Thursday, July 11, 2013

መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ!!


“እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና። በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ” ኢሳ.56፡4

የአዲስ ኪዳኑ የእግዚአብሔር ቤትና መቅደስ፤ ወይም የእግዚአብሔር ከተማና ቅጥር እንደቀደመው ኪዳን በሰው እጅ የተሰሩ ወይም የታነጹና የተገነቡ የሰው እጅ ሥራዎች አይደሉም። ዛሬ እግዚአብሔር ያለው መቅደስ ወይም ቤት ወይም ከተማና ቅጥር አንድ ነው። እርሱም በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተቀደሰው፣ በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ማለትም፤ "አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ" በሚለው አንድ እምነት ላይ የቆመውና፣ በክርስቶስ ባለው ሕይወት እግዚአብሔርን ለመምሰል በቅዱስ ቃሉና በቅዱስ መንፈሱ እየታነጸና እየተሰራ ያለው የእግዚአብሔር ሕዝብ ነው። ይህም በሐዋርያቱ ትምሕርት ላይ በግልጽ ተጽፎ ይገኛል።

"በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ" ኤፌ.2፡20-22

"በሰውም ወደ ተጣለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደ ሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ፥እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ" 1ጴጥ.2፡4-5

የዚሁ የእግዚአብሔር ቤት፣ መቅደስ፣ ከተማና ቅጥር ማንነት በተለይ በራዕይ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፎች ላይ እጅግ ጥልቅና ድንቅ በሆነ መንገድ ተገልጧል። በቀደመው ኪዳን በነበረችው የኢየሩሳሌም ከተማና ቅጥርዋ ምሳሌነትና አስረጂነት ለዮሃንስ በተገለጠለት በዚህ ድንቅ ራዕይ፤ ሰማያዊቱ፣ አዲሲቱና ቅደስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌምና ቅጥርዋ በተለያዩ የከበሩ ድንጋዮች ታንጸውና ተገንብተው ይታያሉ። የዚችን ሰማያዊ ከተማ ማንነት ለዮሃንስ ይገልጥለት ዘንድ የተላከው መልአክ የተናገረው ቃል፤ ዛሬ በአብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች አእምሮ ውስጥ ያለውን አስተሳሰብና እውቀት ፈጽሞ ከሥሩ የሚንድ ነው። ለብዙዎች አዲሲቱና ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም በአንድ ባልታወቀ ሩቅ ሰማይ ላይ እግዚአብሔር ለእነርሱ እየሰራት ያለችና፣ ከሞቱ ወይም “ከተነጠቁ” በኋላ ዘላለማዊ ኑሮቸውን የሚጀምሩባት ከተማ ናት። በመልአኩ የተገለጠው ቃል ግን "ከተማይቱ እናንተ ናችሁ" ይላቸዋል።

"ሰባቱም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ። ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤ ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፥ አሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ፥ የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር። በምሥራቅ ሦስት ደጆች፥ በሰሜንም ሦስት ደጆች፥ በደቡብም ሦስት ደጆች፥ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ። ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር" ራዕ.21፡9-14

የበጉ ሚስትና ሙሽራይቱ የተባለችው፤ ቤተክርስቲያን እንደሆነችና የክርሰቶስ ቤተክርስቲያንም በሰው እጅ የተሰሩ ሕንጻዎች ሳይሆኑ ራሳቸው መሆናቸውን ብዙዎች ይረዳሉ። ይቺ የበጉ ሚስትና ሙሽራይቱ የተባለችው ቤተክርስቲያን አዲሲቱ ኢየሩሳሌምና ቅደስቲቱ ከተማ እንደሆነች የሚያስተውሉት ግን ጥቂቶች ናቸው። ዛሬ የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች እነርሱ እንደሆኑ፣ የእግዚአብሔር ቤት ለመሆን እየታነጹ ያሉትም ሕያዋን ድንጋዮች ራሳቸው እንደሆኑ የሚረዱት ክርስቲያኖች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፤ ነገር ግን አዲሲቱ ኢየሩሳሌም - ቅደስቲቱ ከተማ የታነጸችባቸው የከበሩ ድንጋዮች እነርሱ ራሳቸው መሆናቸውን የሚረዱ በጣም ጥቂቶች ናቸው። (ከተማይቱና ቅጥሯ የታነጹባቸው ልዩ ልዩ የከበሩ ድንጋዮች፣ በቅዱሳኑ የእግዚአብሔር ልጆች የሚገለጠው የመለኮት ባህሪይ ምሳሌዎች ናቸው)

***ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ

***የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ

ነገር ግን እጅግ ልንረዳው የሚያስፈልገን አንድ ዋና ነጥብ አለ፤ ይኸውም በዚሁ የራዕይ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጠው ርኩሰትና ውሸት የሚያደርግ ሁሉ ወደዚች ከተማ አይገባም፣ ወይም የዚች ከተማ ክፍል ሊሆን አይችልም። የዛሬ መዘጋጀታችንና በክርስቶስ ባለ ሕይወት ፍጹማን ለመሆን መሰራታችንም ጥቅሙ እዚህ ላይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስያስ ወንድሞቹ እንደጻፈው፣ በማስተማር፣ በመገሰጽ፣ በመምክር ይተጋና ይጋደል የነበረው በክርስቶስ ፍጹም የሚሆንን ሰው ለማቅረብ ነበር። "ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው፣ በደጆችዋም ወደከተማይቱ ለመግባት ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁአን ናቸው" ተብሎ እንደተጻፈውም፤ ዓለምንና በዓለም የሚገኘውን ትርፍ ሁሉ እየተውን፣ በኑሮአችንና በአካሄዳችን ከሚገለጥ የዚህ ዓለም ዕድፍና ርኩሰት ራሳችንን እያነጻንና፣ ጌታችንና አምላካችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በእምነትና በመታዘዝ እስከፍጻሜው ድረስ የመከተላችን ውጤት ነው በእርግጥ የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች፣ ሕያዋንና የከበሩ ድንጋዮች፣ የቅድስቲቱም ከተማ አባላት ወይም ክፍሎች የሚያደርገን። "ድል መንሳት" የሚባለውም ይኸው ነው። በራዕይ መጽሐፍ ሁለተኛውና ሦስተኛው ምዕራፎችም ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት በላካቸው መልእክቶች መጨረሻ ላይ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ወይም ከቤተክርስቲያን መካከል የእምነት ሩጫቸውንና ተጋድሎአቸውን ድል በመንሳት ለሚፈጽሙ የእግዚአብሔር ልጆች የተሰጠው ተስፋ ተጽፎ እናገኛለን። የዚህ መልእክት ዋና ዓላማም ዛሬ ይህንን መልእክት የሚያነቡ ቅዱሳን ሁሉ መንፈስ ለእነርሱ የሚለውን ለመስማት ጆሮአቸውን እንዲሰጡ ለማበረታት ነው።

=> መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ።

=> እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጐዳም።

=> መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፥ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፥ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎአል።

=> ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፥ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፥ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፤ የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

=> ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

=> ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፥ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

=> እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

***እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና። በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ***

እግዚአብሔር አምላኬና አባቴ ሆይ!! በከበረውና አንድያ በሆነው ልጅህ በክርስቶስ ኢየሱስ እኛን የፈጠርክበት፣ ከወደቅንበት ያነሳህበት፣ ከዚህ በርኩሰትና በጥፋት ከተሞላ ዓለም መካከል እኛን ለይተህ የጠራህበትና የዋጀህበት፣ ያነጻህበትና የቀደስክበት ዓላማህ እንዴት ግሩም ነው። እባክህን!! በዚህ ክፋትና ርኩሰት በሞላበት ዓለምና በተለይም በዚህ አስጨናቂ ዘመን ውስጥ የምንኖረውን እኛን ልጆችህን አስበን!! በክርስቶስ ኢየሱስ አንተን እየመሰልን የምንኖርበትንም ጸጋ ጨምርልን!! እንደተሰጠንም ተስፋ ድል ነስተን የመንግሥትህ ወራሾች፣ የቅድሰቲቱ ከተማ ክፍሎች፣ የመለኮታዊ ባህሪህም ተካፋዮች እንድንሆን እርዳን!! በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን!!!!