ፡፡ ኃጢአት ከሰው ልጆች ጋር እየተቆራኘ ተወልዶአል የምንል ከሆነ አንድም ሰው ጽድቅን መፈጸም ባለተቻለው ነበር፡፡ ኃጢአት ሰው ሲወለድ ተቆራኝቶት ተወልዶአል የሚለውን ትምህርት አልቀበለውም ምክንያቴንም ከላይ ለማስቀመጥ ሞክሪያለሁ፡፡ ቢሆንም አሁን በክርስቶስ ሁሉ ተሟልቶአል፡፡ በአሁን ጊዜ ከሞት ፍርድ በዳግማዊው አዳም ክርስቶስ መዳንን አግኝተናል፡፡ ነገር ግን ከድኅነቱ ተሳታፊ ለመሆን የግድ ልንጠመቅና የልጅነት ሥልጣንን ልንቀበል እንዲሁም ክርስቶስን መስለን በቅድስና ልንመላለስ ይገባናል፡፡ ውድ ወንድሜ እኔ ክርስቶስን ተመልክቼ እንዲህ ብዬ አምናለሁ፡፡ ክርስቶስ ወደሚፈልገው ፍጹም ወደ ሆነ አንድነት እንድንመጣ እፈልጋለሁ፡፡ አንድነታችንን ማምጣት የምንችለው በእኛ መስማማት ሳይሆን የክርስቶስ የአካሉ ሕዋሳት በመሆን ነው፡፡ የክርስቶስ የአካሉ ሕዋሳት ስንሆን ፍጹም የሆነ አንድነት ይኖረናል ፡፡ የእግዚአብሔር አብም ዓላማ ሰውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለለን ነው፡፡ ወንድሜ ሆይ ስለዚህ ነገር እንድትተጋ መለያየትንና መነቋቆርን ከሚያመጡ ነገሮች በመራቅ ክርስቶስን ለማወቅና ሰው ሁሉ በክርስቶስ አንድ አዳም እንዲሆን ልንደክም ይገባናል እላለሁ፡፡ መልካም ዘመን ይሁንልህ!!
ወንድም ሽመልስ መርጊያ፣ ስለ ሰጠኸው ቀናና የበሰለ አስተያየት እግዚአብሔር ይባርክህ! አንተም እውነት ብለሃል። ክርስቶስ ወደሚፈልገው ፍጹምና እውነተኛ አንድነት የምንመጣው በእኛ መስማማት ሳይሆን የአካሉ ሕዋሳት ወይም ብልቶች ስንሆን ወይም መሆናችንን ስንረዳ ብቻ ነው። የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች የምንሆነው ደግሞ አስቀድመን በክርስቶሰ ባለ እምነት ከእግዚአብሔር ወይም ከማይጠፋው ዘር ዳግመኛ ስንወለድ ብቻ ነው። ከዚሁ ጋር አያይዤ የተቃወምከውን ሃሳብ ላንሳ። ኃጢአት እኮ ምንጩ የእባቡ ዘር ነው። አዳም በሔዋን መታለል ባለመታዘዝ ሲገኝ የተባበረው ወይም ከማንነቱ ጋር የተጋባው የእባቡን ዘር ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኃጢአት የኃጢአት ደመዎዝ የተባለውም ሞት የሰው ልጆች የሚወለዱበት ሕግ ሆነ። ለዚህም እኮ ነው ንጉሡ ዳዊት "እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ" ያለው። (መዝ.51፡5) መቼስ ንጉሱ ዳዊት እግዚአብሔር "እንደ ልቤ" ያለውና በዘመኑም የአምላኩን ሃሳብ አገልግሎ ያለፈ የተቀባ ንጉስ እንደነበረ የታወቀ ነው። ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምክንያት ከሰው ዘር ጋር የተጋባው የእባቡ ዘር እርሱንም አልዘለለውም ነበር።
Delete"ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደሰቀለ እንዲሁ የሰው ልጅ ሊሰቀል ይገባዋል።" በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ተጣብቆ የነበረው ክፉ ዘር ከመንገድ የተወገደው በክርስቶሰ ሞት ብቻ ነው። ሔኖክም ይሁን አብርሐም፣ ሙሴም ይሁን ዳዊት... ከዚህ የእባቡ ዘር ነጻ አልነበሩም። ሔኖክም ይሁን ኤልያስ የሥጋን ሞት ሳያዩ ወደሰማይ ቢነጠቁ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደው መንገድ ለእነርሱ ክፍት ነበር፣ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የዘላለምን ሕይወት ተስፋ አግኝተው ነበር ማለት አይደለም። ወደዚህ የማይጠፋ ሕይወት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ቀድሞ የገባ ማንም አልነበረም። ስለዚህ ኃጢአት ምንጩ የእባቡ ዘር ነበርና "ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም" ተባለ። ልብ በል! ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ቃል የተናገረው ሕጉን ጠንቅቆ ለሚያውቀው የአይሁድ መምሕር ነበር። ታድያ ሰው በአዳም በኩል የተወለደው ከሚጠፋው ዘር ነው። ከዚህ ዘር ኃጢአትና የሥጋ ሥራ የተባለው ፍሬ ሁሉ ይታጨዳል። ከማይጠፋው ዘር የምንወለደው ደግሞ በክርስቶስ እምነት ነው። ከዚህም ዘር ጽድቅና ሰላም፣ ቅድስናና የዘላለም ሕይወት ይታጨዳል። ይህ "የማይጠፋው" የተባለውን ዘር ሔኖክም ሆነ አብርሐም አልተካፈሉትም ነበር። ምክንያቱም ገና አልተገለጠም ነበርና።
ወንድሜ ሔኖክ፣ እንግዲህ ከላይ በጥቂቱ ለማለት በፈለግሁት ሃሳብ ላይ የተለየ ሃሳብ ካለህ ልሰማህ ዝግጁ ነኝ። የአንተም ዘመን እንዲሁ የተባረከ ይሁንልህ!!
