Thursday, September 13, 2012

የክርስቲያኖች ሕብረትና አንድነት! (ክርስትና - ሕይወት ወይስ ሐይማኖት) ክፍል 1


አንዳንድ ወገኖች፣ ክርስትና በምድራችን ላይ ከሚቆጠሩት ሐይማኖቶች አንዱ እንደሆነ ያስባሉ። ቡድሃ የሚባለው ሰው ቡዲዝም የሚባለው ሃይማኖት መሪና መስራች እንደነበረ፣ ወይም ደግሞ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የተወለደውና ወላጅ አባቱንና እናቱን ገና በልጅነቱ በሞት የተነጠቀው መሐመድ እስልምና የሚባለውን ሃይማኖት እንደመሰረተ፤ ክርስቶስም ዛሬ በክርስትና ስም ነገር ግን  የየራሳቸውን ጎራ ፈጥረው ካቶሊክ፣ ኦርቶዶክስ፣ ፕሮቴስታንት፣…. እያሉ ራሳቸውን የሚጠሩትን የተለያዩ ሃይማኖቶች እንደመሰረተ አድርገው የሚያስቡ ጥቂቶች አይደሉም። አንዳንዶቹ እንደውም “የበቃችውና ትክክለኛዋ ሐይማኖት” እነርሱ የተቀበሏትና የሚከተሏት ሃይማኖት ብቻ እንደሆነች ደፍረው ይናገራሉ። ነገር ግን እውነቱ ከዚህ የሰዎች አስተሳሰብ በእጅጉ የራቀ ነው። ክርስትና ሃይማኖት ካለመሆኑም በላይ ክርስቶስም እንዲሁ የሃይማኖት መሪና መሥራች አይደለም።

ክርስትና ሃይማኖት ካልሆነ ታድያ ምን ሊሆን ይችላል? ክርስትና - ዓለም ሳይፈጠር በአባቱ ዘንድ በክብር የነበረው፣ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ምሕረት አካባቢ በድንግሊቱ ማርያም ማሕፀን ያለወንድ ዘር በመንፈስ ቅዱስ ተጸንሶ በሥጋ የተወለደው ክርስቶስ ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የሚመሰክር፣ እርሱ በፊተኛው አዳም አለመታዘዝ ምክንያት በሰዎች ሁሉ ላይ የሰለጠነውን የኃጢአትና የሞት ሕግ በሞቱና በትንሳዔው እንደሻረ የሚያበስርና፣ ሰዎች ሁሉ ይልቁንም እርሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምነው የሚቀበሉቱጻድቅና ቅዱስ ከሆነው እግዚአብሔር ዳግመኛ በመወለድና የልጅነትን ጸጋ በመቀበል ፍጹም የሆነ አዲስ ሕይወት እንደሚጎናጸፉ የሚያስተምር እምነት ነው። በአጭሩ ክርስትና - በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነት የምንኖረው አዲስ ሕይወት ነው።

በዚህ እኛ ባለንበት ዘመን ወደ ሰባት ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በምድራችን ላይ እየኖሩ እንደሆነ ይገመታል። ታድያ እነዚህ ሰባት ቢሊዮን ሰዎች በተለያዩ ሃይማኖታዊ ወጎችና ሥርዓቶች የተለያዩ አማልክቶችን ወይም “አንድ ነው” - “አንድም ሶስትም ነው” …. ብለው የሚያምኑትን አምላክ የሚያመልኩ ከመሆናቸው ቀጥሎ፤ የተለያየ ቀለም ያላቸው፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ፣ የተለያየ ባህልና ልማድ ያላቸው፣ በተለያዩ አካባቢዎችና ሁኔታዎች ተፅዕኖ ሥር የሚኖሩ…. ናቸው። ነገር ግን ተፈጥሮአዊ ማንነታቸውንና ሕይወታቸውን የተመለከትን እንደሆነ በምድር ላይ የሚኖሩት ወደ ሰባት ቢሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ ዐይነት ሰዎች ሳይሆኑ፣ ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው። የመጀመሪያው ሰው አዳምና ሁለተኛው ሰው ክርስቶስ፤ አሮጌውና አዲሱ ሰው፤ ፍጥረታዊውና መንፈሳዊው ሰው፣ መሬታዊውና ሰማያዊው….     

የመጀመሪያው ሰው አዳም በኃጢአት፣ በሞትና በጨለማ ውስጥ የሚኖረው ወገን የተፈጥሮአዊ ማንነቱ ምንጭ እና የሕይወቱም ራስ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ይገኙ ለነበሩ ክርሰቲያኖች በጻፈው መልዕክቱ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር፡- “ስለዚህም ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” (ሮሜ.5፡12) ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ከሥጋና ከደም እየተወለዱ በዚህ መሬት በተባለው ፕላኔት ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በመጀመሪያው ሰው ምክንያት ወደ ዓለም ከገባው የኃጢአትና የሞት ሕግ በታች ናቸው። ስለዚህም እግዚአብሔርን ባለማወቅ ልቡናቸው ጨልሞ አንዱ ከአንዱ ሳይበላለጥ ወይም ሳያንስ በኃጢአት ይኖራሉ። “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” የሚለውና በወንድማችን ጳወሎስ በኩል የእግዚአብሔር መንፈስ የተናገረው ቃል እውነት ነው። ነገሥታት ቢሆኑ ወይም ‘ተራ’ ሰዎች፣ የሃይማኖት መሪና መሥራችም ሆኑ ሃይማኖት የለሽ ‘አረመኔዎች’…. ያው በአዳም ምክንያት ወደዚህ ዓለም የገባው የኃጢአትና የሞት ሕግ ሰለባዎች ናቸው።