ውድ ወንድሜ ስለዳግም ልደት የተናገረከው ትክክል ነው፡፡ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ከማይጠፋ ዘር ከእግዚአብሔር ተወልዶ የእግዚአብሔር ልጅ ሊባል ይገባዋል፡፡ ያም ማለት ለመዳን ሊጠመቅ ይገባዋል ማለት ነው፡፡ በዚህ እስማማለሁ፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ልጆች ተሰኝተናል፡፡ የክርስቶስ የአካል ብልቶች የምንሆነው በጥምቀት ነው፡፡ ወንድሜ የእባብ ዘር ያልከው ሰይጣን በእባብ ሰውነት ውስጥ በማደር ለሔዋን እናታችን የተናገረውን የስህተት ቃልን ነውን? ወይስ ጌታችን ፈሪሳዊያንን “…ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድን ነው ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው፡፡ እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ፡፡” እንዳለው በምግባር ዲያብሎስን መምሰልን ነው? ወይስ በምግባሩ የዲያብሎስ ልጅ እንደሆነውና ዲያብሎስ እንደተባለው ይሁዳ የሰው ዘር ሁሉ ዲያብሎስ እንዲሆን ሆኖአል ማለትህ ነው? ወይስ ጌታችን ጸሐፍት ፈሪሳዊያንን የእፉኝት ልጆች እንዳላቸው የሰው ዘር ሁሉ እነርሱን መስሎ ነበር እያልከኝ ነው? የእባብ ዘር ስትል መቼም ወንድሜ ሆይ የሰይጣን ዘር ማለትህ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ካልሆነ አስተካክለኝ፡፡ እንዲያ ከሆነ ሰይጣን በእውን ዘር አለውን? በእርግጥ በክፋት እርሱን ከመሰልን የእርሱ እጣ ፈንታ በእኛ ላይም ይደርሳል፡፡ በክፋት ካልተባበርነው ግን እርሱን አንመስልም፡፡ ተመልከት ወንድሜ ቃሉን የሚቀበሉና ቃሉን ያለተቀበሉ በክርስቶስም ዘመን ነበሩ፡፡ ጌታችን ስለራሱ መልካም እረኝነት ከገለጠልን በኋላ “በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል ከሌለው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም የሌሎችን ድምፅ አያቁምና፡፡”(ዮሐ.10፡4-6)ብሎ ዲያብሎስን ያልሰሙ እንደፈቃዱም ያልተመላለሱ የማይመላለሱ በዘመኑም እንደነበሩ ገልጦልናል፡፡ ወንድሜ ሆይ ይቅርታ ትንሽ እንግዳ የሆነ ቃልን በመጠቀመህ ነው እንዲህ ማለቴ፡፡ ከዘፍጥረት እስከራእይ አንብቤአለሁ አንተ እንዳስቀመጥከው የእባብ ዘር ከሰው ሰብእና ጋር ተዋሐደ አደረ የሚል ሰፍሮ አላየሁም ካለ ጻፍልኝ ወንድሜ፡፡
Deleteስለዳዊት ባነሣህልኝ ኃይለቃል ላይ አንድ አንተም እኔ የምናስተውለው ነገር አለ፡፡ ቅዱስ ዳዊት “እናቴ በኃጢአት ወለደችኝ” አለ እንጂ እናቴ ኃጢአተኛ አድርጋ ወለደችኝ አላለም፡፡ ኃጢአቱ የእናትየው እንጂ የእርሱ አይደለም፡፡ እርሱ ከኃጢአት ጋር ተቆራኝቶ የተወለደ ቢሆን ኖሮ ተፈጥሮው ሆኖአልና እንዴት ጽድቅን መፈጸም ይቻለው ነበር? ግን ዳዊት በሕይወቱ ዘመን ጽድቅን ያልፈጸመበት ስቶም ከሆነ ንስሐ ያለገባበትና ከእግዚአብሔር አምላኩ ጋር ያልታረቀበት ዘመን የለም፡፡
አንድን ሰው ኃጢአተኛ ነው ልንለው የምንችለው ሕግ ተሰጥቶት ሕጉን ጥሶ የተገኘ እንደሆነ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ አንድ ሕጻንን ሕግን ሳያውቅና ሳይለይ ሕግ ሳይሠራለት እንዴት ኃጢአተኛ ሊባል ይችላል? ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገረም “እኔ ድሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ”(ሮሜ.7፡9)ይለናል፡፡ ስለዚህ ሕግ ያልተሠራላቸው ሕጻናት እንዴት ሕጉን ሳያቁ ኃጢአተኞች ሊባሉ ይችላሉ? ከኃጢአት ጋር ተቆራኝተን የተወለድን ቢሆን ኖሮ አንድም ጽድቅን የመፈጸም ፈቃዱ ባልኖረን ነበር እላለሁ ወንድሜ፡፡
ነገር ግን ሁላችንንም የሚያግባባን ነገር ቢኖር የአዳምና የሔዋን የመተላለፍ ውጤቱ በሰው ሁሉ ላይ ደርሱዋል የሚለው ነው፡፡ ያም ማለት ሟች የሆነን ተፈጥሮ ገንዘባችን አድርገናል፡፡ ጌታችንም ይህንን ሰውነት ከቅድስት ድንግል ማርያም በመንሳት ሰው ሆኖ ተገለጦ ስለእኛ በመስቀል ላይ በመሰቀል በሞቱ ሞታችንን አጥፍቶልናል፡፡ የኃጢአት ፈቃድን ድል እንነሳበት ዘንድ በጥምቀት በውስጣችን መንፈስ ቅዱስን አሳድሮልናል፡፡ አሁን የክርስቶስ ልብ የተባለው መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን ማስተዋል የተሰወረውን የሰይጣንን ተንኮልና ሽንገላ መለየትና ድል መንሳት እንችላለን፡፡
ወንድሜ እኔ የምረዳው እንዲህ ነው፡፡ በአዳምና በሔዋን መተላለፍ የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ተለየን የእግዚአብሔር ልጅነታችንን አጣን፡፡ ስለዚህ ሰይጣን ፈቃዱን እንፈጽምለት ዘንድ ክፍተት አገኘ እንዲያም ሆኖ ግን ፈቃዱን ያልተቀበሉ ቅዱሳን ብዙዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን በአዳም ላይ ከተላለፈው ፍርድ በታች ነበሩ፡፡ ስለዚህም ጌታችን በሰው ላይ የተፈረደውን ፍርድ በመቀበል ፍርዱን ከሰው ልጆች ላይ አስወገደ፡፡ ወደ እኛ የተላለፈው የአዳም ኃጢአት ሳይሆን ወይም ምናልባት አንተ እንደምትለው (ትክክል ከሆንኩበኝ) የእባብ ዘር ሳይሆን በእርሱና በሔዋን ላይ የተላለፈው ፍርድ ነው የተላለፈው፡፡ ፍርድ አንድን ሰው ከጥፋቱ ለማረም የሚወድ እንጂ ይበልጥ በእርሱ ውስጥ ኃጢአትን የሚዘራ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሰው በእስር ቤትም ሆኖ ሊበድል ይችላል፡፡ ከክርስቶስ በፊት የነበረው የሰው ልጆች ሕይወት ይህን ይመስል ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ይህ ጉዳይ ብዙ የሚያነጋግረን ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በክርስቶስ አብቅቶአልና፡፡ አሁን ቅዱስ ጳውሎስ “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችሁታልና፡፡” እንዲል አሮጌው ማንነታችን በጥምቀት ተቀብሮ በአዲሱ ማንነታችን ውስጥ እንገኛለን፡፡ እግዚአብሔር ይህን ልዩ የሆነ ማንነታችንን ጠብቀን በመገኘት ከቅዱሳን ጉባኤ እንድንገኝ ፈቃዱ ይሁን አሜን፡፡ ሰውን ሁሉ የሚያፈቅር አምላክ ለሁላችን ፍቅርን አንድነትን ሰላምን ያድለን፡፡