ምንም እንኳን አምላካቸው “የሕያዋን አምላክ” ተብሎ ተጠርቶ በዘመናቸው የእግዚአብሔርን ሃሳብ እያገለገሉ ቢያልፉም፤ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ፣ ሙሴም ሆነ ንጉሱ ዳዊት፣ እንዲሁም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የቀደመው ዘመን ነቢያትና የእምነት ሰዎች፤ ከሰማይ የሆነውና “ሁለተኛው ሰው” የተባለው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ ወደ ሕይወት የሚወስደውን በር እስኪከፍት ድረስ፣ “የዘላለም ሕይወት” የተባለውን ሰማያዊ ተስፋቸውን አላገኙም ነበር። ከእግዚአብሔር መላኩንና የእግዚአብሔር ልጅነቱን ይቃወሙ ለነበሩት አይሁድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር እንዲህ አለ፡- “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሃሴት አደረገ፣ አየም ደስም አለው።” (ዮሃ.8፡56) የዕብራውያን መልዕክት ጸሐፊም ስለቀደሙት የእምነት ሰዎች እንዲህ ጽፎ ነበር፡- “እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፣ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና….” (ዕብ.11፡13)  

በመጀመሪያው አዳም መተላለፍ ምክንያት እግዚአብሔር ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ በኪሩቤልና በምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍ ጠብቆት ወይም ዘግቶት ነበር። በብሉይ ኪዳን የነበሩ መስዋዕቶች ሁሉ ይናገሩ የነበረውም ይህ የተዘጋ የሕይወት መንገድ ሊከፈት የሚችለው በመስዋዕት ብቻ እንደሆነ ነበር። “ኋለኛው አዳም” እና “ሁለተኛው ሰው” የተባለው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለኃጢአት ሥርየት የሚሆን ቅዱስና ሕያው መሥዋዕት አድርጎ በመስቀል ላይ ያቀረበውም ይህንን የሕይወት መንገድ ለመክፈት ነበር ። እጅግ በጣም የሚገርመው እውነት ደግሞ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን የሕይወት መንገድ በሞቱ መክፈቱ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ሕይወት የሚወስደው መንገድም ሆነ እየቆረስን የምንበላው ሕይወት ራሱ መሆኑ ነው። “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ…” ማለቱም ለዚህ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሲሞት በኢየሩሳሌም የነበረው የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከታች ለሁለት መቀደዱ፣ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ የመፍረሱ ምልክት ከመሆኑም በላይ፣ ወደ ሕይወት የሚወስደው መንገድ መከፈቱን የሚያመለክት ነው። ለዚህም ነው የዕብራውያን ጸሐፊ፣ ክርስቶስ በደሙ መርቆ በከፈተልን “በአዲስና በሕያው መንገድ” እግዚአብሔር ወዳለበት፣ ዕረፍትና ዘላለማዊ ሕይወት ወደምናገኝበት መንፈሳዊ ሥፍራ ለመግባት ድፍረት እንደሆነልን የጻፈው። (ዕብ.19-22)

እንግዲህ ክርስትና ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደው የዚህ አዲስና ሕያው መንገድ መገለጫ ነው። ጅማሬውም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምኖ የሞቱንና የትንሣዔውን ፋይዳ በመገንዘብ፤ ማለትም በሞቱ የኃጢአት ሥርየትና ይቅርታ፣ በትንሣዔው ደግሞ ፍጹም የሆነ አዲስ ሕይወት እንደሚገኝ በማመንና ይህንንም በውኃ ጥምቀት መስክሮ ከእግዚአብሔር ዳግመኛ በመወለድ ነው። በዚህም ሂደት ውስጥ ያለፈ አንድ ሰው በአዳም ከሆነው ኃጢአት፣ ሞትና ጨለማ፤ በክርስቶስ ወደሆነው ጽድቅ የተትረፈረፈበት ሕይወትና ወደሚደነቅ ብርሃን ይሻገራል። በኃጢአትና ባለመታዘዝ የወደቀውን ሰው በባርነት ጠፍንጎ ከያዘው የሰይጣን ሥልጣንና አገዛዝ ተላቆ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ወደሚገዛበትና፤ ፍቅርና ሰላም፣ መንፈሳዊ ደስታና ሰማያዊ ዕረፍት ወደሞላበት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መፍለስ ይሆንለታል።  “የሞት መውጊያ” ከተባለው ኃጢአትና ከሥጋ ሥራ ነጻ እየወጣ፣ ወደ እግዚአብሔር መንግስት በሙላት ለመግባት የሚያስችለውን የመንፈስ ፍሬ በሕይወቱ ማፍራት ይጀምራል። በኃጢአት የተበላሸው ሕይወቱ ከላዩ እየተገፈፈ፣ ፍጹምና አዲስ የሆነ ሰማያዊ ሕይወት መልበሰ ይጀምራል። ወንድማችን ጳወሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ሁለተኛ መልዕክቱም የገለጠልን ይህንን እውነት ነው። “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፣ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።” (2ቆሮ.5፡17)

የወንጌልን እውነት እየተቀበሉና በክርስቶስ ባለ እምነት ከእግዚአብሔር በመወለድ አዲስ ፍጥረት የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች የሚጋጠሙትና የሚጨመሩት ደግሞ በተለያዩ ሰዋዊ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ሊከፋፈል ወደማይችል ወደ አንድ መንፈሳዊ አካል ነው። ይህም መንፈሳዊ አካል “የሐዋርያትና የነቢያት መሠረት” በተባለው አንድ ጠንካራ መሠረት - በክርስቶስ ላይ የቆመ፤ መሠረቱ፣ ግድግዳውና ማገሩ፣ ድምድማቱም ጭምር ክርስቶስ የሆነለት አንድ አዲስ ሰው ነው።
“አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤” 1ቆሮ.12፡12